fbpx
AMHARIC

‹‹የፖለቲካ ቀውሱ በውጭ ኃይሎች እንዳይጠለፍ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል›› ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ

  • አገር ለማዳን ሲል ፖለቲካውን ሊቀላቀል እንደሚችል ጠቁሟል

በአገሪቱ የተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ በውጭ ኃይሎች እንዳይጠለፍ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ሲል፣ ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ አስጠነቀቀ፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን የተቃወሙት ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆኑ የተለያዩ አገሮችና ሌሎች የውጭ ኃይሎችም ናቸው ያለው አትሌቱ፣ አዋጁ የሚጎዳው እንደ እሱ ዓይነቱን ኢትዮጵያዊ እንጂ የውጭ ኃይሎችን ባለመሆኑ፣ የፖለቲካ ቀውሱ በሌሎች ሊጠለፍ እንደሚችል ሥጋት እንዳለው ገልጿል፡፡ ‹‹እነዚህ የውጭ ኃይሎች የሚፈልጉት የመንግሥት ለውጥ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ በዘላቂነት ሰላም እንዳይኖራት ማድረግ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይህንን ሴራ ተረድቶ ሊጠነቀቅ ይገባል፤›› ብሏል፡፡

‹‹ሕዝቡ ለሚያነሳው የመብት ጥያቄ እኔም ተባባሪ ነኝ፤›› ያለው ኃይሌ፣ ‹‹ይህ ጥያቄ ግን ከተጠለፈ እንደ ሊቢያ መሆናችን አይቀርም፤›› ሲል አስጠንቅቋል፡፡ የኦሮሞም ሆነ የአማራ ወጣቶች የሚያነሱት ጥያቄ ትክክል መሆኑን የሚገልጸው ኃይሌ፣ ‹‹የመንግሥት ሹማምንት ለዓመታት ሥራቸውን ሳይሠሩ ቆይተዋል፡፡ ሕዝቡም ከ20 ዓመታት በላይ በመልካም አስተዳደር ችግር እየተሰቃየ ነው፡፡ አሁን በወጣቶች የተነሳው ጥያቄ ግን በውጭ ኃይሎች ከተጠለፈ በጣም አደገኛ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያም ቀጣይ ሊቢያ ወይም ሶሪያ የማትሆንበት ምንም ምክንያት የለም፤›› ብሏል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ ጉዳይ ስለማልደራደር ነው ፊት ለፊት መጥቼ ነው የምናገረው፤›› ብሏል፡፡ እሱም ሆነ ሌሎች የአገር ሽማግሌዎች በቅርቡ የተፈቱትን እስረኞች መንግሥት እንዲለቅ ለመሰናበት ጥያቄ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትርን ጨምሮ ሌሎች ባለሥልጣናትን በየጊዜው ይወተውቱ እንደነበር ተናግሯል፡፡

አገሪቷ ለገባችበት የፖለቲካ ቀውስ ሁሉም አካል ወደ ውስጥ መመልከት እንዳለበት የሚናገረው ኃይሌ፣ ሕዝቡ ኢትዮጵያን ማስቀደም ከቻለ ለሁሉም ጥያቄ መልስ ማግኘት ይቻላል ብሏል፡፡

‹‹መንግሥት ምንም የፖለቲካ እስረኛ የለም እያለ ከሰባት ሺሕ በላይ የፖለቲካ እስረኞች መለቀቃቸው ይገርማል፤›› የሚለው ኃይሌ፣ ወጣቱ የሚያነሳው የመብት ጥያቄና የሥራ አጥነት ችግር መፍትሔ ያስፈልገዋል ብሏል፡፡

በቅርቡ ኃይሌ በመገናኛ ብዙኃን ‹በአዲስ አበባ ውስጥ ብሔርተኝነት የለም፣ ይህንን አመለካከትም በመላ ኢትዮጵያ ማምጣት አለብን› ማለቱ ይታወሳል፡፡ ሆኖም ሐሳብህ ብሔርና ቋንቋን መሠረት ያደረገውን ፌዴራሊዝም አይቃወምም ወይ? ተብሎ ተጠይቆ፣ ‹‹ፌዴራሊዝሙ ላይ ብቻ የምናተኩር ከሆነ ኢትዮጵያ የሚለውን ትልቁን ሥዕል ልናጣው እንችላለን፤›› በማለት መልሷል፡፡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል ተከስቶ በነበረው ግጭት ወቅት ሰዎች ላይ ጥቃት የደረሰው ቋንቋን በመለየት መሆኑን አስረድቷል፡፡

አገሪቷ መስቀለኛ መንገድ ላይ መሆኗን ያስታወሰው ኃይሌ፣ ‹‹ይህ ትውልድ የታሪክ ተጠያቂ እንዳይሆን ኢትጵያዊነትን ማስቀደም አለበት፤›› ብሏል፡፡ የትም አገር ሄዶ በድሎት መኖር እንደሚችል የሚናገረው ኃይሌ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን በችግር መኖርን እንደሚመርጥ አስታውቋል፡፡

‹‹የተለያዩ ሰዎች እዚህ መኖር የምፈልገው ኢትዮጵያ ውስጥ ሀብት በማፍራቴ፣ የመንግሥት ደጋፊ ስለሆንኩ ይመስላቸዋል፤›› ያለው ኃይሌ፣ ‹‹በሌላ በኩል ደግሞ የመንግሥት ሰዎች ሁልጊዜ ለምን ትተቸናለህ፤›› በማለት ይጠይቁኛል ብሏል፡፡ በመሆኑም በአንዳንዶች ዘንድ የመንግሥት ደጋፊ በሌሎች ደግሞ ተቃዋሚ ተደርጎ እንደሚፈረጅ ገልጿል፡፡ ሆኖም ኃይሌ ሦስተኛ አማራጭ ይዞ መምጣት እንደሚፈልግ አስረድቷል፡፡

ምንም እንኳን ኃይሌ ከእሱ የተሻሉ ሰዎች ካሉ አገሪቷን እንዲመሩ እንደሚፈልግ ተናግሮ፣ አገሪቱ በዚህ ሁኔታ የምትቀጥል ከሆነ ግን ፖለቲካ ውስጥም ገብቶም ቢሆን አገር ለማዳን እንደሚሠራ ተናግሯል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትሯን እስከማውረድ የደረሰች አገር መሆኗ ምን ያህል ውድቀት ላይ መሆናችንን ያመለክታል፤›› ያለው ኃይሌ፣ አገር ለማዳን ሲባል የሚያስከፍለውን ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል፡፡ አሁን አገር የማዳን ዘመቻ ላይ መሆኑንም ጠቅሶ፣ ‹‹በዚህ ሒደት ግን ፖለቲካ ውስጥ ከመግባትና ፓርቲ ከማቋቋም ባለፈ ሌላ መስዋዕትነት የሚጠይቅ ቢሆን እንኳን፣ እሱን ከመክፈል ወደ ኋላ አልልም፤›› ብሏል፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ስለአገሪቱ ተወያይቶ መፍትሔ ማምጣት አለበት ብሏል፡፡

ምንጭ፤- ሪፖርተር

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram