fbpx

የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነትን በዓለም አቀፍ ሕግ

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለኤርትራ የሰላም ጥሪ ካቀረቡበት ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ የኤርትራ እና የኢትዮጵያ መሪዎች ግንኙነት በፍጥነት እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ግንኙነቱ ለብዙዎች አስደሳች ቢሆንም፤ የሂደቱ ፍጥነት አስግቷል፡፡ ቀጣይ ግንኙነት ዓለም አቀፍ ሕግን በጥብቅ መከተል የሚገባው መሆን እንዳለበት የፖለቲካ ምሁራኑ ጠቁመዋል፡፡

በአገር ሰላምና ደህንነት ላይ የሦስተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እየሰሩ ያሉት አቶ አበበ ዓይነቴ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት መታየት ያለበት በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት እንደሚዳኙ ሁለት አገሮች ነው፡፡ እያንዳንዱ ነገር በጥልቀት በዝርዝር መታየት ያለበት ሲሆን፤ በፖለቲካ ውሳኔ ብቻ ሳይሆን ሳይንሳዊ የሆነ የባለሙያ ዝርዝር ጥናት ያስፈልጋቸዋል፡፡ የሁለቱ አገራት ግንኙነት በሕግ የማይመራ ከሆነ ከመጥቀም ይልቅ ይጎዳል፡፡

የአሁኑ የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት ብዙዎችን አስደስቷል፡፡ አሁን የተደረሰበት ደረጃ አጠቃላይ ሂደቱ ተጨርሶ፤ ድርድር ተደርጎ ችግሩ ከተፈታ በኋላ ሊደረስበት የሚገባ ደረጃ ነው፡፡ እየተመጣ ያለው ከታች ወደ ላይ ነው፡፡ በእርግጥ መጀመሪያ ሰላማዊ ግንኙነቱ መቅደሙ ውይይቱንም ሆነ ድርድሩን ሰላማዊ ለማድረግ የሚጠቅም በመሆኑ መልካም ነው ካሉ በኋላ፤ ሆኖም ግንኙነቱ በጥንቃቄ እና በቅደም ተከተል መቃኘት እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡

የሁለቱ አገራት ጉዳይ የድንበርና የመሬት ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ሁለቱም ሀገሮች መሬት በመስጠትና በመቀበል ብቻ ችግሩን በዘላቂነት መፍታት አይችሉም፡፡ በዚህ መንገድ ብቻ ችግሮች እንደማይፈጠሩ ዋስትና የለም፡፡ ከመሬትም በላይ ብዙ ያልተነገሩ ነገሮች አሉ፡፡ ለሁለቱም አገራት በመንግሥታቱ መካከል ሊኖር የሚገባው ግንኙነት ሰላማዊ መሆኑ በጣም አስፈላጊ ቢሆንም፤ ዋስትናው ግን እያንዳንዱ ነገር በዝርዝር መታየቱ እና በሕግ መመራቱ ነው ብለዋል፡፡

በ1984 ዓ.ም ኤርትራ ስትገነጠል የሁለቱ አገራት ኮሚሽን ተቋቁሞ ጥናት ተጀምሮ እንደነበር አስታውሰው፣ የዜግነት፣ የድንበር፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የፖለቲካ እና ሌሎችም የሚያገናኙ ጉዳዮች አሉ፡፡ የእነዚህ ጉዳዮች ጥናት በወቅቱ በጅምር ቀርቷል፡፡ ሆኖም ሁለቱ ድንበር የለሽ ሕዝቦች ናቸው፡፡ እንደ አንድ አገር የነበሩ በመሆኑ እያንዳንዷ ነገር ተለቅማ በባለሞያና በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት መፍትሄ ተሰጥቶ የማያዳግም ሥራ መሰራት አለበት ብለዋል፡፡

የዓለም አቀፍ ግንኙነትን የተማሩት ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌውም የአቶ አበበን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ ግንኙነቱ ዓለም አቀፍ ሕግን ተመስርቶ፤ በሰከነ መልኩ ግልፅነትን ተከትሎ መሄድ አለበት፡፡ መጀመሪያ የሁለቱን ሕዝብ ግንኙነቶች ወደ ሰላማዊ መንገድ መቀየር ትክክል ነው፡፡ የኢኮኖሚ ግንኙነቱ በምን መልክ መሆን አለበት? የአየርና የባህር ግንኙነት እንዴት ይሁን? የአልጀርሱ ስምምነት እንዴት ይፈታ? ቀድሞም በፈንጂ በታጠረ ቦታ ላይ ወደ ኢትዮጵያ ይሰደድ የነበረው ኤርትራዊ ድንበር ሲከፈት ሊፈጠር የሚችለው ምንድን ነው? የስደተኞች ጉዳይስ እንዴት ይታያል? እነዚህ ሁሉ በቅደም ተከተል መታየት እንዳለባቸው አመልክተው፤ ለሚቀጥለው ትውልድ የምንተወው ነገር መኖር የለበትም ብለዋል፡፡

ያለን የተለያየ ገንዘብ ነው፤ የምንሆነው እንደማንኛውም ሁለት አገር ነው ወይስ የተለየ ነገር ሊኖር ይችላል? በዚህ ላይም መታሰብ አለበት፡፡ ከባድመ ጦርነት በፊት የነበርንበትን እና ለጦርነቱ የዳረገውን ሁኔታ ማስታወስ ይገባል፡፡ እነዚህን ሁሉ ከማሰብ ባለፈ ጥናትና ድርድር ያስፈልጋቸዋል፡፡ በሂደት ቀስ እያለ ከሕዝብ ግንኙነት ተነስቶ ወደ ኢኮኖሚ መቀናጀት የሚሄድበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ይህ ሲሆን ወደ ፖለቲካዊ ውህደትም መድረስ አያዳግትም፡፡ ዋናው ነገር ጥሩ ስሜት እየተፈጠረ ነው፡፡ በመሪዎች የተፈጠረው ስሜት ወደ ሕዝብ ማውረድ እና የሕዝብ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ጥርጣሬና ስጋት ያለው ሕዝብስ አለ ወይ? የሚለውን ማየት፣ መድረክ እየፈጠሩ ማወያየት እንደሚገባም ነው አቶ ልደቱ የተናገሩት፡፡

የመጀመሪያ ዲግሪያቸው የመመረቂያ ጽሑፍ በኢትዮጵያና በኤርትራ ግጭት ላይ የሰሩ ሲሆን፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በብሔራዊ ደህንነት ላይ ሰርተዋል አቶ መረሳ ፀሐዬ፤ አሁን በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር ናቸው፡፡ አቶ መረሳ እንደሚገልፁት፤ በእርግጥ ኢትዮጵያ ለኤርትራ በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ አቅርባለች፡፡ ሆኖም አሁን በኢትዮጵያ የተፈጠረው ለውጥ ከፍተኛ ግፊት በመፍጠሩ ኤርትራም ጥሪውን ተቀብላለች፡፡ ጥሪውን የተቀበለችው የአውሮፓ ጣልቃ ገብነት፣ የኢትዮጵያ ጥሪ ተደጋጋሚነት እና የኤርትራ ሕዝብም ከዚህ በላይ መቀጠል ስለማይችል ግፊቱን ለመቋቋም ስለማትችል ነው፡፡

ብቻ የግንኙነቱ መነሻ ምንም ሆነ ምን ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለኤርትራም በሚጠቅም መልኩ መሆን አለበት፡፡ የዜግነት፣ የገንዘብ፣ የኢኮኖሚ ስምምነት ጥያቄ አለ፡፡ ይህን በሚገባ መመለስ ያስፈልጋል፡፡ የዜጎች እንቅስቃሴ፣ የንግድ ግንኙነት፣ የወደብ ጉዳይ ሁሉንም የሚጠቅም ወደ ሰላማዊ ግንኙነት በሚለውጥ መልኩ ማካሄድ የግድ ነው፡፡ በዋናነት ወንድም ሕዝቦች ነን በሚል ከሕግና ከብሔራዊ ጥቅም፣ ከፖሊሲ ውጪ የሚሰራ ነገር እንዳይኖር መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ህወሓትና ህግሓኤ አብረው ሲታገሉ ቆይተው እርስ በእርስ ሲጣሉ የተዋጋው አገርና ሕዝብ ነው፡፡ ከእንግዲህ በኋላ ከኤርትራ ጋር የሚኖረን ግንኙነት በግልፅ በብሔራዊ ጥቅም መርህ መሠረት መሆን አለበት፡፡ ወደብ ይሰጠናል፣ በኪራይ ነው ወይስ በነፃ የሚለው በግልፅ መቀመጥ አለበት፡፡ አሁን ያለው መንግሥት ላይኖር ይችላል፡፡ የግንኙነት መንገዱን የሚቀጥለው መንግሥት የሚቀይረው መሆን የለበትም፡፡ ከሱዳንም፣ ከኬንያም፣ ከሶማሊያም ጋር ወንድም ነን፡፡ ግንኙነታን ግልፅ የሆነ ብሔራዊ ጥቅምን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ በኤርትራም ተመሳሳይ መሆን አለበት፡፡ ሕጋዊ ከሆነ ማንም ማንንም አይጎዳም፡፡ ሂደቱ ለፖለቲካ ትርፍ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ግንኙነቱ ከኤርትራ ሕዝብ ጋር እንጂ ከግለሰብ ጋር መሆን የለበትም ብለዋል፡፡

በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ኢትዮጵያን የወደብ ባለቤት ለማድረግ ከኤርትራ ጋር ለማስተሳሰር በተደረገው ትግል በኤርትራ ሕዝብ ተወካዮች ፍላጎትና በተባበሩት መንግሥታት ውሳኔ በ1952 ዓ.ም በፌዴሬሽን ተቀላቅላለች፡፡ በሂደትም ፌዴሬሽኑ ፈርሶ ኤርትራ የኢትዮጵያ ሙሉ አካል ስትሆን ግን የመገንጠል ጥያቄን አስነስቶ ህግሓኤ እና ጀብሃ ወደ ትጥቅ ትግል በመግባታቸው ብዙ ዋጋ አስከፍሏል፡፡
ኢትዮጵያና ኤርትራ በሪፈረንደም ከተለያዩ በኋላ ሊኖር የሚገባው ግንኙነት እንደሁለት አገር በትክክል በዓለም አቀፍ መርህ መመራት ቢኖርበትም ያ አልሆነም፡፡ መለያየቱም ሆነ ከተለያዩ በኋላ ሁለቱ አገሮች አንዱ ከሌላው ጋር ሊኖር የሚገባው ጥቅም፣ ዝርዝር ነገሮች አለመደረጋቸው የባድመን ጦርነት አስከትሏል፡፡ ብዙ ዋጋ አስከፈሏል፡፡ ለ20 ዓመታትም ሰላም አልባ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

ስለዚህ ካለፉት ሁለት ታሪካዊ ስህተቶች በመማር የሁለቱን አገራት ግንኙነት በዓለም አቀፍ ሁለት አገሮች በሚኖራቸው የዓለም አቀፍ ግንኙነት ሕግ መሠረት መቀጠል አለበት፡፡ ሕግን ተከትሎ ግንኙነቱን ማጠናከር ካልተቻለ ደግሞ እንደገና ሦስተኛ ስህተት መፍጠር ይሆናል፡፡

ዜና ትንታኔ
ምህረት ሞገስ – የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram