fbpx

የዝንጅብል ውሃ ጠቀሜታዎች

ዝንጅብል ለጤና በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ይነገራል።

ዝንጅብልን አጥቦ በማፍላትና በመጭመቅ በፈሳሽ መልክ መጠቀም እንደሚቻልም ባለሙያዎች ይመክራሉ።

በዚህ መልኩ የዝንጅብልን በፈሳሽ መልክ ለማዘጋጀት ደግሞ፤ በመጀመሪያ ዝንጅብሉን አጥቦ ማዘጋጀትና አድርቆ መፍጨት አልያም ፈጭቶ ማዘጋጀት።

ከዚያም 1 ተኩል የሾርባ ማንኪያ የዝንጅብል ዱቄት በአራት የሻይ ብርጭቆ ውሃ ከ5 እስከ 10 ደቂቃ ማፍላትና አውጥቶ ማቀዝቀዝ።

ምናልባት ዝንጅብል ካለው ጣዕም አንጻር ብቻውን መጠጣት ለሚከብዳቸው ሰዎች ዝንጅብሉ ላይ ጥቂት ማር አልያም ሎሚ በመጨመር መጠቀም።
የዝንጅብል ውሃ ጠቀሜታዎች፦

የህመም ስሜትን ለማስታገስ፦ የዝንጅብልን ውሃ በሚመለከት ለበርካታ አመታት በተደረገ ጥናት ከቀላል የህመም ስሜት ጀምሮ እስከ ከባድ ራስ ምታት (ማይግሬይን) ድረስ ያሉ የህመም ስሜቶችን ለመፈወስ ይረዳል።

ማቅለሽለሽና ማስመለስን ለማስታገስ፦ ከምግብ አለመስማማት አልያም በሚወስዱት መድሃኒት የሚፈጥርብዎ ስሜትና እንደ ጨረርና መሰል ባሉ የህክምና ሂደቶች ላይ በሂደት ሊፈጠር የሚችልን የማቅለሽለሽና ማስመለስ ስሜት ለመከላከል ያግዛል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ የሚችሉ ስሜቶችን ለማስታገስም ሳይበዛ በጥቂቱ ይህን መጠቀም ይረዳል።

በሰውነት ውስጥ የቅባት መጠንን ለመቀነስ፦ በሰውነት ውስጥ ከፍተኛ የስብና የቅባት ክምችትን ለመቀነስ ይረዳል።

ተመራማሪዎች በአይጦች ላይ ባደረጉት ሙከራ ይህን ማረጋገጥ መቻላቸውን ይገልጻሉ።

በሰውነታቸው ውስጥ ከፍተኛ የስብ ክምችት ያለባቸውን አይጦች ዝንጅብል በመስጠት የቅባት ክምችታቸውን መቀነስ ማስወገድ እንደቻሉም ገልጸዋል።

በደም ውስጥ የስኳር መጠንን ለመቆጣጠር፦ በደም ውስጥ የስኳር መጠንን መቆጣጠርና መከላከል ይችላል።

ይህ ደግሞ በተለይም አይነት 2 የስኳር በሽታ ላለባቸው ሰዎች እጅጉን እንደሚረዳም ነው የሚነገረው።

ባለሙያዎቹ ለተከታታይ 12 ሳምንታት የአይነት 2 የስኳር በሽታ ተጠቂ የሆኑ ሰዎች ላይ ባደረጉት ጥናት ይህን አረጋግጠናል ነው ያሉት።

በጥናታቸው ያካተቷቸውን ሰዎች በሁለት ምድብ በመክፈል፥ በአንደኛው ቡድን የሚገኙ ሰዎች የዝንጅብል ውሃ በብዛት እንዲጠጡ ሲደረግ በሌላኛው ቡድን ያሉ ሰዎች ደግሞ ሌላ መድሃኒት እየወሰዱ ቆይተዋል።

ከተባለው ጊዜ በኋላም የዝንጅብል ውሃ ሲጠጡ የነበሩት ሰዎች በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን እንዳይጨምር በማድረግ መቆጣጠር መቻላቸውን ገልጸዋል።

ክብደት ለመቀነስ፦ በዚህ ጥናት በሁለት ምድብ የተከፈሉ ሰዎች ከምግብ በኋላ የፈላ ዝንጅብል እንዲጠጡና ሌሎች ደግሞ ውሃ ብቻ እንዲጠጡ በማድረግ ረዘም ላለ ጊዜ ጥናት አድርገዋል።

በዚህም ከምግብ በኋላ የፈላ ዝንጅብል የሚጠጡት ውሃ ከሚጠጡት በተሻለ የመጥገብ ስሜት እንደተሰማቸው ተናግረዋል።

ይህ ደግሞ የመጥገብ ስሜት የተሰማቸው ሰዎች ተጨማሪ ምግቦችን ካለመብላታቸው ጋር ተያይዞ ክብደትን ለመቆጣጠር በሚያደርጉት ጥረት አጋዥ ነው ተብሏል።

ከላይ ከተጠቀሱት ባለፈም የዝንጅብል ውሃ ወቅትን ተከትለው ለሚከሰቱ የአለርጅ ችግሮችን ለመከላከል፣ ከባድ ጉንፋንና በመጥፎ ሽታ የሚከሰቱ የአፍንጫና ጉሮሮ መዘጋትን ለማከም ይረዳል።

ከዚህ ባለፈም ባክቴሪያና በቫይረስ እንዳይጠቁም ይህን አትክልት ከምግብ ጋር አልያም ከሻይና ከውሃ ጋር ቀላቅለው መጠቀምም ይችላሉ።

ይሁን እንጅ ይህን አትክልት ሲጠቀሙ መጠኑን ማብዛት አይመከርም፤ በአንዳንድ ህክምናዎች ዝንጅብል ደም ለማቅጠን ጥቅም ላይ መዋሉና በብዛት ሲወሰድ የሆድ መነፋት ስሜት ማምጣቱ አወሳሰዱ ላይ ጥንቃቄ እንዲኖር ያስገድዳል።

በጣም ከበዛ የልብ አካባቢ ማቃጠል ስሜት፣ ማስቀመጥ፣ ሆድ አካባቢ ምቾት የመንሳት ስሜት ሊኖረው ስለሚችል በብዛት መጠቀም እንደማይገባም ባለሙያዎች ይመክራሉ።

ምንጭ፦ medicalnewstoday.com

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram