fbpx

የኢንተርኔት አገልግሎት በግል ኩባንያዎች እንዲሰጥ የተጀመረው ስራ የፖሊሲ ለውጥ አይደለም- ኢትዮ ቴሌኮም

የኢንተርኔት አገልግሎት በግል ኩባንያዎች እንዲሰጥ የተጀመረው ስራ የፖሊሲ ለውጥ አይደለም አለ ኢትዮ ቴሌኮም።

የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አንዱአለም አድማሴ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ አሁን ላይ ስምንት ኩባንያዎች የኢንተርኔት አገልግሎትን ከኢትዮ ቴሌኮም ገዝተው ለደንበኞች ለማቅረብ ውል አስረዋል።

ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ ወዴት እየሄደ ነው የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎች ተነስተዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አንዱአለም አድማሴ፥ እንደዚህ አይነት ኩባንያዎች የሚሰሩት ስራ በቴሌኮም ዘርፍ እሴት የሚጨምር ስራ ነው ብለዋል።

የዚህኛው ተጠናጠል ስያሜም “ቨርቹዋል ኢንተርኔት ሰርቪስ ፕሮቫይደር የሚል ነው፤ የዛሬ አራት አመት የታሰበ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

ዶክተር አንዱአለም፥ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ከዚህ ስምምነት ደርሶ የሚሰራ ኩባንያ በኩባንያውና በደንበኞች መካከል ሆነው ኢንተርኔትን ከኢትዮ ቴሌ ኮም ገዝተው ወደ መጨረሻ ተጠቃሚ የማድረስ ስራን የሚሰሩ እንጂ የየትኛውም መሰረተ ልማት ባለቤት ሆነው አይደለም ይላሉ።

የኢንተርኔት አገልገሎቱን የሚሰጡ ተቋማትም ከኢትዮ ቴሌኮም የገዙትን አገልግሎት ለሰበሰቧቸው ደንበኞች ሲሸጡና አግልገሎትን ለመቆጣጠርም ሆነ ገቢ ለመሰብሰብ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የሚናበብ ስርአትን እንደሚዘረጉ ገልፀዋል።

ዋና ስራ አስፈጻሚው፥ እንዲህ አይነት ኩባንያዎች ገበያ ውስጥ ሲገቡም በተለይ ለድርጅቶች መልካም መሆኑን ያነሳሉ።

ኢትዮ ቴሌኮም ለህንጻዎች አገልገሎቱን ሲሰጥ ዝርጋታ የሚያደርገው ህንጻው ድረስ ብቻ መሆኑን ተናግረው እንዲህ አይነት ኩባንያዎች ግን ሙሉ አገልገሎት በመስጠት የተሻለ ስራን የመስራት አቅምን ይፈጥራሉ ነው ያሉት።

በግል የኢንተርኔት አገልግሎቱን ከሚያቀርቡ ኩባንያዎች ድርጅቶች ብቻ ሳይሆኑ ግለሰቦችም ደንበኛ መሆን እንደሚችሉም ዶክተር አንዱአለም አንስተዋል።

የግል ኩባንያዎች ከኢትዮ ቴሌኮም ግዥ ፈጽመው መልሰው አገልግሎትን ሲሸጡ ማትረፍ ስለሚኖርባቸው ቀጥተኛ ደንበኞችና በግል ኩባንያዎቹ ተጠቃሚዎች መካከል ልዩነት አይፈጥርም ወይ የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ዶክተር አንዷለም።

ኩባንያዎቹ ኢንተርኔቱን በጥቅል በአነስተኛ ዋጋ ገዝተው በችርቻሮ መልክ ለደንበኞቻቸው ስለሚያቀርቡ ዋጋ ላይ የሚያመጣው ልዩነት የለውም፤ ይልቁንም ተወዳዳሪ ሊያደርጋቸው የችላል ብለዋል።

ስራው ለኢትዮጵያውያንም ይሁን ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት ነው፤ ይሁን እንጂ መጀመሪያ ላይ በኢትዮጵያውያን ደረጃ እንይ በሚል የውጭ ኩባንያዎች በስራው ውስጥ እንዳይካተቱ መደረጉንም ዶክተር አንዷለም ተናግረዋል።

የኢንተርኔት አገልግሎትን በዚህ ደረጃ ለመስጠት ሲታሰብ ምናልባት የቴሌኮም ዘርፍን ወደ ፕራይቬታይዜሽን ለማስገባት እንደ መንገድ ጠቋሚ ነው የተባለውንም ዶክተር አንዷለም ስህተት ነው ብለዋል።

አሰራሩ በህግ አግባብ የሚሰራ መሆኑን እና ተቋሙን ወደ ፕራይቬታይዜሽን ለማስገባት ያለመ እንዳልሆነ ነው የገለፁት።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አንዱአለም አያይዘውም፥ አዲሱ አሰራር ከፖሊሲ ለውጥ ጋር የሚገናኝ ነገር እንደሌለውም ተናግረዋል።

አሁን ላይ አሁን ላይ ጂቱጂ ፤ ዌብስፕሪክስና ቪቫቴክን ጨምሮ ስምንት ኩባንያዎች የኢንተርኔት አገልግሎትን ለመስጠት ከኢትዮቴሌኮም ጋር ውል አስረዋል።

ከነዚህ ውስጥ ዌብስፕሪክስ የተባለው ኩባንያ 30 የሚሆኑ ደንበኞችን መዝግቦ አገልግሎቱን እየሰጠ ይገኛል።

በካሳዬ ወልዴ – ኤፍ.ቢ.ሲ

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram