fbpx

የኦዲት ግኝት ለማረም ፈቃደኛ ያልሆኑ ተቋማት ቁጥር አየጨመረ መምጣቱን የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ገለጸ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፓርት እንደገለፀው የኦዲት ግኝት ለማረም ፈቃደኛ ያለሆኑ ተቋማት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ አየጨመረ መጥቷል።

ከ2002 እስከ 2008 ባሉ ተከታተይ ዓመታት በተለያዩ ተቋማት ላይ የታዩ የኦዲት ግኝቶች ላይ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ መረጃው የተሰጠው ቢሆንም እስካሁን ምንም እርምጃ ያለመውሰዱን ዋና ኦዲተሩ ለምክር ቤቱ ማቅረባቸው ነው የተገለጸው።

ለፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የእምቢተኞች ዝርዝር ቢላክም መስሪያ ቤቱ ለኦዲት ተደራጊ መስሪያ ቤቶች ተገቢውን እርምጃ ወስደው እንዲያሳውቁ ደብዳቤ ከመፃፍ ውጭ በተጨባጭ የተገኘ ውጤት የሌለ መሆኑንም ዋና ኦዲተሩ አስረድተዋል።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱብሶ የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶች 2009 በጀት ዓመት ሂሳብና ክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት የኦዲት ግኝት ሪፖርት በተለያዩ ጊዚያት የተገኙባቸው ተቋማት ቁጥር እያደረ መቀነስ ሲገባው እየጨመረ መሄዱን ተናግረዋል።

በዚህም የኦዲት ግኝት ተቀባይነት የሌለው አስተያየት የተሰጠባቸው መስሪያቤቶች ቁጥር በ2007 ዓ.ም 37 የነበረ ሲሆን ይህ አሃዝ በ2008 እና በ2009 ዓ.ም ቁጥሩ ወደ 53 ከፍ ማለቱን ነው የገለጹት።

ከዚህ በተቃራኒው በዋና ኦዲተር መስሪያቤቱ የኦዲት ግኝት የሌለባቸው ተቋማት ቁጥር በ2007 ዓ.ም ከነበረበት 36 በ2008 ወደ 27 እና በ2009 ወደ 25 ዝቅ ማለቱን ነው ያስታወቁት።

በኦዲት ግኝቱ ተቀባይነት የሚያሳጣ አስተያየት የተሰጠባቸው እና ነቀፌታ የሌለባቸው መስሪያ ቤቶች በኦዲት ግኝቱ ተምረንበታል ኦዲቱ ጠቅሞናል ቢሉም መሻሻል እንዳላሳዩም ዋና ኦዲተሩ አመላክተዋል።

እነዚህን ችግሮች ለማስተካከል በምክር ቤቱና በምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች እንዲሁም በገንዘብና ኤኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር በኩል እየተደረገ ያለውን ድጋፍ ገንቢ መሆኑን ዋና ኦዲተሩ በሪፖርታቸው ጠቁመዋል።

ኤፍ.ቢ.ሲ

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram