fbpx

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኤቲኤም ባለመሥራቱ ደንበኞች መማረራቸውን ተናገሩ

ታምሩ ጽጌ – ሪፖርተር

‹‹አዳዲስ አገልግሎቶችን ለመጨመር የሲስተም ለውጥ እየተደረገ ነው››

 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አውቶማቲክ የገንዘብ መክፈያ ማሽን (ኤቲኤም) ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ባለመሥራቱ፣ ደንበኞች መማረራቸውን ተናገሩ፡፡ ባንኩ በበኩሉ የተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱና አንዳንድ አገልግሎቶችን መጨመር በማስፈለጉ፣ ሲስተሙን ለማሻሻል እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

 

ባንኩ ከሐምሌ 2 ቀን  2010 ዓ.ም. ጀምሮ ሲስተሙ እንደሚሠራ ቢገልጽም፣ የሚስጥር ቁልፍ አስገብተው ሲጨርሱ ምላሽ አይሰጥም፡፡ በማሽኑ አጠገብ ያሉት የጥበቃ ሠራተኞች በመሆናቸው መሥራት አለመሥራቱን ሲጠይቋቸው የባንኩን ሠራተኞች ጠይቁ እንደሚሏቸው፣ ሠራተኞቹን ሲጠይቁም በሥራ ላይ በመሆናቸው ለመተባበር ካለመቻላቸውም በተጨማሪ፣ ማሽኑ ለምን አገልግሎት መስጠት እንደማይችል መረጃ እንደሌላቸው እንደሚናገሩ ደንበኞች በምሬት ገልጸዋል፡፡

 

አቶ ገብረ መድኅን ሥዩምና ወጣት ፍሰሐ በቀለ የኤቲኤም ተጠቃሚዎች መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ባለፈው ሳምንት ግን በሒሳብ ደብተርም ሆነ በኤቲኤም ካርድ ገንዘብ ለማውጣት በጣም መቸገራቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ አራት ኪሎ፣ ለገሐር፣ የረር፣ ቦሌና በተለያዩ ሥፍራዎች የሚገኙ ገንዘብ መክፈያ ማሽኖችን  ቢሞክሩም እንደማይሠሩ አረጋግጠው፣ በደብተር ለማውጣትም ወረፋው ጊዜ እንደፈጀባቸው አስረድተዋል፡፡ ሲስተም እየተቀየረ መሆኑን ከአንዳንድ የባንክ ሠራተኞች ከመስማታቸው ውጪ፣ ምንም ዓይነት መረጃ ማግኘት እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡

 

አውቶማቲክ መክፈያ ማሽኑን የሚጠቀሙ ደንበኞች መቸገራቸውን ገልጸው፣ አንድ ዘመናዊ አሠራር ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ ማሻሻል ቢፈለግ እንኳን፣ የተወሰነውን ቀድሞ በማጠናቀቅ ለሕዝብ ይፋ አድርጎ ሌላውን በመተካት መሥራት ሲቻል፣ ሁሉንም በአንድ ጊዜ ለመለወጥ ውሳኔ ላይ መድረስ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚበልጥም ጠቁመዋል፡፡

 

‹ደንበኛ ንጉሥ ነው› የሚለው አባባል በተለይ ለቢዝነስ ተወዳዳሪ ኩባንያ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የገለጹት ደንበኞቹ፣ ሌላው ቢቀር አውቶማቲክ የገንዘብ መክፈያ ማሽኑ የማይሠራባቸው ቀናትንና ከመቼ ጀምሮ እንደሚሠራ መግለጽ ተገቢ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ባንኩ ያንን ባለማድረጉም ቅሬታ እንደተሰማቸውም አክለዋል፡፡

 

አውቶማቲክ መክፈያ ማሽኑ ለምን አገልግሎት መስጠት እንዳቆመ ማብራሪያ እንዲሰጡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ በልሁ ታከለ፣ ሲስተም በመቀየር ላይ ነው ብለዋል፡፡ ሲስተሙን መቀየር ያስፈለገውም የደንበኞች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ነው ብለው፣ በቀን ያለው እንቅስቃሴ (Transaction) እስከ 400 ሺሕ በመድረሱ ስዊቹ ማስተናገድ አልቻለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

 

ጫና ስለበዛ ቀደም ብሎ የነበረው የሚስጥር ቁልፍ ከተሰጠ በኋላ በቀጥታ አገልግሎት ይሰጥ የነበረው እንዲቀየር ተደርጓል ብለዋል፡፡ ሚስጥር ቁልፉ ከገባ በኋላ ‹ኢንተር› የሚለውን በመንካት ነው አገልግሎቱ ማግኘት የሚቻለው ብለው፣ ይኼ የሆነው ደግሞ አራት ዲጂት የነበረውን ሚስጥር ቁልፍ ከዚያም በላይ መጠቀም እንዲቻል ለማድረግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የኤቲኤም ካርድ ማሽኑ ውስጥ ሲገባ ተንቀሳቃሽና ሴቪንግ የሚል አማራጭ መቀመጡን፣ ደንበኛው ደግሞ እንደ ፍላጎቱ እንዲጠቀም ለማድረግ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ባንኩ ከ1,600 በላይ የኤቲኤም ማሽኖች እንዳሉት ጠቁመው፣ 1,000 ያህሉ መሥራታቸውንና ቀሪዎቹም በአጭር ቀናት ተጠናቀው አገልግሎት እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram