fbpx

HT

ሐበሻ ታይምስ ሚዲያ

AMHARIC

የኢሕአዴግ አራቱም ብሔራዊ ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ይወዳደራሉ

አራቱ የኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት ለጠቅላይ ሚኒስትርነት እንደሚወዳደሩ ታወቀ፡፡

አራቱ የኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች ማለትም የሕዝባዊ ወያነ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት)፣ የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን)፣ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) እና የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ሊቃነ መናብርት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት በሚደረገው ውድድር እንደሚሳተፉ ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በቅርቡ የኦሕዴድ ሊቀመንበር የሆኑት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የብአዴን ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኰንን እና የደኢሕዴን ሊቀመንበር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ  ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ግምት የተሰጣቸው እንደነበሩ የሚታወስ ሲሆን፣ የሕወሓት ሊቀመንበርና የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ለመወዳደር ዕጩ ሆነው እንደሚቀርቡ የሪፖርተር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የሕወሓት ከፍተኛ አመራር ለሪፖርተር እንዳረጋገጡት፣  ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን ይወዳደራሉ፡፡  ከዚህ በፊት በኢሕአዴግ ምክር ቤት ይሁንታ በማግኘት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሕወሓት ተመርጦ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁንም በምክር ቤቱ ይሁንታ ከተገኘ ለኢሕአዴግ ሊቀመንበርነትና ለጠቅላይ ሚኒስትርነት እንደሚወዳደሩ አመራሩ ጠቁመዋል፡፡

በተለያዩ መረጃዎች የሕወሓት ሊቀመንበር ለጠቅላይ ሚኒስትርነት እንደማይወዳደሩ ሲናገሩ ቢሰማም፣ ‹‹የተለያዩ ሰዎች የተለያየ ሐሳብ ሊያወሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ሕወሓት ዕድሉን ካገኘ ሊቀመንበሩን በዕጩነት ከማቅረብ የሚያግደው ነገር የለም፤›› ሲሉ አመራሩ አስረድተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የካቲት 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ከጠቅላይ ሚኒስትርነትና ከኢሕአዴግ ሊቀመንበርነት ለመነሳት ጥያቄ ማቅረባቸው የሚታወስ ሲሆን፣ የኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች  ሊቃነ መናብርት በዕጩነት እንደሚቀርቡ ይታወቃል፡፡

ለኢሕአዴግ ሊቀመንበርነትና ለአገሪቱ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ከፍተኛ ተወዳዳሪ ለመሆን አዲስ ሊቀመንበር የመረጠው ኦሕዴድ፣ ከዚህ በፊት የፓርቲው ሊቀመንበር የነበሩትን አቶ ለማ መገርሳን አንድ ደረጃ ዝቅ በማድረግ ዶ/ር ዓብይን በሊቀመንበርነት መምረጡ አይዘነጋም፡፡

ዓብይ (ዶ/ር) የኦሕዴድ ሊቀመንበር ሆነው ከተመረጡ ጀምሮ የኢሕአዴግ ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ ተብሎ ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ከአገር ውስጥ እስከ ውጭ ያሉ ሚዲያዎች እሳቸው ይሆናሉ በማለት፣ ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው መካከል በግንባር ቀደምትነት እንደሚጠቀሱ ሲዘግቡ ነበር፡፡

የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ለአንድ ወር ያደረገውን ስብሰባ ሲያጠናቅቅ አቶ ደመቀን በሊቀመንበርነት እንዲቀጥሉ መወሰኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

አቶ ደመቀ የብአዴን ሊቀመንበርና የአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው እያገለገሉ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን፣ ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ይሆናሉ የሚል ግምት እየተሰጣቸው ይገኛሉ፡፡

ለአገሪቱ ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ ተብሎ ግምት የተሰጣቸው ሌላው ዕጩ አቶ ሽፈራው ሲሆኑ፣ የደኢሕዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ለ24 ቀናት ባደረገው ስብሰባ የፓርቲው ሊቀመንበር አድርጎ መርጧቸዋል፡፡

አቶ ሽፈራው ከዚህ በፊት የደኢሕዴን ምክትል ሊቀመንበርና የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ሲያገለግሉ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ አቶ ኃይለ ማርያም ከኃላፊነት ለመነሳት ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት የፓርቲው ሊቀመንበር እንዲሆኑ ተመርጠዋል፡፡

የሕወሓት ሊቀመንበርና የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ለተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትርነት ይወዳደራሉ ተብሎ ብዙም ግምት ሲሰጣቸው ባይሰማም፣ በዕጩነት እንደሚቀርቡ ግን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram