fbpx

የደራው ጨዋታ: ማንም ተናግሮለት የማያውቀው የግንቦት 08,1981 ዓ.ም መፈንቅለ መንግስት ሙከራ

በ1980 ዎቹ የመጀመሪያ ሩብ ዓመታት ውስጥ ደቂቃዎች ይበራሉ። ሰዓታት ቀናትና ወራት ይከንፋሉ። ድርጊቶች ጊዜን ይሻማሉ። ሌትም እንደቀን የእንቅልፍ ወጉን አጥቷል። ክንዋኔዎች እየተቀጣጠሉ እየተሰናሰሉ ወደ ፊት ይገሰግሳሉ። ታሪክ ይሰራል፤ ይገነባል፤ያድጋል። ዓላማ ከሰንደቅ ላይ ከየአቅጣጫው ይውለበለባል። ላንዱ ወገን እንደታቦት ይመለካል። ሌላው እንደ ሰብዓ ሰገል ኮከብ በመሪነት ይታወቃል። መፈክሮች በየከተማው፣ በየጋራው፣ በየሸንተረሩ፣ በየሜዳው፣ በየምሽጉ ያስተጋባሉ።

መድፎች ያጓራሉ፤ ሚሳይልና ሮኬት ይወነጨፋሉ፤ ታንኮች ይርመሰመሳሉ። ጥይቶች ይንጣጣሉ፤ ቦንቦች ይፈነዳሉ፤ሚግና ሄልኮፕተሮች እቶን ያስታውካሉ፤ ሳንጃ ለሳንጃ ይሞሻለቃል፤ደም እንደ ጎርፍ ይፈሳል። አካል ይበሳል፤ ይሰነጠቃል፣ ይቦደሳል፣ ይጎመዳል፣ ይደቃል፣ ይጨሳል፣ … ሕይወት ከሞት ይተናነቃል።

ግብግብ ነው! ትግል ከወደ ሰሜኑ ይበልጥ ይታያል፤ ይበልጥ ይሸታል፤ይበልጥ ይጨበጣል፤ ይበልጥ ይሰማል።

ሬዲዮ ጣቢያዎች ከከተማና ከበረሃው ከምን ጊዜም የበለጠ የሚያስተጋቡት ይህንኑ ነው። ትግል ሽንፈትና ድል-ትግል-ትግል…

ደርግ ሰራዊቱን፣ስንቁንና ትጥቁን ከከተማ ወደ በረሃ ያዘምታል። የነፃነት ታጋዮች ኃይላቸውን ከበረሃ ወደ ከተማ ያዘምታሉ።ጉዞ በሞት ፅልመት ውስጥ ነው። በእሳት ነበልባል ውስጥ። ሰው ብቻ ሳይሆን የዓላማም ምንነት የሚፈተንበት እሳት። የዓላማ ፅናት በድል አድራጊነት የሚረጋገጥበት ጉዞ።

በዚህ ሂደት የደርግ ሰፊ ግዛቶች ቀስ በቀስ እየጠበቡ ሄደዋል። ከቀበሌዎች አልፎ ወረዳዎች፣ ከወረዳዎች አልፎ…

የካቲት 1980 «ዘመቻ ድልድል» በተባለ ስምሪት የትግራይ ህዝብ ሽሬ፣ አክሱም፣ አድዋ፣ አዲግራት፣ ውቅሮ፣ ማይጨውና ኮረም ላይ ደርግን ገጠመ። የቀዳማይ ወያኔ የትግልና የድል ድባብ ገዘፈ፤ መሬት ቀውጢ ሆነች፤ ሰማዩ ቀላ። 604ኛ ኮር ተመታ። ከአፍሪካ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ተብሎ ይነገርለት የነበረው ሰራዊት ተፈታ። «እፍኝ የማይሞሉ ወንበዴዎች» ይባሉ በነበሩበት የትግራይ ልጆች ተረታ።

ለሰሚው የሚገርም ነበር በተለይ ላልጠበቀው። እውነታው ለደርግ ለእራሱ እንኳን የሚታመን አልሆን አለ። የኢሠፓ መሪ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለ ማርያም የጦርነቱን ቪድዮ አይቶ የፈጠራ ስራ ነው አለ። ወያኔ ያቀነባበረው ፊልም ነበር የመሰለው። ይህንኑም ነበር ለሕዝብ የገለፀው።

ወዲያው የኢሠፓ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴና ማዕከላዊ ኮሚቴ ተሰብስቦ መከረ። ትግራይ ላይ ጊዜያዊ አዋጅ አወጀ። ነፃ የወጡትን አውራጃዎች መልሶ ለመያዝና ተቃዋሚ ኃይሎችን እስከ መጨረሻው ለመደምሰስ የጦርነት እቅድ ወጣ። ደርግ ከስራ አስፈፃሚ አባላት መካከል ታማኙን ለገሠ አስፋውን በዋና ጦር አዝማችነት መደበና ወደ መቀሌ ላከ። በቀድሞው ውጊያ ተበታትኖ የነበረው የ604ኛ ኮር ኃይል በስንቅና በጦር መሳሪያ እንደገና እንዲጠናከር ተደረገ። መቀሌ በበርካታ የደርግ ሰራዊትና የፈንጅ አጥር ቀለበት ታጠረች። ከተለያየ አቅጣጫ መጠነ ሰፊ የደርግ የጥቃት ንቅናቄ ተጀመረ። ህወሓት ስልታዊ ማፈግፈግ ለማድረግ አክሱምን፣ ሽሬን፣አድዋን ለቆ ወደ ኋላ ኃይሉን ሳበ።

ደርግ አሳውን ለማጥፋት ከባሕሩ ቀይ ውሃ እየቀዳ አፈሰሰ። ብዙ አፈሰሰ፤ ግን ሊደርቅ አልቻለም። የሠላም ጭምጭምታ ደግሞ መናፈስ ጀመረ። ድርድሩ ከኤርትራ ነፃ አውጭ ግንባር ጋር ብቻ እንጂ ከሌሎች ተቃዋሚ ኃይሎች ጋር ሊሆን እንደማይችል ደርግ ይፋ አደረገ። እፍኝ ከማይሞሉ የትግሬ ወንበዴዎችና ሽፍቶች ጋር እንዴት ባንድ ጠረጴዛ እቀመጣለሁ አለ። ክብረ ነክ ሆነበት። በትግራይና በወሎ የሚንቀሳቀሰው ነፃ አውጪ ደግሞ በመከላከሉና በመልሶ ማጥቃቱ ገፋበት።

የ1981 ዓ.ም የካቲት ወር እየገሠገሠ ደረሰ። የደርግ 604ኛ ኮር እንደገና ተደመሰሰና በርካታ የትግራይ ከተማዎች ነፃ ወጡ። ከ22ሺ ወታደር በላይ ተማረከ።

የህወሓት ወደ ፊት መግፋት ደርግን አሳሰበው፤ አስጨነቀው። እና የፖለቲካ ስሌት አደረገ። ምጣኔ ሀብታዊ ሂሳብ አሰላ። ከትግራይ የሚገኘውን ትርፍና ኪሳራ ደማምሮ ቀነሰ። በትግራይ ፋብሪካ የለም፤ የመንግስት እርሻ የለም። ያለው ሕዝብ ነው። በትግራይ ያለው ትግል ነው። በትግራይ የሚያጋጥመው ተደጋጋሚ ሽንፈት ነው። እና ይህች በጠላ ንግድ ኢኮኖሚ የምትዳክር ትግራይ ለኢትዮጵያ አክሳሪ ናትና ትቅርብኝ ሲል የተራረፈውን ጓዙን ጠቅልሎ የካቲት 13 ቀን 1981ዓ.ም ከመቀሌ ወጣ። የታሪክ ኮከብ ልዩ የበረራ አቅጣጫ።

የትግራይ ሙሉ በሙሉ ነፃ መውጣት የሚያሳየው የደርግን ኃይል ማጣት ሳይሆን በጥቂት ታጋዮች የተጠነሰሰው የነፃነት እንቅስቃሴ ጎልብቶ ከፍተኛ እርከን ላይ መድረሱን ሆነ። ደርግ በሕዝብ ዘንድ የነበረውም ተቀባይነት ዝቅተኛ መሆኑን ለዓለም አቀፍ ሕብረተሰብ ይፋ አወጣበት። ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለእራሱም ሰራዊት አበክሮ አጋለጠበት።

ከመጋቢት 1 እስከ መጋቢት 4ቀን 1981 ዓ.ም በተደረገው የህወሓት 2ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ደግሞ የትግራይ ሕዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር ተሰልፎ ደርግን ለመደምሰስ ቆርጦ መነሳቱን ለወታደራዊው መንግስት አረዳ። የኤርትራም ሕዝብ ትግል በጦርነት ሊከስም እንደማይችልና ይልቁንም እየጎለበተ መጥቶ ከሌሎች የነፃነት ንቅናቄዎች ጋር በመዳመር ሊጥለው እንደተቃረበ ለደርግ አስገነዘበ።

አጠቃላይ የጦርነቱ ሂደት በተለይም ተደጋጋሚው ሽንፈት በደርግ በእራሱም ውስጥ ቅራኔን ጠነሰሰ። በዚህ ሳቢያ ተራው ሰራዊት ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የጦር አዛዦችና መኮንኖች በሰራዊቱ ፊት በደርግ ታማኞች በሳንጃ ተወጉ፤ በጥይት ተደበደቡ። ቅራኔው ተካርሮም ግንቦት 1981 ዓ.ም አስመራና አዲስ አበባ ላይ የገዛ መንግስታቸውን እንገለብጣለን ብለው እርስ በእርሳቸው በየተራ ተገለባበጡ።

ቀድሞ ከሩብ ሚሊዮን በላይ የሆኑትን ወጣቶች በቀይ ሽብር ቁርስ እንዳደረገ ሁሉ፤ መንግስቱ የግልበጣ ሴራውን ለማክሸፍ የእራሱን ጀኔራሎችና ከፍተኛ መኮንኖች ምሳ አደረገ።

ይህን ውስጣዊና ውጫዊ ውጥረት ለማርገብና ፋታ ለማግኘት ደርግ በእንግሊዝና በኢጣሊያ መንግስታት የተሰነዘረውን የሰላም ድርድር ጥሪ ለመቀበል ተንበረከከ። ግንቦት 28ቀን 1981 ዓ.ም ሸንጎውን ለአስቸኳይ ጉባኤ ጠርቶ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከሁሉም ተቃዋሚ ኃይሎች ጋር ለመወያየት ፍቃደኛ መሆኑን በይፋ ገለፀ። ስለ ሰላም ዘመረ።

ጥቅምት 1982 ሮም ላይ ለድርድር ሊቀመጥ ዝግጅት ማድረግ ጀመረ። እግረ መንገዱን ሠራዊት ምልመላና ስልጠና ስንቅና ትጥቅ ዝግጅቱን ከወትሮ በበለጠ አፋፋመ። ለሰላም ድርድሩ ይህን መሰናዶ ማድረጉ ለነፃ አውጪ ድርጅቶች ያረጋገጠው አንድ ነገር አለ። የደርግ የተፈጥሮ ባህሪ ጦረኛነት እንጂ ሰላማዊ አለመሆኑን። በግድ እንጂ በውድ ወደ ሰላም ውይይት የማይመጣ መሆኑን። ስለዚህም በትግል ወደ ሰላም ሊገፉት ህወሓትና ኢህዴን ከሰኔ 29/1981 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 1 ቀን 1981ዓ.ም ተገናኝተው የመጀመሪያ መደበኛ ጉባኤ አድርገው መከሩ። ሁለቱም ተዋህደው ወደ ኢህአዴግነት ተሸጋገሩ።

ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድከገጽ 175-180

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram