የክልሉ ህዝብ የተጀመረውን እንቅስቃሴ እንዲደግፍ ጥሪ ቀረበ

የኦሮሚያ ክልል ህዝብ በመንግስት የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎችን በትኩረት፣ በትዕግስትና በአንድነት መንፈስ እንዲደግፍ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ ጥሪ አቀረቡ።

የክልሉ ምክር ቤት (ጨፌ) 5ኛ የስራ ዘመን 3ኛ ዓመት 7ኛ መደበኛ ጉባዔ በአዳማ ገልማ አባ ገዳ ዛሬ ተጀምሯል።

የክልሉ የ2010 በጀት ዓመት የ6 ወር ዕቅድ የአፈጻጻም ሪፖርት ለምክር ቤት (ጨፌ) ቀርቧል።

የግማሽ ዓመት የስራ አስፈጻሚ የዕቅድ አፈጻጻም ሪፖርት ያቀረቡት ፕሬዚዳንት ለማ ከተከናወኑት በርካታ ተግባራት በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ በተከሰተ ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎችን መልሶ የማቋቋም ስራ አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉና በአጎራባች ክልሎች መካከል ለተነሱት ግጭቶች መፍትሄ ለመስጠትና በአገሪቱ ክልሎች፣ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መካከል የተጠናከረ አንድነት ለመፍጠር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ስራዎች መከናወኑንም ጠቁመዋል።

በኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፍ በተለይ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተሰሩ ስራዎች መልካም እንደሆኑም በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

የተፈጠረውን መነሳሳት ውጤታማ ለማድረግ የክልሉ ህዝብ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎችን እንዲያግዝም ፕሬዚዳንቱ ጠይቀዋል።

ጨፌው ያለፈውን ጉባዔ ቃለጉባዔ በማጽደቅ የተጀመረ ሲሆን የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ/OBN/ ማቋቋሚያ አዋጅ፣ በክልሉ መንግስት የፋይናንስ አስተዳደር ረቂቅ ህግና የተለያዩ ሹመቶችን እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል።

የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት 537 አባላት እንዳሉት ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

Share your thoughts on this post

Advertisements
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram