fbpx

የእነሌንጮ ለታ መምጣት ምን ይፈይድ ይሆን?

የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን መቀመጫውን በውጭ አገር ካደረገው የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር (ኦዴግ)ጋር ድርድር መጀመሩን ይፋ አድርጓል፡፡

ኦዴግም ከዋሽንግተን ዲሲ ባወጣው መግለጫ ከኢትዮጽ መንግሥት ልዑካን ቡድን ጋር ከግንቦት 3 አስከ 4 ቀን 2010 ዓ.ም እየታዩ በመጡ ለውቶች ዙሪያ ውይይት ማካሄዱን አስታውሶ እንዚህ የማሻሻያ እርምጃዎች እንዲሰፉ፣ እንዲጎለብቱና ጥልቀት እንዲኖራቸው ያለውን ፍላጎት ገልጿል፡፡ ገና ብዙ የሚቀረው ቢሆንም ኢትዮጵያ መንግሥት እየወሰደ ባለው የለውጥ እርምጃዎች ኦዴግ መበረታታቱን መግለጫው ይጠቅሳል፡፡ ኦዴግ የተጀመሩትን የማሻሻያና የለውጥ እርምጃዎች እንዲጎለብቱ ለማስቻል የሚጠበቅበትን ሚና ለመጫወት ዝግጁ መሆኑን አብስሮ ውይይቱን ለመቋጨት አንድ የኦዴግ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በቅርቡ ወደአገር ቤት እንደሚልክ አስታውቋል፡፡

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ፥ የኢፌዴሪ መንግስት የሃገሪቱን ሠላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ ያላሰለሰ ጥረትና ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኑን ጠቅሷል።

የሃገሪቱን ህገ መንግስት ተቀብለው በሰላማዊ መንገድ ከሚታገሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን በገለጸው መሰረት፥ ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሠላም ጥሪ ማስተላለፉን አስታውሷል።

በዚህም የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች መቀመጫውን ከሃገር ውጭ ካደረገውና የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር (ኦዴግ) ተብሎ ከሚጠራው ድርጅት ጋር ድርድር አድርገዋል ብሏል መግለጫው።

ግንባሩም ከመንግስት የቀረበለትን ጥሪ አክብሮ በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግ መወሰኑን መንግስት በአድናቆት ይመለከተዋል ብሏል፡፡

ከግንባሩ ጋር የተደረገው ድርድር የተሳካና ሃገራዊ መግባባት የሰፈነበት እንደነበር ያነሳው መግለጫው፥ በሰለጠነ መንገድ የሚደረግ ውይይትና ድርድርን መንግስት በሰላማዊ መንገድ ከሚታገሉ አካላት ጋር በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።

መግለጫው የግንባሩ አመራሮች በቅርብ ቀናት ውስጥ አዲስ አበባ እንደሚገቡ ጠቅሶ፥ ቀሪ ድርድሮችም አዲስ አበባ እንደሚደረጉ ይጠበቃል ብሏል።

መንግስት ወደፊትም ህገ መንግስቱን ባከበረና ሰላማዊ በሆነ መንገድ በሃገራቸው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ መሳተፍ ከሚፈልጉ አካላት ጋር ለመወያየትና ለመደራደር ዝግጁ መሆኑንም መግለጫው አንስቷል፡፡

በድርድሩ ዙሪያ የተሰጡ አስተያየቶች

የአዴግ ወደ ኢትዮጵያ መግባት ከተሰማ በኋላ በድጋፍም ሆነ በተቃውሞ የተለያዩ አስተያየቶች እየተንጸባረቁ ነው፡፡ ባለቅኔው ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ፈጠን ብለው ቁጣቸውን ከገለጹ ኢትዮጵያውያን አንዱ ናቸው፡፡ በፌስ ቡክ ገጻቸው እንዲህ ብለዋል፡፡

“የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ግንባር የሚባለው “ድርጅት” ከቀድሞው የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር ተገንጥሎ የወጣ ነው። በአመራሩ ውስጥ ያሉት ግለሰቦች ዋናዋናዎቹ ግማሽ ደርዘን ወይም ከዛ በላይ የሚቆጠሩ ሲሆኑ በቀድሞው የኦነግ አመራር ውስጥ የነበሩ ናቸው። ከእነሱም ውስጥ እንደ እነ አቶ ሌንጮ ለታ፥ዶክተሮቹ ዲማ ነገዎ እና በያን አሶባ ይገኙባቸዋል።

እነዚህ በሽምግልናቸው ዘመን የአሉ ግለሰቦች ኦነግን ወክለው ከኢህአዴግ ጋር አብረው ለአጭር ጊዜ የመንግሥት አካልና አምሳል ሆነው በኢህአዴግ እስከተባረሩ ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለስልጣናት ሆነው መቆየታቸው ይታወሳል። ከ17000 የሚበልጡ የኦነግ ጦረኞችን ኢህአዴግ ትጥቃቸውን አስፈትቶ አስሮ ደብዛቸው በጠፋበት ሁኔታ እነዚህ መሪዎች እግሬ አውጭኝ ብለው የራሳቸውን ነፍስ ብቻ ማትረፋቸውም ከቶውንም አይረሳም። በእዚህ ሁሉ ሳቢያ የኦነግ አባላት ናችሁ እየተባሉ የኦሮሞ ወጣቶች ሁሉ እየተሰቃዩ እስከአሁንም ድረስ እስር ቤታቹን እንደአጣበቡት የታወቀ ነው።

በእዚህ ላይ ደግሞ በበደኖ፣ አርሲ፣ አርባጉጉ፣ አሶሳ እና በሌሎችም ቦታዎች በግፍ ለተገደሉት አማሮች እነዚህን የቀድሞ ኦነግ መሪዎች በሀላፊነት እንጠይቃለን የሚሉ ፍትህ የሚሹ ሰዎች አሉ።

እነዚሁ ግለሰቦች ከግንቦት 7ት ጋር ግንባር ፈጥረው ወዲያ ወዲህ እየተንሸራሸሩ በኢሳትም ሬድዮ እና ቲቪ ሲገለገሉበት ከርመዋል። አሁን እንደምንሰማው ደግሞ ግንቦት ሰባትን ሸውደው ለብቻቸው በሚስጥር ከኢህአዴግ ጋራ ተስማምተው ከተባረሩ ከ20 ምናምን ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ሊገቡ ነው።

ወደ ፍሬነገሬ ልግባና አሁን እነዚህ ጥቂት ግለሰቦች የሚደራደሩበት የጦር ሰራዊት እና ከቁጥር የሚገቡ አባላት በውጭ ሀገርና ኢትዮጵያ ውስጥ ሳይኖራቸው መንግሥት እነሱን ኑ እና አብረን እንሥራ የሚላቸው በምን ሂሳብ ይሆን? ኢትዮጵያ ገብተውስ በባዶ እጃቸው ምን ተግባር ሊፈጽሙ ይችላሉ? አላማቸው አዳዲስ አባላትን ለማሰባሰብ ከሆነ የኦሮሞ ቄሮ ኦሆዴድን በደገፈበት ሰዐት እነሱ አዲስ አባለትን ምን ብለው አሳምነው ሊመለምሉ ነው? እነሱ ኢትዮጵያ ቢገቡ ስልጣን ላይ ያለው መንግሥት ምን ይጠቀማል? እውጭ ሀገር ቢቀሩስ ምን ይጎዳል?” ሲሉ ውሳኔውን ነቅፈዋል፡፡

አንዳንዶች የኦዴግ ውሳኔና ፈር ቀዳጅ ለመሆን የወሰደው እርምጃ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር መስፋት አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል የሚል ተስፋን ሰንቀዋል፡፡

sendek newspaper

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram