fbpx

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በሀገሪቱ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት ያዋቀራቸው 12 ግብረ ሃይሎች ስራዎች ወደ ሚመለከታቸው ተቋማት ተላለፉ

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባለፈው ታህሳስ ወር ባካሄደው ስብሰባው በሀገሪቱ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት ያዋቀራቸው 12 ያህል ግብረ ሃይሎች ሲያከናውኗቸው የነበሩት ሥራዎች በቀጥታ ጉዳዩ በሚመለከታቸው ተቋማት እንዲከናወኑ መንግስት ወሰነ።

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ፥ የኢፌዴሪ መንግስት የህዝብን ጥያቄዎች እና ሳይፈቱ እየተንከባለሉ ዛሬ ላይ የደረሱ ችግሮችን ለመፍታት ከምንጊዜውም በላይ በቁርጠኝነት በመስራት ላይ ይገኛል ብሏል።

መንግሥትን የሚመራው ድርጅት /ኢህአዴግ/ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከታህሳስ 3 ቀን ጀምሮ ለ17 ቀናት ባካሄደው ስብሰባ በሀገሪቱ የሚታዩ የቆዩና ወቅታዊ ችግሮችን በመለየት በመንስኤና መፍትሄዎቻቸው ላይ ከመከረ በኋላ ችግሮቹ የሚፈቱበትን አቅጣጫ አስቀምጦ እንደነበር መግለጫው አስታውሷል።

በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተካሄዱ ህዝባዊ መድረኮች፣ ህዝባችን በመንግሥት ዘንድ የሚታዩ ጉልህ ድክመቶችን በማሳየት ረገድ መተኪያ የሌለው ሚና ተጫውቷል ብሏል ጽህፈት ቤቱ።

መንግስትም ከህዝቡ የተነሱትን ችግሮች በመቀበል እና ለመፍትሄዎቹም በመትጋት በርካታ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ ይገኛል ብሏል።

ችግሮቹን መፍታትም እንደየችግሮቹ ባህርያት የተቀመጡ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የለውጥ ሥራውን በባለቤትነት የሚመሩ 12 ያህል ግብረ ሃይሎችን በማቋቋም ወደሥራ ተገብቶ እንደነበረም ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው አስታስሷል።

ግብረ ሀይሎቹ በትክክል እና በቀጥታ በህዝቡ ውስጥ ያሉትን በርካታ ጥያቄዎችና ቅራኔዎች በተገቢው መንገድ መምራት እንዲችሉ አስፈላጊውን ድጋፍ እና ክትትል ከማድረግ ጀምሮ የለውጡን ሂደት በሚፈለገው ፍጥነት እና መጠን መምራታቸውን በቅርበት ብቻ ሳይሆን በትጋትም ጭምር ለመከታተል ብርቱ ጥረት ተደርጓልም ነው ያለው።

መንግሥት የግብረ ሃይሎቹን አፈጻጸም ከገመገመ በኋላ የህዝቡን ጥያቄዎች በአጥጋቢ ሁኔታ ለመፍታትና ሀገሪቱ ያጋጠሟትን ችግሮች ውጤታማ በሆነ መንገድ መፍታት የሚቻለው በተደራጀ ተቋማዊ አፈጻጸም መሆኑን ድምዳሜ ላይ ተደርሷል ብሏል መግለጫው።

በመሆኑም ግብረ ሀይሎቹ እስካሁን ሲያከናውኗቸው የነበሩትን ሥራዎች በቀጥታ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ተቋማት እንዲያስረክቡ በመንግሥት መወሰኑን ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል።

በዚህም መሰረት በግብረ ሀይሉም ሆነ በሚመለከታቸው ተቋማት በኩል ለጉዳዩ ተግባራዊነት ምንም የሚባክን ጊዜ እንደሌለ ታሳቢ ተደርጎ በአፋጣኝ ወደ ትግበራ እንዲገባ ግልጽ እና ጠንካራ አቅጣጫ ማስቀመጡ ተገልጿል።

መንግሥት በአሁኑ ጊዜ እያካሄደው ያለው የለውጥ ሥራ መነሻውና መድረሻው ህዝብን እያዳመጡ እና እያሳተፉ ችግሮችን መፍታት፣ ጥያቄዎቹን መመለስ፣ ስኬት የተመዘገቡባቸውን የሰላም፣ የልማት እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በማጠናከር የህዝቡን የላቀ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ መሆኑንም ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል።

እየተካሄደ ያለው የለውጥ ሥራ የደረሰበትን ሂደት አስመልክቶም በየጊዜው ለህዝብ የሚያሳውቅ መሆኑንም አመለክቷል።

ጽህፈት ቤቱ አክሎም የተጀመረው የለውጥ ስራ በአንድ ጀምበር የሚከናወን እንዳልሆነ መገንዘብ ያሻል በማለት ህዝቡ በዚሁ አግባብ መንግስትን እንደሚረዳና ለተጀመረው የለውጥ ሂደትም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት መንግስት እምነቱን የገለፀው።

የተጀመረውን ሀገራዊ የለውጥ ሥራ ከዳር ለማድረስ ህብረተሰቡ በተለመደው አርቆ አሳቢነት፣ ትዕግስትና ጽናት ከመንግሥት ጎን በመሰለፍ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል መንግሥት ጥሪውን አቅርቧል።

ኤፍ.ቢ.ሲ

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram