fbpx
AMHARIC

የአፍሪካ የጋራ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት ተፈረመ

የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት የአፍሪካ የጋራ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት ተፈራረሙ። ስምምነቱ የተፈረመው በንግድ ቀጠናው በሩዋንዳ ርዕሰ መዲና በኪጋሊ እየተካሄደ ባለው 10ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ነው።
ስምምነቱ ተግባራዊ የሚሆነው ከ15 እስከ 22 አባል አገራት ስምምነቱን በአገራቸው ህግ አውጪ አካል ወይም ፓርላማ ከጸደቀ ብቻ ነው።

ስምምነቱ የአፍሪካ አገራትን የንግድ ግንኙነት በማጠናከር በአህጉሪቷ የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት ይቀይራል የሚል እምነት ተጥሎበታል። በረቂቅ ስምምነቱ መሰረት የአፍሪካ አገራት 90 በመቶ በሚሆኑት ዕቃዎች ላይ የሚጥሉትን ቀረጥ የሚያነሱ ሲሆን አስፈላጊ በሚባሉ ቁሶች" ላይ የሚጣል የ10 በመቶ ቀረጥ ይኖራል ማለት ነው።

በተጨማሪም በስምምነቱ መሰረት የአፍሪካ አገራት ዜጎች ወደ ሌሎች አገራት ነጻ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚችሉ ተጠቁሟል። የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና እ.ኤ.አ በ1995 ከዓለም አቀፉ የንግድ ድርጅት ምስረታ በኋላ የተፈጠረ ትልቅ ነጻ ቀጠና እንደሆነ ተነግሯል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማሀማት ነጻ የንግድ ቀጠናው አፍሪካ በዓለም የንግድ ስርአት ውስጥ ያላትን ቦታ የሚያሳድግ እንደሆነ ገልጸዋል።

የንግድ ቀጠናው አፍሪካን በዓለም ላይ ከሚገኙ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ከሚመደቡ አገራትና ተቋማት ተርታ እንደሚያሰልፋትና ከሌሎች ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ማህበረሰቦች ጋር በእኩል ደረጃ መደራደር የሚያስችላትን አቅም የሚያጎለብት ነው" ብለዋል ሊቀመንበሩ። የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስኬት የተመሰረተው በፖሊሲ አውጪዎችና በግሉ ዘርፍ ትብብር ላይ ነው ተብሏል።

ለንግድ ቀጠናው ተግባራዊነት ከግሉ ዘርፍ ንቁ ተሳትፎና ድጋፍ እንፈልጋለን ያሉት የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ፤ ያለ እነሱ ድምጽ ወሳኝ የሚባል አንድ ነገር እንደሚጎል" ተናግረዋል። የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠናን ይፋ ለማድረግ በሚደረገው በዚሁ የስምምነት ስነ ስርአት ላይ የተመረጡ የአህጉሪቷ የግሉ ዘርፍ መሪዎችም ተገኝተዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የአፍሪካ የነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት ላይ ቁጥጥር የሚያደርግ የስራ ክፍል እንደሚያቋቁም ተገልጿል።

የአፍሪካ አገራት መሪዎች የአህጉሪቷን የነጻ የንግድ ቀጠና ለመመስረት እ.አ.አ በ2012 የተስማሙ ሲሆን ከሶስት ዓመት በፊት የምስረታውን ስምምነት ለመፈረም ድርድር መጀመራቸው የሚታወስ ነው። የአፍሪካ የነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት እ.አ.አ በ2020 የአፍሪካን አገራት የንግድ ልውውጥ በ52 በመቶ እንደሚጨምረው የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የንግድ ለልማት ጉባኤ በስምምነቱ መሰረት የአፍሪካ አገራት እቃዎች ላይ የሚጥሉትን ቀረጥ በማንሳታቸው የአራት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር ወጪ ቢያስወጣቸውም በረጅም ጊዜ ውስጥ ከንግድ ልውውጡ 16 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያስገኝላቸው ግምቱን አስቀምጧል።

Source ENA

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram