fbpx
AMHARIC

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲና የመከላከያ ሚኒስቴር በትብብር በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ እና የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የመረጃ ዋና መምሪያ በትብብር በሚሰሩበት ጉዳዮች ዙሪያ በትናንትናው እለት ተወያይተዋል።

በውይይታቸው ወቅትም ሁለቱ ተቋማት እንደከዚህ በፊቱ በትብብር የሚሰሩበትን ሁኔታ አጠናክረው ለመቀጠል ከስምምነት መድረሳቸውም ተገልጿል።

ተቋማቱ የመረጃ መሰብሰቢያ፣ መተንተኛ እና ማሰራጫ ስርዓቶችን በማዘመን ረገድ በጋራ ለመስራት ከመግባባት ላይ ደርሰዋል።

በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የመረጃ ዋና መምሪያ ሃላፊ ሌተናል ጀኔራል ሀሰን ኢብራሒም በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት፥ የሀገሪቷን የመረጃ ማሰባሰቢያ፣ መተንተኛ እና ማሰራጫ መንገዶችን ዘመናዊ በማድረግ በኩል በየጊዜው እያደገ የሚሄድ አቅም መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።

ሁለቱ ተቋማት ለጋራ ሀገራዊ ዓላማ የሚሰሩ በመሆኑ በአሠራር ሂደት የነበሩ ክፍተቶችንና ችግሮችን በመፍታት የራስ አቅምን አጎልብቶ የሃገሪቱን የመከላከያ ሠራዊት የመረጃ ሥርዓት ዘመናዊነት ይበልጥ በማጠናከር በኩል በጋራ መስራታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የኢንፎርሜሽ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው፥ ኤጀንሲው በአዋጅ የተሰጠውን ተግባር እና ሃላፊነት መሰረት አድርጎ በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ሥር ካሉ ልዩ ልዩ ተቋማትና ከሌሎች ባለድርሻ ተቋማት ጋር በጋራ ይሰራል ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በፕሮጀክት አስተዳደር ስርዓት እና የፕሮጀክት አፈፃፀምን አስመልክቶ በሚፈለገው ደረጃ ግንኙነት ያለመደረጉ የፈጠረውን ክፍተት በመቅረፍ እና በመግባባት እንደሚሰራም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

አቶ ተመስገን አያያዘውም፥ የፕሮጀክት አስተዳደርን ውጤታማ ለማድረግ እንዲቻል ኤጀንሲው የሚወስዳቸው ፕሮጄክቶች በአንድ የፕሮጄክት አስተዳደር ሥርዓት እንደሚመሩ መግለጻቸውን ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram