የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባውን ማካሄድ ጀመረ
የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ ዛሬ ማካሄድ ጀምሯል።
የኢህአዴግ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የግንባሩ አባል የሆኑት አራት ብሄራዊ ድርጅቶች የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ግምገማን መሰረት አድርገው ባካሄዱት ግምገማ ውጤት ላይ እንደሚወያይ ሰሞኑን መግለፃቸው ይታወሳል።
አቶ ሽፈራው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በታህሳስ ወር ባካሄደው ስብሰባ ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች በየብሔራዊ ድርጅቶች እንዴት እየተፈፀሙ እንዳሉ ይገመግማሉም ነበር ያሉት።
ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ሀገሪቱ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታና የጥልቅ ተሃድሶውን አፈፃፀም መነሻ በማድረግ ስራ አስፈፃሚው ያሳለፋቸው ውሳኔዎችና ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ያሉበትን ደረጃ ገምግሞ ቀጣይ አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጥም ጠቁመዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ኮሚቴው በስብሰባው ባለፉት ስድስት ወራት በመላው ሀገሪቱ የተከናወኑ ስራዎችን እና ፀድቀው ወደ ስራ የገቡ እቅዶችን አፈፃፀም እንደሚገመግምም አንስተዋል።
በተጨማሪም የኢህአዴግ ሊቀመንበር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ያቀረቡትን ከሃላፊነት መልቀቂያ ጥያቄ ተከትሎ የተፈጠረውን የአመራር ጉድለት የማሟላት አጀንዳን ተወያይቶ ለምክር ቤቱ እንደሚያቀርብ አቶ ሽፈራው ገልፀዋል።
በሌላ በኩል በኢህአዴግ ህገ ደንብ መሰረት የድርጅቱ ጉባዔ ከ2 ዓመት እስከ 2 አመት ከ6 ወር ባለው ጊዜ ውስጥ መካሄድ ሲገባው፤ በፀጥታና ወቅታዊ ጉዳዮች የተነሳ ባለመካሄዱ ምክር ቤቱ በህገ ደንቡ ላይ በተቀመጠለት ሃላፊነት መሰረት ጉባዔው የሚካሄድበትን ወቅት ይራዘም፤ አይራዘም በሚለው ላይ ውይይት ያካሂዳል ነው ያሉት።
የሁሉም ብሔራዊ ድርጅቶች ማዕከላዊ ኮሚቴዎች የየብሔራዊ ድርጅቶቹ ጉባኤ በስድስት ወር እንዲራዘም ውሳኔ በማሳለፋቸው እና አሁን በኢሕአዴግ ምክር ቤት ውሳኔ ላይ የሚሳተፉትም የብሔራዊ ድርጅቶቹ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በመሆናቸው ጥያቄው ተቀባይነት አግኝቶ እስከ ነሃሴ ወር ድረስ ሊራዘም እንደሚችል እምነታቸውን ገልፀዋል።
የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ታህሳስ ላይ ባደረገው ውይይት ወቅታዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ በማድረግ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል በተባበረ ድምፅ ወስኖ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሽፈራው፥ ከስብሰባው በኋላ በምስራቅ አማራ አካባቢዎች እና ኋላም በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የፀጥታ ችግር በመነሳቱ አዋጁ ተግባር ላይ መዋሉን ገልፀዋል።
በአንድ በኩል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተግባራዊ ማድረግና የሃገሪቱን የፀጥታ ችግር ማስተካከል በሌላ በኩል ደግሞ የብሔራዊ ድርጅቶች የተናጠል ጉባዔዎችን ማካሄድ ወቅታዊ ስራዎች ስለነበሩ የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚና የምክር ቤቱ ስብሰባዎች እስካሁን አለመካሄዳቸውን አንስተዋል።
ከስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ስብሰባ መጠናቀቅ በኋላም የኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ እንደሚካሄድም አቶ ሽፈራው ገልፀዋል።
በዚህ የምክር ቤቱ ስብሰባም የኢህአዴግ ሊቀመንበር እንደሚመረጥ ነው የጠቆሙት።
በድርጅታዊ እንቅስቃሴ፣ ችግሮች እና መፍትሄዎች ላይም ምክር ቤቱ ተወያይቶ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ እና አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጥ ይጠበቃል።