fbpx
AMHARIC

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር ብዙ ይጠብቃል!

ኢትዮጵያ በታሪኳ በውስጥ ችግር ምክንያት አጣብቂኝ ውስጥ ከገባችባቸው ጊዜያት መካከል እንዳሁኑ የከበደ የለም፡፡ ላለፉት ሦስት ዓመታት ያህል ሰላምና መረጋጋት ደፍርሶ የበርካቶች ሕይወት ከማለፉም በላይ፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ በተለያዩ ግጭቶች ሳቢያ ተፈናቅለዋል፡፡ የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳት የደረሰባቸውም በርካቶች ናቸው፡፡ መጠኑ የማይታወቅ የአገር ሀብት ወድሟል፡፡ በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ውስጥ በተፈጠረ አለመግባባት ሳቢያም አገር ቋፍ ላይ ትገኛለች፡፡ እነዚህ ተከታታይ ሁነቶች ባጋጠሙበት አሳሳቢ ጊዜ ላይ ነው የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በፈቃዳቸው ከሥልጣን ለመሰናበት ጥያቄ ያቀረቡት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በአገሪቱ አርዓያነት ያለው ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር እንዲኖርና እሳቸውም ለተፈጠረው ችግር የመፍትሔ አካል ለመሆን መወሰናቸው ያስመሠግናቸዋል፡፡ ላለፉት ስድስት ዓመታት ያህል በተቻላቸው መጠን ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምሥጋና በማቅረብ በክብር ማሰናበት ተገቢ ነው፡፡ የኢትዮጵያዊነት መገለጫም መሆን ይኖርበታል፡፡ አገሩን የሚወድ ቅን ዜጋም ይህንን አይስተውም፡፡ እሳቸውን የሚተካው ጠቅላይ ሚኒስትርም በዚህ የፈተና ጊዜ ብዙ የሚጠበቅበት በመሆኑ፣ መሠረታዊ የሚባሉ ጉዳዮችን አንስቶ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡

ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር የሚጠብቀው ኃላፊነት እጅግ በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ከፍተኛ ድጋፍ ያስፈልገዋል፡፡ የሚሰጠው ኃላፊነት ትከሻ የሚያጎብጥ ብቻ ሳይሆን፣ በጣም አታካች መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ ያለፉት ሦስት ዓመታት ችግሮች ይዘዋቸው የመጡ በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ የአገሪቱ ሰላምና ፀጥታ በመደፍረሱ ምክንያት ለሁለተኛ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል፡፡ አንፃራዊውን ሰላም ወደነበረበት ለመመለስ አሁንም ከፍተኛ የሆነ ፈተና አለ፡፡ ወጣቱ ትውልድ በተደጋጋሚ እያነሳቸው ላሉ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ አሳማኝ ምላሽ ለመስጠት እንቅልፍ የሚያሳጣ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ይጠብቃል፡፡ የወጣቱን የሥራ፣ የፍትሐዊ ሀብት ክፍፍል፣ የዴሞክራሲ፣ ወዘተ. ጥያቄዎች ለመመለስ ደግሞ ከተስፋ ቃል በላይ የሚፈትን ተግባር ይኖራል፡፡ በዚህ ላይ መጪው አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒነት ያለው እንዲሆን ምኅዳሩን የማመቻቸት ኃላፊነት ይጠብቃል፡፡ ይህ ግን በአንድ ሰው ትከሻ ላይ ብቻ የሚወድቅ አደራ አይሆንም፡፡ ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር የተመሠከረላቸውና ብቃታቸው ጥያቄ የማይነሳበት ሰዎችን በካቢኔው ማሰባሰብ አለበት እንጂ፣ እንደ ከዚህ ቀደሙ በኮታ ሹመት የትም መድረስ አይቻልም፡፡ የሕዝብን ጥያቄ ከሥር መሠረቱ መፍታት የሚቻለው ብቃት ባላቸው ተሿሚዎች ነው፡፡ አለበለዚያ ‹‹ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም›› እንደሚባለው፣ መቅኖ ቢስ ሆኖ መቅረት ያመጣል፡፡ ከኮታ ወደ ብቃት ሽግግር ማድረግ የሚበጀው ለአገር ነው፡፡

በአሁኗ ኢትዮጵያ የእኛነት ስሜት እየጠፋ የአገር አንድነት ለአደጋ ተዳርጓል፡፡ ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው ከማንነታቸው በላይ ቅድሚያ የሚሰጡት ለአገራቸው ነው፡፡ አሁን ግን ይህ የአገር አንድነት እየተጎዳና ኢትዮጵያዊነት የሚባለው ትልቁ ምሥል እየተጎሳቆለ ነው፡፡ አገር ከአካባቢ ማንነት በታች እየተደረገች የደረሰው አደጋ ምን ያህል አጥፊ መሆኑን ምልክቶቹን በሚገባ ማየት ተችሏል፡፡ በዚህ ጊዜ የእኛነት ስሜት ለዲስኩር ወይም ለታይታ ሳይሆን፣ ሕዝብ የአገሩ ባለቤትነት እንዲሰማው መደረግ አለበት፡፡ ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትርና አስተዳደሩ የአገር አንድነት ሊፈረካከስ መቃረቡን ግንዛቤ በመያዝ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር በእኩልነት የማስተዳደር ታሪካዊ ኃላፊነት አለበት፡፡ የኢሕአዴግ ትውልድ የሆነው ወጣት የአገር ፍቅር ስሜቱ መገንባት አለበት፡፡ ለአገር አንድነት አሳቢ እንዲሆን ደግሞ ታላቁ የኢትዮጵያዊነት ምሥል አዕምሮው ውስጥ መታተም ይኖርበታል፡፡ ይህንን ለማድረግ ለብሔራዊ መግባባት የሚረዱ ገንቢ ዕርምጃዎች ላይ ማተኮር ተገቢ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ሥራን መጀመር ለአገሪቱም ሆነ ለመላው ሕዝቧ ጠቃሚ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ለገባችበት ቀውስ ዋነኛ ናቸው ከሚባሉ ጉዳዮች መካከል አንዱ የዴሞክራሲ ዕጦት ነው፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በሕግ ዋስትና ቢያገኝም፣ ይህ መሠረታዊ መብት ባለመከበሩ ብቻ ብሶቶች እንዲጠራቀሙ ምክንያት ሆኗል፡፡ አገሪቱም በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ በፀረ ዴሞክራሲያዊነትና በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ገጽታዋ ተበላሽቷል፡፡ ላለፉት ሦስት ዓመታት ያህል በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የፈነዱ ተቃውሞዎች የዚህ እውነታ ማሳያ ናቸው፡፡ ሰላማዊ የሐሳብ ነፃነትና የፖለቲካ እንቅስቃሴ መፈናፈኛ በማጣቱ፣ ዜጎች ተገፍተው አደባባይ ለተቃውሞ እንዲወጡ ምክንያት ሆኗል፡፡ በዚህም ሳቢያ ግጭቶች እየተቀሰቀሱ በርካታ ንፁኃን ሰለባ ሆነዋል፡፡ በሕግ ዋስትና ያገኙ መሠረታዊ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች ተግባራዊ መሆን ባልቻሉበት አገር፣ ለተቃውሞ የሚወጡ ሰዎች የሚጠብቃቸው ምን እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ይህም አገሪቱን ከቀውስ ወደ ቀውስ እያሸጋገረ ቋፍ ውስጥ ከቷታል፡፡ ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትርና አስተዳደሩ  ይኼንን ጉዳይ የተልኮው ዋነኛ አካል ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ የተዘጋጋው የፖለቲካ ምኅዳር ተከፋፍቶ ሰላማዊው የፖለቲካ ፉክክር ነፍስ እንዲዘራ ማድረግ አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ህዳሴ ዕውን መሆን የሚጀምረው ወደ ሥልጡን ዴሞክራሲያዊ ጎዳና መሸጋገር ሲቻል ነው፡፡ የሕዝቡም ፍላጎት ይኼ ነው፡፡

ከፖለቲካው ቀጥሎ አገሪቱ ላይ የተጋረጠው አንዱ መሠረታዊ ችግር የኢኮኖሚው ጉዳይ ነው፡፡ ንግድና ኢንቨስትመንትን የሚጎዱ ነውጦች ከፍተኛ ሥጋት ደቅነዋል፡፡ በብዙ ሥፍራዎች የሚታዩ መቀዛቀዞች ባሉበት የሚቀጥሉ ከሆነ ቀውስ ይፈጥራሉ፡፡ በተለይ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ረሃብ በተፈጠረበት በዚህ አሳሳቢ ጊዜ፣ ከምንም ነገር በላይ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ አለመቻል ፈተናውን ያከብደዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ይዘው የሚመጡ ኢንቨስተሮች በብዛት ያስፈልጋሉ፡፡ አምርተው ኤክስፖርት በማድረግ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ኢንቨስተሮችን በማሳመን ወደ ኢትዮጵያ ለመሳብ የሚቻለው፣ ሰላምና ፀጥታውን አስተማማኝ ከማድረግ ጎን ለጎን ለኢንቨስትመንታቸው መተማመኛ በመፍጠር ጭምር ነው፡፡ የውጭ ኢንቨስተሮችን በብዛት ማግኘት የሚቻለው መንግሥት በራስ መተማመናቸውን ሲጨምርላቸው ነው፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ አሁን እየታየበት ያለው መቀዛቀዝና መዳከም እንዲገታና የበለጠ ቀውስ እንዳይፈጠር፣ ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትርና አስተዳደሩ በቁርጠኝነትና በኃላፊነት ስሜት ለዚህ ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡  የኢኮኖሚው ችግር ውስጥ መግባት ከፖለቲካ ያልተናነሰ ቀውስ እንደሚያመጣ በኃላፊነት ስሜት ግንዛቤ ሊያዝበት ያስፈልጋል፡፡

ሁሌም እንደምንለው ከአገር በላይ ምንም ነገር የለም፡፡ መላው ሕዝብም ትልቁ ትኩረቱ አገሩ ናት፡፡ በፖለቲካው ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳትፎ የሚያደርጉ ወገኖች ከምንም በፊት ለአገር ቅድሚያ ይስጡ፡፡ ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትርም ሆነ የሚመሠርተው አስተዳደር ቅድሚያ ለአገር እንዲሰጥ ዕገዛ ይደረግለት፡፡ ከቡድንና ከጎራ አስተሳሰብ በመላቀቅ ለትልቁ ኢትዮጵያዊነት ምሥል ማሰብ ይገባል፡፡ ይህ ኩሩ፣ ጨዋና አስተዋይ ሕዝብ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልግፅና እንጂ የሚያስፈልገው፣ በሥልጣን ሽኩቻ ምክንያት ለቀውስ መዳረግ የለበትም፡፡ ኢትዮጵያ በታሪኳ በርካታ ፈተናዎችን አልፋለች፡፡ በክፉም ሆነ በደግ ጊዜያት ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ውለታ የፈጸሙ ባለታሪኮችን በማሰብ፣ የታሪክም ሆነ የትውልድ ተጠያቂ አለመሆን ይመረጣል፡፡ አሁን ኢትዮጵያውያንን አንድ በማድረግ ለጋራ ዓላማ ማሠለፍ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያዊነት እየጎመራና እያበበ እንዲሄድ ማንኛውንም መስዋዕትነት መክፈል ይገባል፡፡ አገርን ሰላም ማድረግ፣ የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተሳትፎ በማረጋገጥ ብሔራዊ መግባት መፍጠር፣ ወደ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚያሸጋግረውን መደላድል ማመቻቸትና ከቂምና ከበቀል የፀዳ ምኅዳር ዕውን ማድረግ የጊዜው አንገብጋቢ ጥያቄ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን እርስ በርሳቸው እየተናቆሩ ለታሪካዊ ጠላቶች ክፍተት የሚፈጥሩ ከሆነ መከራው ለአገርና ለሕዝብ ነው፡፡ ይህንን አሳሳቢ ጊዜ በብልኃት ለማለፍ የጋራ ዓላማ ሊኖር ይገባል፡፡ ፈተናው ከባድ ሊሆን ቢችልም፣ ለአገር ጥቅም ሲባል መሥራት ከተቻለ መላው ሕዝብን የሚያግባባ ውጤት ማግኘት ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር ብዙ ይጠብቃል!

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram