‹‹የኦሮሚያን ተማሪዎች ከጅግጅጋ የሶማሌን ክልል ተማሪዎች ከኦሮሚያ ውጪ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች መመደብን አላምንበትም››
አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር፣ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር
አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ናቸው፡፡ ክልሉን ላለፉት ስድስት ዓመታት መርተዋል፡፡ እሳቸው የሚመሩት ክልል ከኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ጋር በነበረው ግጭት በርካቶች ሕይወታቸውን እንዳጡና በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩት ደግሞ ከቀያቸው እንደተፈናቀሉ ይታወቃል፡፡ ሪፖርተር ሐረር ከተማ ድረስ በመሄድ ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆችን በማግኘት ሰፊ ዘገባ መሥራቱ አይዘነጋም፡፡ በሶማሌ ክልል ከፍተኛ በደል ደርሶብናል ያሉ ተፈናቃዮችን በተመለከተ፣ የሶማሌ ክልል ኃላፊዎችን ለማነጋገርና በሌሎች ጉዳዮች ላይ መረጃ ለማግኘት በተደጋጋሚ ጊዜ ቢሞከርም አልተሳካም ነበር፡፡ ነገር ግን ዓርብ ኅዳር 1 ቀን 2010 ዓ.ም. የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤትና የክልሎች ኃላፊዎች ውይይት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰብሳቢነት ሲደረግ፣ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የነበረውን ግጭትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ በተጣበበ ጊዜ ውስጥ ዘመኑ ተናኘ ከአቶ አብዲ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል፡፡
ሪፖርተር፡- ከወራት በፊት በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት እንደነበረ ይታወሳል፡፡ ግጭቱ አሁን ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አቶ አብዲ፡- በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት የተነሳ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፡፡ አሁን ግን እየተሻሻለ ነው፡፡ በሁለቱም በኩል የተፈናቀሉ አሉ፡፡ በፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር አማካይነት በወጣው ዕቅድ መሠረት፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡ ሌሎችም እንዳይፈናቀሉ እየሠራን ነው፡፡ መፈናቀሉ በፍፁም መሆን ያልነበረበት እንደነበር እንደ ሶማሌ ክልል እናምናለን፡፡ ሁለቱ ወገኖች ወንድማማች ናቸው፡፡ በዚህ በወሰን ግጭት ምክንያት ከዚህ በፊት እየተጋጩ እንደገና በሽምግልና እየፈቱ ነው የመጡት፡፡ ይኼ ግን አዲስ ነገር ሆነብን፡፡ በተለይ አወዳይ አካባቢ ባለፈው ጊዜ የተፈጠሩ ችግሮች ነበሩ፡፡ ሆኖም አሁን ያለፈው አልፏል፡፡ ሁለተኛ ይኼ ችግር እንዳይከሰት፣ የተፈጠረውን ችግር በመፍታት ወንጀለኞችን ወደ ሕግ ማቅረብ አስፈላጊ ነው፡፡ በሁለቱም በኩል ችግር የፈጠሩ ወደ ሕግ እንዲቀርቡ እየተሠራ ይገኛል፡፡
ሁለተኛም እንደዚህ ዓይነት ነገር እንዳይደረግ መሠራት አለበት፡፡ ተፈናቃዮች ደግሞ ወደቦታቸው መሄድ አለባቸው፡፡ ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉትን እኛው ራሳችን ኃላፊነት ወስደን ወደ ክልሉ የሚመለሱበትን መንገድ ማመቻቸት አለብን፡፡ እናደርጋለን ብዬ አምናለሁ፡፡ ተፈናቃዮቹ ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ በዚያ በኩልም መሠራት አለበት፡፡ ከሶማሌ የተፈናቀሉትን ወደ ቦታቸው መመለስ ግድ ነው፡፡ ስለዚህ ሁለቱ ሕዝቦች ለረዥም ጊዜ አብረው የኖሩ፣ ለረዥም ጊዜ ከመኖራቸው አኳያ በተለያዩ መንገዶች የተሳሰሩ ናቸው፡፡ በባህልም፣ በጋብቻም በብዙ ምክንያቶች የተሳሰሩ ናቸው፡፡ ነገር ግን በተፈጠረው ሁኔታ በጣም አዝነናል፡፡ ለወደፊቱ እንደዚህ ዓይነት ግጭት እንዳይፈጠር አቅደን እየሠራን እንገኛለን፡፡
ሪፖርተር፡- በ2009 ዓ.ም. ሚያዝያ ወር እርስዎና የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ሁለቱ ክልሎች በፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር አዳራሽ ዳግመኛ ግጭት እንዳይከሰት ተፈራርማችሁ ነበር፡፡ እርስዎም ሆኑ አቶ ለማ የሁለቱን ክልሎች ሕዝቦች በልማት ማስተሳሰርና የግጭት መነሻ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት ሰፊ ሥራ ለማከናወን ቃል ገብታችሁ ነበር፡፡ ይኼ ከተደረገ በኋላ በድጋሚ ዳግመኛ ግጭቱ የማገርሸቱ ምክንያት ምንድነው ብላችሁ ነው በእናንተ በኩል የገመገማችሁት?
አቶ አብዲ፡- ባልሳሳት ሁለቱ ክልሎች 148 ቀበሌዎች ነው የሚጋሩት፡፡ ከዘጠኝ ቀበሌዎች በስተቀር ሌላውን ሕዝቡ ነው የተስማማው፡፡ ከታች ማለት ነው፡፡ በወቅቱ ወደ ዘጠኝ ቀበሌዎች ብቻ ናቸው የተስማሙት፡፡ በክልል ወይም በፌዴራል ደረጃ የተስማማንባቸው ትንሽ ቀበሌዎች ናቸው፡፡ በሙሉ ኅበረተሰቡ ነው የተስማማው፡፡ የቆመበትን መንገድ ይኼ ነው ብዬ አላውቅም፡፡ በእርግጥ ቆሟል፡፡ ግጭቱ የተከሰተው በዚህ ምክንያት ነው ከተባለ ፋይዳ ስለሌለው ሰላም የሚመጣበትን መንገድ ማመቻቸት ነው የሚሻለው፡፡ አሁን እከሌ እንደዚህ አድርጓል፣ እኛ እንደዚህ ነን ማለት አልፈልግም፡፡ ምክንያቱም መስማማትን አያመጣም፡፡ ሰላምን አያመጣም፡፡ ሰላምን የሚያበላሹ ቃላትን መናገርም አልፈልግም፡፡ እዚህም ሆነ እዚያ አንዴ ችግር ተፈጥሯል፡፡ የአንድ አገር ዜጎች ተጣሉ፡፡ ችግር ተፈጠረ በቃ ይኼ ነው፡፡ ምክንያቱ ይኼ ነበር ከሚባል ችግሩ እንዳለ አውቀን የተፈናቀሉትን ማቋቋም ነው ተገቢ የሚሆነው፡፡ በሁለቱም በኩል የሞቱ አሉ፡፡ ያ መጥፎ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በግጭቱ ሳቢያ በእናንተ ክልል ውስጥ ተጠልለው ያሉ ዜጎች ቁጥር ምን ያህል ነው?
አቶ አብዲ፡- እውነት ለመናገር በእኛ ክልል ያሉት ተፈናቃዮች ብዙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በጅግጅጋ ብቻ ከ50 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች አሉ፡፡ በግጭቱ ምክንያት ተፈናቅለው የመጡ ናቸው፡፡ ይኼ ቁጥር በግለሰብ ደረጃ ነው፡፡ ሁለት ሺሕ ቤተሰብ አካባቢ ይሆናል ማለት ነው፡፡ እነዚህ ግን በጅግጅጋ ብቻ ያሉት ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- ከጅግጅጋ ውጪ አሉ የሚባሉት የት አካባቢ ነው ያሉት? ቁጥራቸውስ?
አቶ አብዲ፡- የተፈናቀሉትን ለማቋቋም በክልልና በፌዴራል ደረጃ ሥራዎች እየተሠሩ እንደ ክልልም እያገዝናቸው ነው፡፡ ግን ለወደፊቱ ወደ ቤታቸው ቢመለሱ ደስ ይለናል፡፡ ምክንያቱም እዚያ እንደ ስደተኛ ነው የተቀመጡት፡፡ ኦሮሚያ ያለው በስደተኛ መልክ ነው የተቀመጠው፡፡ እኛ ጋ በስደተኛ መልክ ነው የተቀመጡት፡፡ ለምሳሌ ሰለሃደ የተፈናቀሉ አሉ፡፡ ሰለሃ ወረዳ አሉ፡፡ ለከዳ ወረዳ አሉ፡፡ ሊበን ዞን አሉ፡፡ በእነዚህ ሁሉ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎች አሉ፡፡ ዋናው የተፈናቀሉት ወደ ቤታቸው መመለስ አለባቸው፡፡ ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉትን ሶማሌ ክልል ራሱ ሂዶ ፈልጎ መመለስ አለበት ማለት ነው፡፡ ከዚያም ከኦሮሚያ የተፈናቀሉትን የኦሮሚያ መንግሥት ራሱ ፈልጎ መመለስ መቻል አለበት በማለት ወደዚያ እየገባን ነው ያለነው፡፡ ከኦሮሚያ ክልልም ሆነ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ እየሠራን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት ጋር ምን ያህል ተቀራርባችሁ እየሠራችሁ ነው?
አቶ አብዲ፡- እየተነጋገርን ነው፡፡ ሰላም መምጣት አለበት፡፡ ዋናው የተፈናቀሉት ወደ ቀዬአቸው መመለስ አለባቸው፡፡ የመጀመርያው አጀንዳ የተቸገረ ሕዝብ አለ፡፡ እነዚህ ወገኖች ወደ ቤታቸው መመለስ አለባቸው ማለት ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ እየተነጋገርን ነው፡፡ እንደገና ደግሞ ግጭቶች መቆም አለባቸው፡፡ የሁለቱ ክልሎች ታጣቂ ኃይሎች ከዚያ አካባቢ እንዲርቁ እየተነጋገርን ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥት ገብቶ እዚያ መሣሪያ የያዘውን ለሕግ ማቅረብ አለበት፡፡ መሣሪያ የያዘ እዚያ አካባቢ መምጣት የለበትም በማለት እየተስማማን ነው፡፡ ፌዴራል ፖሊስና መከላከያ እዚያ ይገባል፡፡ መሣሪያ ይዘው የሚዘዋወሩ ከሕዝብ በስተቀር ወደ ሕግ እንዲቀርቡ እየተስማማን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- እንደሚታወቀው በግጭቱ ወቅት በሶማሌ ክልልና በኦሮሚያ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ቢሮዎች የሚሰጡ መግለጫዎች ነበሩ፡፡ በተለይ በእናንተ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ በኩል ይሰጡ የነበሩ መግለጫዎች ብዙ ጥያቄዎች ይነሳባቸው ነበር፡፡ በሚዲያዎች ጭምር መነጋገሪያ ነበሩ፡፡ ይህንን ጉዳይ እናንተ እንዴት ነው የገመገማችሁት?
አቶ አብዲ፡- በሚዲያ ብዙ ችግር አለ፡፡ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያው ለምሳሌ በአንተ ስም ብዙ ሰው መሥራት ይችላል፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያ ማንም እንደፈለገው ማድረግ ይችላል፡፡ እሱን ለመቆጣጠር ይከብዳል፡፡ ግን የመንግሥት ወይም የሆነ ሚዲያ ላይ በሁለቱም ችግር እንዳለና መስተካከል እንዳለበት ነው የተስማማነው፡፡ በወቅቱ ችግር ነበር፡፡ ያንን ገምግመን አስተካክለናል፡፡ የተሰጡ መግለጫዎች ነበሩ፡፡ ስህተት ናቸው፡፡ የሁለቱን ክልሎች ሕዝቦች ወደ ግጭት የሚወስዱ መግለጫዎች በሁለቱም ክልሎች መውጣት አልነበረባቸውም፡፡
ሪፖርተር፡- በማኅበራዊ ሚዲያ በተለይም በፌስቡክ በእርስዎ ስም ግጭትን የሚያባብሱና አብሮ የመኖር እሴትን የሚሸረሽሩ መረጃዎች ይለቀቁ ነበር፡፡ የፌስቡክ ገጹ የማን ነው?
አቶ አብዲ፡- እሱ እንኳን በጣም ያስቃል፡፡ እኔ ኋላ ላይ ግራ ቢገባኝ ከሰስኩኝ፡፡ በፌስቡክ ከሰስኩት፡፡ ሁሉም ቦታ ከስሻለሁ፡፡ የወቅቱን ሁኔታ ዓይቶ ነው በእኔ ስም የሚነግደው፡፡ ሦስት ጊዜ እንዲዘጋ አደረግኩት፡፡ ከስሼ ማለት ነው፡፡ ይዘጋል ይከፈታል፡፡ አሁንም ያስከፍቱታል፡፡ ይዘጋል አሁንም ያስከፍቱታል፡፡
ሪፖርተር፡- ለማን ነው የከሰሱት? ማንንስ ነው ሲያዘጉ የነበረው?
አቶ አብዲ፡- እኔ ለፌስኩብ ነው የከሰስኩት፡፡ በይፋዊ መንገድ የጻፈውን በራሴ በፌስቡክ ገጽ ገብቼ ይኼ ሰውዬ በእኔ ስም እየነገደ ነው ብዬ ከሰስኩኝ፡፡ በፌስቡክ ላይ ቅሬታ የምታቀርብባት ቦታ አለች፡፡ በእኔ ስም የተሳሳተ መረጃ እያቀረበ ነው ብዬ ለፌስቡክ ከስሸዋለሁ፡፡ ብዙ ጊዜ አቀረብኩኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ምሥሎችን አሳየሁ፡፡ ይኼ በራሴ ስም የተጻፈ ነው አልኩ፡፡ እኔ የማላውቀውን ነገር ብሏል ብዬ ከሰስኩት፡፡ በዚህ አጋጣሚ ፌስቡክ አግዞኛል፡፡ አሁንም ግን በሌላ መንገድ ይከፈታል፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያ ታብዳለህ፡፡ እኔም መጀመርያ ገርሞኝ ነበር፡፡ ሕዝብ ለሕዝብ የሚያጣላ ነው እየተጻፈ ያለው፡፡
ሪፖርተር፡- ከአወዳይ ወደ ሶማሌ ክልል ጫት በበቂ ሁኔታ እየገባ አይደለም ይባላል፡፡ ወደ ክልሉ ይገባ የነበረው የጫት ንግድ በአሁኑ ወቅት ምን ይመስላል?
አቶ አብዲ፡- ጫቱን በተመለከተ በእርግጥ እንዳልከው ችግሮች አሉ፡፡ የጫት ንግዱ አካባቢ ላይ በተለይ አወዳይ ላይ ባለፈው ካጋጠመው ግጭት ጋር በተያያዘ የተፈጠረ ችግር ነበር፡፡ አሁን ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ይገኛል ማለት ነው፡፡ ጫት አካባቢ እንዳልከው ችግር ነበር፡፡ ገበሬው መጎዳት የለበትም፡፡ አሁን ገበሬው እየተጎዳ ነው፡፡ ምክንያቱም ዛሬ ያመረተውን ምርት ካልሸጠ ችግር ነው የሚሆነው፡፡ ሰው ደግሞ ጫት ይፈልጋል፡፡ መግዛት ይፈልጋል፡፡ ከአገር ውስጥ ባሻገር ወደ ውጭም በሚላከው ጫት ላይም ችግር እንደነበረ ነው የሚታወቀው፡፡ አሁን ግን ንግዱ እየተከፈተ ነው፡፡ ሰላም ነው፡፡ ለምሳሌ በዚህ ሰዓት እኔ የማረጋገጥልህ የኦሮሚያ ተወላጅ ወይም የኦሮሚያ ነጋዴ ወደ ሶማሌ ክልል እየገባ ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ውስጥ የትም ቦታ እየሄደ በሰላማዊ መንገድ መንቀሳቀስ ጀምሯል፡፡ ተዘግተው የነበሩ መደብሮችም በመከፈት ላይ ያሉ እንዳሉ አረጋግጥልሀለሁ፡፡ ማንንም መጠየቅ ትችላለህ፡፡ ጫት ከኦሮሚያ ቀጥታ ወደ ሶማሌ ክልል በሰላማዊ መንገድ እየሄደ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ሰሞኑን ትምህርት ሚኒስቴር በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የሚማሩ የኦሮሚያ ክልል ተወላጆችን ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች መድቧል፡፡ በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ የሶማሌ ክልል ተማሪዎች ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እንዲማሩ አዲስ ምደባ አውጥቷል፡፡ እናንተ እዚህ ላይ ያላችሁ አቋም ምንድነው?
አቶ አብዲ፡- ይኼ ፌዴራሊዚምን የሚያበላሽ ነገር ነው፡፡ የኦሮሚያ ተማሪዎች ከጅግጅጋ የሶማሌ ክልል ተማሪዎች ከኦሮሚያ ውጪ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች መመደብን አላምንበትም፡፡ የኦሮሞ ተማሪ ጅግጅጋ የራሱ ነው፡፡ የራሱ መሬት ነው፡፡ ደግሞ አንድ አገር ነን፡፡ አንድ ላይ ነን፡፡ ኦሮሚያ ውስጥ ያለ መሬት የራሱ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ አናምንበትም፡፡ ነገር ግን ሆኗል፡፡ እኔ በግሌ አላምንበትም፡፡ የኦሮሚያ አመራርም የሚያምንበት አይመስለኝም፡፡
ሪፖርተር፡- ይኼን ለማስተካከል ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
አቶ አብዲ፡- እኔ መስተካከል አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ እኛ በበኩላችን የሚያስፈልገውን ሁሉ ለማስተካከል ዝግጁ ነን፡፡ እውነቴን ነው የምልህ እኔ የኦሮሞ ሕዝብ የሶማሌ ጠላት ነው ብዬ አልፈርጅም፡፡ ሶማሌ ደግሞ የኦሮሞ ጠላት ነው ብዬ አልፈርጅም፡፡ የሁላችንም ጠላት ድህነት ነው፡፡ የኦሮሞ ጠላት ድህነት ነው፡፡ የሶማሌ ጠላት ድህነት ነው፡፡ ስለዚህ ዋናው ጠላታችንን መዋጋት አለብን፡፡
ሪፖርተር፡- የሶማሌ ክልል በአሁኑ ወቅት ምን ይስመላል?
አቶ አብዲ፡- ክልሉን ለስድስት ዓመታት ያህል መርቻለሁ፡፡ በእርግጥ ከሌሎች ክልሎች ጋር ሲነፃፀር ብዙም ለውጥ አላሳየም፡፡ አሁን ግን ለኢኮኖሚ ልማት እየተሯሯጥን እንገኛለን፡፡ የእኛ ዋና ችግር ውኃ ነው ብለናል፡፡ ውኃ ነው የክልሉ ችግር፡፡ ውኃን በተመለከተ በከፍተኛ ሁኔታ እየሠራን እንገኛለን፡፡ ሌላው ድልድይ ነው፡፡ ድልድይ በከፍተኛ ሁኔታ እየሠራን እንገኛለን፡፡ የክልሉ ቁልፍ ችግሮች ውኃ፣ መንገድና ድልድይ ናቸው፡፡ ጤናና ትምህርትም እየተስፋፉ ናቸው፡፡ በመሠረተ ልማቶች በደንብ እየሠራን ነው፡፡ እነዚህን እየሠራን እዚህ ደግሞ ችግር ካለ ትርጉም የለውም፡፡ ከኦሮሚያ ጋር ችግር ካለ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ ልማት እያከናወንን ነው የሚለውን ሳይሆን ከኦሮሚያ ጋር ያለውን ችግር መፍታት አለብን በማለት አምናለሁ፡፡ ክልሉ ሰፊ ድንበር አለው፡፡ መንግሥት አልባ ከሆነችው ሶማሊያ በዚህ አጋጣሚ መጠቀም የሚፈልጉ አሉ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ወንድማማቾች ሲጣሉ ጠላት ደግሞ ገብቶ መጠቀም ይፈልጋል ማለት ነው፡፡