fbpx

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሶች የዕርቀ ሰላም መርሃ ግብር ነገ በሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሶች የዕርቀ ሰላም መርሃ ግብር ነገው በሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል።

በነገው እለት ከቀኑ 9 ሰዓት ጀምሮ በሚሊኒየም አዳራሽ የሚካሄደው የእርቀ ሰላም መርሃ ግብር በአሜሪካ ከተካሄደው ቀጥሎ የሚካሄድ ሁለተኛው መሆኑም ታውቋል።

በእርቀ ሰላም መርሃ ግብሩ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጨምሮ የሀይማኖት መሪዎች እና የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች እንደሚታደሙበትም ተገልጿል።

በጥቅሉ ሁለተኛው የዕርቀ ሰላም መርሃ ግብር ላይ ከ30 ሺህ በላይ የእምነቱ ተከታዮች እንደሚገኙበትም ይጠበቃል።

በዛሬው እለትም በሁለቱ ሲኖዶች መካከል የተፈጠረውን እርቀ ሰላም ተከትሎ ሁለቱ ሲኖዶሶች በይፋ የአንድነትና ትውወቅ ስነ ስርዓት አካሂደዋል።

የአንድነትና ትውወቅ ስነ ስርዓቱ ላይም ብፁዓን አባቶች በጋራ ፎቶ የመነሳት ስነ ስርዓት አካሂደዋል።

ባለፉት 26 ዓመታት ለሁለት ተከፍለው የሀገር ቤትና የውጭ ሲኖዶስ እየተባሉ ሲጠሩ የነበሩት ሁለቱ ሲኖዶሶች ቃለ ውግዘታቸውን አንስተው ሰሞኑን ወደ ዕርቅ መምጣታቸው ይታወሳል።

ዕርቀ ሰላሙን ተከትሎ አራተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ እና ብፁአን አባቶች ባሳለፍነው ረቡዕ አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወሳል።

ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጀምሮ እስከ መንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ድረስ የቤተ ክርስቲያኗን ቀኖና በጠበቀ መልኩ የአቀባበል ስነ ስርዓት ተከናውኗል።

የሀገር ውስጡ ቅዱስ ሲኖዶስ በውጭ ሲኖዶስ ላይ አሳልፏቸው የነበሩ የ1984፣ 1985 እና 1999 ዓመተ ምህረት ውግዘቶችን ማንሳቱ የሚታወስ ነው።

በተመሳሳይ በውጭ ሀገር የሚገኘው ሲኖዶስ ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥ በሚገኘው ሲኖዶስ ላይ አሳልፏቸው የነበሩ ቃለ ውግዘቶችን ባለፈው ሳምንት ማንሳቱ ይታወቃል።

ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በአንድ የቅዱስ ሲኖዶስ አመራር እንድትመራ መወሰኑም ይታወሳል።

በስምምነቱ መሰረትም ሁለቱ ቅዱሳን ፓትርያርኮች በሕይወት እስካሉ ድረስ ቤተ ክርስቲያቲያኗን በእኩልነት የአባትነት ክብራቸውን ጠብቃ እንደምትይዝ ተነግሯል።

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram