fbpx

የግብርና ምርቶችን የገበያ ዋጋ መረጃ ለተጠቃሚዎች የሚደርስበት ስርአት እየተዘረጋ ነው

የግብርና ምርቶችን የገበያ ዋጋ መረጃ ለተጠቃሚው ህብረተሰብ የሚደርስበት ብሄራዊ የገበያ መረጃ ስርአት እየተዘረጋ ነው።

የንግድ ሚኒስቴር ለፋናብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሳወቀው ስርአቱ የሚጀመርባቸው 4 ክልሎች እና 30 የገበያ ማእከላት ተመርጠዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እየዘረጋ ያለው ስርአት የ10 ዓመት ፕሮጄክት ሲሆን፥ የመጀመሪያዎቹን 3 ዓመታት ከግብርና ትራንስፎርሜሸን ኤጀንሲ ጋር ያከናውነዋል።

በሚኒስቴሩ የንግድ መረጃ ስራ አመራር ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ይበልጣል አሰፋ እንደተናገሩት፥ ስርአቱ የግብርና ምርቶች የገበያ እለታዊ ዋጋ ለተጠቃሚው ህብረተሰብ የሚደርስበት ነው።

ስርአቱ በተለያዩ ምእራፎች የሚተገበር ሲሆን፥ ለመጀመሪያው ክፍል አራት ክልሎች በናሙናነት መመረጣቸውንም ተናግረዋል።

በእነዚህ ክልሎችም 157 ወረዳዎች የተመረጡ ሲሆን፥ 30 ያህል የገበያ ማእከላት መዘጋጀታቸውንም ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም 300 የሚደርሱ መረጃ ሰብሳቢ ባለሙያዎች ለስርአቱ ተዘጋጅተዋል።

እየተገባደደ በሚገኘው በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ ይጀምራል የተባለው ይህ ስርአት፥ በ5 የግብርና ምርቶች የገበያ ዋጋ ነው የሚጀምረው።

እነዚህ የተመረጡት ምርቶችም ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ሰሊጥ እና ቦሎቄ መሆናቸውን ነው የሚኒስቴሩ መረጃ የሚያሳየው።

ስርአቱ ወደ ስራ ሲገባም የእነዚህ ምርቶች እለታዊ የገበያ ዋጋም በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ መረጃዎች ለተጠቃሚው ህብረተሰብ የሚደርሱ ሲሆን፥ በዚህም ሸማቹም ነጋዴውም ተጠቃሚ ይሆናል።

በዙፋን ካሳሁን – ኤፍ.ቢ.ሲ

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram