fbpx

የይቅርታና ክስ የማቋረጥ ሂደቱ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው- መንግስት

የይቅርታና ክስ የማቋረጥ ሂደቱ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ገለፁ።

የይቅርታና ክስ የማቋረጥ ሂደቱ ህብረተሰቡ በተለያዩ ጊዜያት በፍትህ ዘርፍ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የሚመልስ መሆኑንም አቶ አህመድ ገልፀዋል።

መንግስት በሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩ የ27 ግለሰቦችና 4 ድርጅቶች ክስ እንዲቋረጥ፤ 576 ታራሚዎችም በይቅርታ እንዲለቀቁ እንዲሁም በሽብር ወንጀል የተከሰሱ 137 ተጠርጣሪዎች ክስ እንዲቋረጥ ማድረጉ ይታወሳል።

ሃላፊ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ይህንን አስመልክተው ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ የይቅርታና ክስ የማቋረጥ ሂደቱ ዋና አለማ የህብረተሰቡን ጥቅም ማስጠበቅ ነው ብለዋል።

የተቋረጡት ክሶችም ሀገራዊ መግባባትን፣ ሳላምና ደህንነትን የሚያመጣ እንዲሁም ህብረተሰቡ ከፍትህ ስርአት ጋር ተያይዞ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በመመለስ ረገድ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ታምኖባቸው መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ።

ሂደቱም የህግ መሰረት ያለውና መስፈርቱም የህዝብ ጥቅም መሆኑን ሃላፊ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ተናግረዋል።

አቶ አህመድ አክለውም፥ የተጠርጣሪዎችን ክስ ማቋረጥና ታራሚዎችን በይቅርታ መልቀቅ በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ስርአት ውስጥ በፊት ጀምሮ የነበረ አሰራር መሆኑን ገልፀዋል።

የአሁኑን ለየት የሚያደርገው ግን በጥልቅ ተሃድሶ ወቅት ሰዎች አላግባብ ይታሰሩ እንደነበርና የፍትህ መጓደልም በስፋት ይታይ እንደነበር ህብረተሰቡ ሲያነሳ ስለነበር ምላሽ ለመስጠት የተካሄደ ነው ብለዋል።

የኢህአዴግ ስራ አስፈሚ ኮሚቴም በእስር ላይ ያሉ ሰዎችን መልቀቅ የገባውን ቃል ለመፈጸምምና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋትም የተወሰደ እርምጃ ነው።

አቶ አህመድ፥ የክስ መቋረጡ ዋና አለማ የተፋጠነ ፍትህ ባልተሰጠበት እነዚህን ሰዎች በማረሚያ ቤት አስቀምጦ እነሱንም፤ ቤተሰቦቻቸውንም ማንገላታት የህግ የበላይነትን የሚያረጋግጥ በመሆኑ ነው ብለዋል።

የተዘጉ የግለሰቦች ድርጅቶችም ቢሆኑ ክሳቸው የተቋረጠው ኪሳራው ተመዝኖ ነው ብለዋል አቶ አህመድ።

አቶ አህመድ አክለውም፥ በሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩት ግለሰቦችና ድርጅቶች ክስ መቋረጥ መንግስት በፀረ ሙስና ትግሉ ላይ ያለው አቋም ተለሳልሷል ማለት እንዳልሆነ ገልፀዋል።

መንግስትም የፀረ ሙስና ትግሉን በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ፣ በመረጃና ማስረጃ ላይ ተመስርቶ የተፋጠነ ፍትህ ሊያሰጥ በሚችል መልኩ በማካሄድ ላይ መሆኑንም አንስተዋል።

መንግስት አሁን እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎችም ለዓመታት እየተንከባለሉ የመጡትን ችግሮች በአፋጣኝ በመፍታት በቀጣይ ትኩረቱን በልማት እና ብሄራዊ መግባባት መፍጠር ላይ እንዲያተኩር የሚያግዙ ናቸው ብለዋል አቶ አህመድ።

እርምጃዎቹ አስፈላጊ መሆናቸውን በመገንዘብ ለብሄራዊ መግባባት እና ለሀገር ግምባታ ሁሉም አካል ከመንግስት ጋር በጋራ እንዲጠቀምበት ሃላፊ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ መልእክት አስተላልፈዋል።

በትእግስት ስለሺ-

ኤፍ.ቢ.ሲ

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram