የኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶስየሽን ስራ አስኪያጅ አቶ የማነ ወልደ ማርያም የኮማንድ ፖስቱ አባል ነን ባሉ የታጠቁ ግለሰቦች የግድያ ሙከራ ተፈፀመባቸው

የኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ደቨሎፕመንት አሶስየሽን ስራ አስኪያጅ አቶ የማነ ወልደ ማርያም የኮማንድ ፖስቱ አባል ነን ባሉ የታጠቁ ግለሰቦች የግድያ ሙከራ እንደተፈፀመባቸው ተሰማ፡፡

አሁን የህክምና ክትትል እያደረጉ መሆኑን ሰምተናል፡፡

በአፋር የሚገኝን የጎዳና ተዳዳሪዎች ማሰልጠኛ ማዕከልን ጎብኝተው ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ ወንጀሉ አዳማ ከተማ መውጫ ላይ እንደደረሰባቸው ተነግሯል፡፡

በድርጅቱ የሚድያ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ነጋሽ በዳዳ ለሸገር እንደተናገሩ አቶ የማነ ባለፈው አርብ ከምሽቱ 4 ሰዓት አካባቢ ከአዳማ ወደ አዲስ አበባ እያሽከረከሩ እያለ የመከላከያ ሰራዊት የደንብ ልብስ የለበሱና የታጠቁ አምስት ግለሰቦች የኮማንድ ፖስቱ አባል መሆናቸውን በመግለጽ እንዲሸኟቸው ይጠይቋቸዋል፡፡

የቀረበላቸውን የትብብር ጥያቄ የተቀበሉት አቶ የማነ ታጣቂዎቹን ጭነው ማሽከርከር ይጀምራሉ፡፡ ከአዳማ ከተማ መውጫ ሲደረሱ ግን የታጠቁት ግለሰቦች አስቁመዋቸው ይደበድቧቸዋል፡፡
በኋላም በገመድ ዛፍ ላይ እንደሰቀሏቸውና ሞተዋል ብለው ሲያስቡም አንገታቸው ላይ የቋጠሩትን ገመድ በጥሰው ገደል ውስጥ ወርውረዋቸዋል ብለዋል አቶ ነጋሽ፡፡ ወንጀለኞቹ የአቶ የማነን የእጅ ስልክና ተሽከርካሪያቸውን ይዘው ተሰውረዋል፡፡

የግድያ ሙከራ የተፈፀመባቸው አቶ የማነ በአካባቢው ሃብሃብ ይሸጡ በነበሩ ወጣቶች ትብብር በአዳማ ጀነራል ሆስፒታል የህክምና ክትትል ሲያደርጉ ቆይተው አሁን ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውን ሰምተናል፡፡ በተሻለ የጤንነት ሁኔታ ላይም ይገኛሉ ተብሏል፡፡ ስለ ጉዳዩ የጠየቅነው የአዳማ ፖሊስ በበኩሉ ወንጀሉ ስለመፈፀሙ አረጋግጫለሁ፡፡

ወንጀሉን የፈፀሙትን ግለሰቦች እና ይዘው የተወሰወሩትንና ንብረትነቱ የአቶ የማነ የሆነውን ተሽከርካሪ እያፈላለግሁ ነው ብሏል፡፡

(ትዕግስት ዘሪሁን)

Share your thoughts on this post

Advertisements
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram