fbpx

የኢትዮጵያና ኤርትራ ዕርቅ ማንን ያከስራል?

የኢትዮጵያና ኤርትራ ዕርቅ ማንን ያከስራል? | ሬሞንድ ሃይሉ 

አርስቶትል እንደሚለው የሰው ልጅ የፖለቲካ እንስሳ ባይሆን ኑሮ ሀገራት ባልተከፋፈሉ ነበር፡፡ ኢትዮጵያና ኤርትራም አንድ ከሚያደርጋቸው ነገር ይልቅ ልዩነትን ባላስቀደሙ ፡፡ግን እዚህም እዛም ፖለቲካ የነፍስ ጥሪ ሁኗል፡፡

በዚህም የተነሳ ሌላው ነገር በሙሉ በፖሊቲካ ተሸሮ መለያየት ምርጫ ሆነ፡፡ ፖለቲካ ስለለያየ ግን ህዝብ አይለያይም፡፡ ሀዘኑም ደስታውም ያው አንድ እንደሆነ ይቀጥላል፡፡ ጥላሁን ገሰሰ ሲሞት ታዋቂው ኤርትራዊ ድምጻዊ በረከት መንግሰተአብ ልቡ በሀዘን ቢሰበርም የሙያ አባቱን ለመቅበር ግን አልታደለም፡፡

እናም በሚያሰፈራው የኤርትራ የፖለቲካ ሰማይ ስር ሁኖ ጥሌን ለማስታወስ አሰመራ ያለ ሙዚቃ ቤቱን ለሶስት ቀናት ዘጋ፡፡ የፖለቲካ ሰዎች የቀኝ ገዥ ሀገር ድምፃዊ ሰለሞተ እንዴት የንግድ ድርጅት ትዘጋለህ ብለው ቢያፋጥጡትም ፖለቲካ ሳይሆን ሙዚቃ ያስተዋወቀውን ሰው አሰበለጠ፡፡

ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ ጦርነት ገብተው ሁሉም ነገር በነበር ሲቀር ሙዚቃው ግን ባለበት ቀጠለ፡፡ አስመራና መቐሌ አንድ ሙዚቃ ለሁለት ተካፍለው የሚያድሩ ከተሞች ከመሆን የሚያግዳቸው ጠፋ፡፡ የመሐል ሀገሩ ድምጻዊውም በእውን ያጣነውን ወደብ በምናቡ እያስመለሰ ማንጎራጎሩን ቀጠለ፡፡ የሀገሬውን ሰው የምናብ ዕስረኛ እደርጎም ከኤርትራ ሙዚቃ ዜማና ግጥም እየተዋሰ አዲስ አበባ ላይ ዝነኛ መሆን ተለመደ፡፡

ከጃኪ ጎሲ እሰከ ወንዲ ማክ፣ ከአሌክስ ኦሎምፒያ እሰከ ጆሲ እን ዘ ሃውስ የዘለቀው የኤርትራን ሙዚቃ የዜማ ምንጭ አድርጎ የመጠቀም አባዜ በበርካታ ወጣት ድምጻውያን ተለምዶ አዕላፍ የኤርትራ ሙዚቃዎች እንደ ድንበር ነዋሪዎች ወደ ኢትዮጵያ ፈለሱ፡፡

የጻሐይቱ ባራኺን ዜማዎች ህገ መንግስቱ የፈቀደ ይመስል እዚህም አዛም የሷን ሙዚቃ መዋስ ፋሽን ሆነ፡፡ የአብረሀም አፈወርቂ ስራዎች እየተኮረጁ በሸገር የምሽት ቤቶች ናኙ፡፡ የተኼሌ ተስፋዘጊ “ምስጥራዊው ድብዳቤ”ን የመሰሉ ስራዎች በየቦታው ስማቸው ገነነ፡፡ ታረቀ ተስፋሕይወትን የመሰሉ ኤርትራውያን የሙዚቃ ሰዎች ዜማቸው ዕየተበጣጠሰ የአማረኛ ሙዚቃ አዋዜ ሁኖ ቀረ፡፡

የሁለቱ ሀገር ህዝብ ፖለቲካ ለሀያ ዓመት ቢለያየውም በሙዚቃ ግን አብሮ ውሎ ሲያድር ኑሯል፡፡ ከፊሉ የሀገሬው ድምጸዊ ሲጨልም አይነጋም መስሎት በጠራራ ፀሐይ የኤርትራን ሙዚቃ በአደባባይ ሲዘርፍ ኑሯል፡፡ የቀረውም ብልጠት የታከለበት ስርቆትን እየተጠቀመ የአንድ ሰሞን ዘናን ተቀናጅቷል፡፡

ዛሬ ለወዲያ ማዶ ድምጻውያንም ቀን ወጥቶላቸዋል፡፡ ሰለዚህ ያን የዘመን ጨለማ ተገን አድርገን ስናከናውን የነበረውን የጥበብ ዝርፊያ ልናቆም ይገባል፡፡ የሁለቱ ሀገር ህዘብ ወንድም ነው እያለን በየመገናኛ ብዙሃን የምናወራ ድምጻውያንም የፖለቲካን ግንብ ምሽግ አድረገን ከወንድሞቻችን የወሰድናቸውን የግጥምና የዜማ ድረሰቶች በይፋ ዕውቅና ልንሰጥባቸው ይገባል፡፡

በርግጥ ለእንዲህ ያሉ ድምጻውያን የኮንሰርታቸው ዋና ድምቀት የሁለቱ ሀገራት መለያየት ነው፡፡ ፕሮሞተሮችም በውጭ ላለ የመድረክ ስራ ስለኢትዮጵያና ኤርትራ መለያት መዝፈንን ሲያበረታቱ የኖሩት ከምንም በላይ አዋጭ የቢዘነስ መንገድ በመሆኑ ጭምር መሆኑ አይካድም ፡፡ ዛሬ ይህ መንገድ ሊዘጋ ግንባታው ተጀምሯል፡፡

ከዕውነተኛ ስሜት ይልቅ ገብያን ታሳቢ አድርገው የኤርትራን ዜማ በአደባባይ እየዘረፉ ስለኢትዮጵያና ኤርትራ መለያየት የአዞ እምባ ያነቡ ድምጻውያን ዛሬ የዜማ ምንጫቸው እየደረቀ ነው ፡፡ የሁለቱ ሀገራት ዕርቅም ከከሰሩት ፖለቲከኞችች እኩል እንሱንም ያከስራቸዋል፡፡ DireTube 

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram