የአክሱም ሆቴሉ ቡድን የሚዲያ ውጊያ ክተት

መቀሌ የሚገኘው አክሱም ሆቴል የቪአይፒ ክፍሎች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከመንግስት ሀላፊነት በጡረታ በተወገዱ በህወሀት ነባር ታጋዮች ተሞልቷል፡፡ እነዚህ የቀድሞ ባለስልጣናት ከጦር ሰራዊት፣ ከደህንነት ወይም ከከፍተኛ የመንግስት ስልጣን ተነስተው በዚህ ለወትሮው በቱሪስቶች ማዘውተሪያ ቦታ የመሸጉት የለመዱትን ውስኪ ለመጨበጥ አመቺ ስፍራ ስለሆነ ብቻ አይደለም፡፡ በዚህ ሆቴል ውስጥ የኢትዮጵያን ፖለቲካ አቅጣጫ ሊለውጥ የሚችል አጀንዳን ያነሳሉ/ይጥላሉ፡፡ በቀደሙት ጊዜያት ሲያሾሯት የነበረችውን ሀገር አቅጣጫ ለመወሰን አዳዲስ እቅዶችን ያወጣሉ፡፡ ከስልጣን በመነሳታቸው ቁጭት ያደረባቸው እነዚህ የቀድሞ ባለስልጣናት በዚህ ቦታ ሆነው አዲሱን የአብይ አህመድን መንግስት ከማማት ጀምሮ በእያንዳንዱ እርምጃው ውድቀት እንዲገጥመው ሲመኙ ይውላሉ፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን የመንግስትን እርምጃ እግር በእግር እየተከታተሉ የመቃወም እና የማጥላላት ዘመቻ ይከፍታሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ እኛ ለትግራይ ቴሌቪዥን የአማርኛ ዴስክ ስርጭት ስራ ቅጥር ስናመለክትም ሆነ ቃለ-መጠይቅ ስናደርግ ሁሉንም የቀድሞ ባለስልጣናት በተለይም የቀድሞው የብሮድካስት ባለስልጣን ኃላፊውን አቶ ዘርአይ አስገዶም እና አቶ ጌታቸው ረዳን ያገኘናቸው እና ያነጋገሩን እዚሁ አክሱም ሆቴል ቪአይፒ ውስጥ ነበር በማለት ለተጠቀሰው ስራ ፍለጋ ወደዛ ያቀና አንድ ማንነቱ እንዲጠቀስ ያልፈለገ ጋዜጠኛ ይገልጻል፡፡

ትግራይ ቲቪ የአማርኛ ዴስክ ለመጀመር በዝግጅት ላይ ነው የሚገኘው፡፡ አሁን ላይ በተለያዩ ማማለያዎችና ጥቅማ ጥቅሞች የሰው ሀይል ማሟላት የጀመረው ቴሌቪዥኑ በቅርቡ ወደስራ ለመግባት ከፍተኛ ዝግጅት ማድረጉን ከቅርብ ምንጮች ማረጋገጥ ችለናል፡፡ በአዲስ አበባም የአማርኛ ዴስክ ቅርንጫፍ ቢሮ የመክፈት እቅድ ያለው ድርጅቱ ለዚህ ፕሮጀክቱ እጅግ ከፍተኛ መዋእለ ነዋይ መመደቡን ሰምተናል፡፡ ይህ ፕሮጀክት የተጸነሰውና በስራ ላይ እየዋለ ያለው ደግሞ በቀድሞ የመንግስት ባለስልጣናት እና በህወሀት ነባር ታጋዮች ነው ይላሉ ምንጮቻችን፡፡

ወዲ ዳኜ ወይም የቀድሞ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ሀላፊ ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው፣ የኢንሳው ሜጀር ጀነራል ዶክተር ተክለብርሀን ወልደአረጋዊ (ሳንቲም)፣ የጦር ሀይሎች ኤታማዦር ሹሙ ጀነራል ሳሞራ የኑስ፣ ብዙ ቦታዎች እጃቸው ያለው የውጪ ግንኙነት የፖሊሲ ጥናት እንዲሁም የኢፈርት ሀላፊው ሰው አቶ አቦይ ስብሀት፣ የቀድሞው ብሮድካስት ባለስልጣን ሀላፊው ዘርአይ አስገዶም፣ የቀድሞ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሚኒስትርና የህግ ጥናት ተቋም ዳይሬክተሩ ጌታቸው ረዳ እና ሌሎችም ቁልፍ የመንግስት ስልጣን የነበራቸው አንጋፋ የህወሀት ታጋዮችን ያሰባሰበው ቡድን ዋና ማዘዣውን (ኮማንድ ፖስቱን) እዚህ አክሱም ሆቴል ማድረጉ ቀድሞም ቢሆን የታወቀ የአደባባይ ሚስጥር ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች በተለያየ ጊዜ በሚሰጡት መግለጫ ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መቀሌ መሽገው ሰላም የሚነሱን አሉ፤ ስርቆትና ግፉ ሳያንሳቸው ዝም ስላልናቸው ሌት ተቀን እረፍት ይነሱናል የሚል ይዘት ባለው ንግግራቸው ሁሉንም ይፋ እስኪያደርጉት ድረስ መቀሌ ተቀምጠው ስለሚሰሩት ስራ በደንብ የሚታወቅም ጭምር ነው፡፡ አሁን ደግሞ እነዚህ ሰዎች በአንድ ፕሮጀክት ላይ መጠመዳቸውን ማረጋገጥ የቻልን ሲሆን በትግራይ መገናኛ ብዙሀን ስር የአማርኛ ዴስክ አቋቁሞ ለመጨረሻው የሚዲያ ውጊያ መዘጋጀት መሆኑን ደርሰንበታል፡፡

ለዚህ ፕሮጀክት መሳካት በቅርብ ሰሞን መንገድ የመጥረግ ስራ የጀመሩት የቀድሞ ባለስልጣናቱ ከነርሱ እቅድ ጋር አብሮ አይሄድም ያሉትን የትግራይ መገናኛ ብዙሀን ኤጀንሲ ሀላፊንና ነባር የህወሀት ታጋዩን አቶ ብርሃኑ አባዲን ከሀላፊነት ገሸሽ በማድረግ ነበር እርምጃቸውን አንድ ያሉት፡፡ እርሱን ተከትሎ አሁን ላይ ለሚከፈተው ጣቢያ ተስማሚ የሆኑ ጋዜጠኞችንና የሚዲያ ባለሙያዎችን ቅጥር በመፈጸም ላይ የሚገኙት ሰዎቹ ለዚህ አመቺ ሆኖ ያገኙት ደግሞ በሁለት አመቱ ለመዘጋት ከበቃው ከቀድሞው የ ኢኤንኤን ቴሌቪዥን ጣቢያ ምልመላ ማድረግ አንዱ ነበር፡፡ በግል ሚዲያነት የስም ሽፋን ተከልሎ ሲሰራ የቆየው ኢኤንኤን ጣቢያ የመንግስት በተለይ የደህንነት መስሪያ ቤት ዋና ተደጓሚ ድርጅት እንደነበር ሲደረስበት ባለፈው ሀምሌ ከ 100 በላይ ሰራተኞችን በትኖ በሁለት አመቱ ከዚህ አለም በሞት መለየቱ ይታወሳል፡፡

ሚዲያው የግለሰብነት ሽፋን እንዲያገኝ ዋና ሚና ሲወጡ የቆዩት የኢትዮጵያን ፈርስት ድህረ ገጽ መስራቹ ሰው እና የደህንነት መስሪያ ቤቱ ሀላፊ ጌታቸው አሰፋ የቅርብ ሰው የሆነ አንድ ሰው ነበሩ፡፡ በእነኚህ ሁለት ሰዎች ጠቋሚነት ኢኤንኤን ከመዘጋቱ በፊት የህወሀት ሰዎች ባለሙያዎችን ወስደው መቀሌ ላይ ሰፊ ተደራሽነት ባለው በአማርኛ ቋንቋ አንድ ሚዲያ የመመስረት ምክረ ሀሳብ የቀረበለት የአክሱም ሆቴሉ ቡድንም ለጀመረው ፕሮጀክት ስኬት መንገዶች ቀድመው አመቺ እንደሆኑለት ነው ምንጮቻችን የሚያስረዱት፡፡

ይህን ተከትሎ የሰራተኛ ቅጥር ምልመላውን ስራ ከፈቱ የ ኢኤንኤን ወጣት ጋዜጠኞች ላይ ያተኮረው የአክሱም ሆቴሉ ቡድን አሁን ላይ እጅግ ከፍተኛ ጥቅማ ጥቅምና ደሞዝ በማቅረብ የሚዲያ ባለሙያዎችን ማሰባሰቡን እያገባደደ እንደሚገኝ በምንጮቻችን በኩል አውቀናል፡፡ የአክሱሙ ቡድን የሚያቀርበው ደሞዝ ደግሞ ወደጎን የማይሉት እንደሆነባቸው እነዚሁ ምንጮች ይጠቅሳሉ፡፡ ከስራ ልምድና ከእውቀቱ በታች ሲከፈለው የነበረ ባለሙያ አሁን እስከ 50 ሺህ ብር ወራዊ ደሞዝ፣ ትራንስፖርት፣ ስልክና ቤት ይቀርብለታል፡፡ ሌላው ቀርቶ ዝቅተኛ የስራ ልምድ ቢኖራቸው እንኳን በጠቋሚዎች ይቀጠሩ ተብለው አክሱም ሆቴል ለቃለመጠይቅ የቀረቡ ወጣት ባለሙያዎች ኢኤንኤንም ሆነ ሌላ ቦታ ከሚያገኙት በ 3 እጥፍ የሚበልጥ ደሞዝ ቀርቦላቸዋል፡፡ የአክሱም ሆቴሉ ቡድን ለገንዘብ ግድ የለበትም ያሉት ምንጮቻችን ትንሹ የባለሙያዎች የደሞዝ መጠን ተብሎ የቀረበው ከ 30 ሺህ ብር በላይ መሆኑን አረጋግጠውልናል፡፡ ከኢኤንኤን ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ቴሌቪዥን ጣቢያዎችም ለአዲሱ ፕሮጀክት ተስማሚ ናቸው የተባሉ ሙያተኞች መቀሌ መጠራታቸውን አውቀናል፡፡ የደርሶ መልስ የአውሮፕላን ትኬት እንዲሁም የሆቴል መቆያ ወጪ ተችሎት መቀሌ ላይ በከፍተኛ ደሞዝ ለስራ ቅጥር መጠራት ደግሞ እንኳን አዲስ አበባ ስራ ፈቶ የተቀመጠን ቀርቶ ሞያሌ ላይ ያለን ሰውም የሚያማልል መሆኑን ምንጮቻችን ይናገራሉ፡፡

የአክሱሙ ቡድን ይህን ፕሮጀክት ያቀደው በፖለቲካው ሜዳ ያጣውን ጥቅም በሚዲያ ውጊያ ለማስመለስ ባለው ፍላጎት እንደሆነ መረዳት ችለናል፡፡ ቡድኑ መቀሌ ተቀምጦ የሚዲያ ውጊያን ለመክፈት ያሰበው ጥቅሙን ለማስጠበቅ ብቻም ሳይሆን ተወስዷል የሚለውን የህወሀት የበላይነትንም ለማስመለስ ጭምር እንደሆነ ይነገራል፡፡ የቅርብ ምንጮች ይህን ቢሉም ይህ ቡድን በቀድሞው አገዛዝ ወቅት ለተፈጸሙ ግራንድ ሙስናና ምዝበራዎች እንዲሁም የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በቡድኑ ውስጥ ያሉ ሰዎች ስም ተደጋግሞ መነሳት ምቾት እንዳልሰጠው ነው የሚገመተው፡፡ በቅርብ ጊዜያት በተለያዩ የክልልና የፌደራል መገናኛ ብዙሀን የቀድሞ አገዛዝ አስተዳደራዊ በደሎች እንዲሁም ምዝበራና ሙስና እየተጋለጠ ይገኛል፡፡ ለነዚህ ሁሉ ወንጀሎች ደግሞ መቀሌ የመሸገው ቡድን አባላትና የቀድሞው ስርአት በተለይ የህወሀት ባለስልጣናት ስም ተደጋግሞ በተጠያቂነት ይነሳል፡፡ የአክሱም ሆቴሉ ቡድን ያለተጠያቂነት በክብርና በጡረታና በይቅርታ መሸኘቱ ትልቅ እድል መሆኑ ቢታወቅም ነገር ግን አሁንም ቢሆን ከተጠያቂነት ሙሉ ለሙሉ ለማምለጥ የሚችልበትን ዋስትና ለማግኘት ሲጥር መቆየቱ ይታወቃል፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች በቅርብ ጊዜያት ከሚነሱ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች ጀርባም ቢሆን ረጅም እጅና ድብቅ የሴራ ጉንጉን መኖሩ ደጋግሞ ይነገራል፡፡ ይህ የሴራ ድር ደግሞ ዞሮ ዞሮ የአክሱም ሆቴሉ ቡድን አባላት ጋር እንደሚደርስ በመንግስት ባለስልጣናት ሳይቀር በግልጽም ባይሆን በዘወርወዘራው ሲጠቀስ ቆይቷል፡፡ ይህ ቡድን በሀገሪቱ የተፈጠረው ለውጥ ምቾት ከነሳቸው ወገኖች ቁንጮው ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በዚህ ሁሉ የተነሳ ያሰበውን ለማሳካት ቡድኑ የራሱ ልሳን የሆነ ሚዲያ በተለይ ሰፊ ተሰሚነት ባለው የአማርኛ ቋንቋ መክፈትን አማራጭ ቢያደርገው የሚያዛልቅም ባይሆን እንደ ዋነኛ መመከቻ መንገድ ሊያገለግለው እንደሚችል ይገመታል፡፡

የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዘዳንት እና በእስር ላይ የሚገኙት አብዲ ኢሌ በቅርብ ጊዜያት ተመሳሳይ እርምጃ ሲወስዱ ታይተዋል፡፡ ሰውየው በ 2010 አጋማሽ ላይ የአማርኛ ደስክ በሶማሌ ክልል ቴሌቪዥን ለመክፈት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ነበር የቆዩት፡፡ የ 10 ሺህ ብር ደሞዝ ብርቅ ለሆነባቸው ጋዜጠኞች ከ 20-30 ሺህ ብር ደሞዝ፣ መኪናና ቤት እያቀረቡ ከአዲስ አበባ ሲያስመለምሉ እንደነበር በቅርበት ለማወቅ ችለናል፡፡ ይሁን እንጂ የራሳቸው ግፍና ወንጀል ጠልፎ የጣላቸው አብዲ ኢሌ በስተመጨረሻ ወደ እስር ቤት ከመወርወር ያቋቋሙት የሚዲያ ልሳን አላዳናቸውም ነበር፡፡ ያም ቢሆን ግን ይህን የሶማሌ ቴሌቪዥንን በመጠቀም ሰውየው የረጩት ፕሮፖጋንዳና ግጭት አባባሽ የጥላቻ መልእክት ጦሱ በስተመጨረሻ በጅግጅጋና በክልሉ አንዳንድ ቦታዎች ለተፈጠረው እልቂት ማገልገሉ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ጅግጅጋንና አካባቢውን ለማረጋጋት የገባው የፌደራል የጸጥታ ሀይል አዛዦች በቅድሚያ ከወሰዷቸው እርምጃዎች መካከል የአብዲ ኢሌ ልሳን የሆነውን የሶማሌ ቴሌቪዥንን ማስጠንቀቅና የእርምት እርምጃ መውሰድ አንዱ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም፡፡

በ ኢኤንኤን እንዲሁም በሶማሌ መገናኛ ብዙሀን የተሞከሩት ሚዲያን የውጊያ መመከቻ አድርጎ የመጠቀም ዝንባሌ አሁን አክሱም ሆቴል የመሸገው ቡድን ዋነኛ የፖለቲካ ስልት አካል ነበር፡፡ በቡኖ በደሌ የግጭት አባባሽ ዘገባው፣ በአርበኞች ግንቦት 7 ታጋዮች ምርኮና ግድያ ዶክመንተሪዎቹ እንዲሁም በዶ/ር መረራ ጉዲና እስር ላይ ሰፊ ዘመቻ የከፈተው ኢኤንኤን አብይ አህመድ በጠቅላይ ሚኒስትርነት እንደተመረጡ ሰፊ የማጥላላት ዘገባዎችን ሲሰራ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆንይሁን እንጂ ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የታተረውና የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ኢላማ አድርጎ ሲያጠቃ የቆየው ይህ ተቋም በስተመጨረሻ በህዝብ ተጠልቶና ጥቂት መልካም ስራዎቹንና ጥቂት የማይባሉ ንጹህ ባለሙያዎቹን ሰለባ አድርጎ ለመዘጋት በቃ እንጂ የተንኮል አላማው አልተሳካም ነበር፡፡ አብዲ ኢሌ በሶማሌ መገናኛ ብዙሀን ስር የተከሉት የቴሌቪዥን ስርጭትም ቢሆን ሰውየው ያሰቡትን ተንኮል ሳያሳኩበት እና በጥቅማ ጥቅም የሰበሰቧቸው ባለሙያዎች ከጅግጅጋ ከተማ መውጫ ቀዳዳ እስኪያጡ ድረስ ለችግር ተዳርገው ክልሉን አበጣብጠው ሜዳ ላይ እንደጣላቸው በቅርብ ጊዜ አይተናል፡፡ ከዚህ ሁሉ ተሞክሮ ያልተማረው የአክሱም ሆቴሉ ቡድን ግን ለሌላ ተመሳሳይ ጥፋት መቀሌ ላይ የጥላቻ ሚዲያ ለማቋቋም ሲታትር ነው የምናገኘው፡፡

የትግራይ ክልል ህዝብና መንግስት በመረጠው አይነት ሚዲያ የመገልገል፣ የመረጠውን አይነት የማቋቋም እና ባሻው ሚዲያ ድምጹን የማስተጋባት የማይጣስ ህገመንግስታዊ መብት እንዳላቸው ማንም አይክድም፡፡ አሁን ላይ ሚኒሊክ ሂትለር፣ ነፍጠኛ ይውደም፣ እና ሌላም ሌላም የጥላቻ መልእክቶችና ሙዚቃዎችን ለ 24 ሰአታት የሚለቁ የሳተላይት ቴሌቪዥኖች በሞሉበት ሀገር ማንም አካል የፈለገውን አይነት ሚዲያ ቢያቋቁም ተቆጣጣሪውን መንግስትን የሚያስወነጅል እንጂ እንደ ሀጢያት የሚታይ አይደለም፡፡ ትግራይ ቴሌቪዥንን ጨምሮ ሁሉም የክልል መገናኛ ብዙሀን በዚህች ሀገር ገንቢ ሚና እየተጫወቱ ስለመሆናቸው ደፍሮ መናገር አይቻልም፡፡ ሁሉም በየፊናው አንዱ ሌላውን ማጥላላት ላይ ከሞላ ጎደል የተጠመዱ ሲሆን አሁን ለተፈጠረው ለውጥ በአግባቡ ድጋፍ ለመስጠት ይችላሉ ብሎ ማመን ይከብዳል፡፡ ይህ ሁሉ በተቆጣጣሪው አካልና በመንግስት እየታየ መልክ ሊበጅለትና ሊስተካከል የሚገባው ጉዳይ ሆኖ ነው የምናገኘው፡፡

ይህ ድርብርብ ችግር ሳይስተካከል ደግሞ የፕሮፓጋንዳ መገልገያ የሚሆን አዲስ ሚዲያ እየፈጠሩ ለጥፋት ውጊያ መሰለፍ ሌላ ራስ ምታት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የትግራይ መገናኛ ብዙሀን በቅርቡ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሰጠውህን የተውሶ ቢሮ ባስቸኳይ ልቀቅልኝ የሚል ቀጭን ትእዛዝ ያዘለ ደብዳቤ መጻፉ ታውቋል፡፡ ይህ ተቋም በቦንብ አደጋ በታጀበው በሰኔ 16ቱ የመስቀል አደባባይ ሰልፍ ማግስት ከፌደራል መንግስቱ ጋር የገባበትን እሰጥ አገባ የምናስታውሰው ነው፡፡ ከዛ በፊትም ሆነ በኋላ ትግራይ ቴሌቪዥን (ትግራይ መገናኛ ብዙሀን) በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሚሰጣቸው የዘገባ ሽፋኖቹ በተደጋጋሚ በህዝብ ሲተች መቆየቱም አይዘነጋም፡፡ ተቋሙ ሀላፊነት በሚሰማውና የፌደራል መንግስቱ አካል በሆነ የክልል መንግስት ስር እስከተዳደረ ድረስ እስከአሁን የሄደባቸውን መንገዶች ገምግሞ የተሻለ ተቀባይነት ሊያስገኙለት የሚችሉ ስራዎችን ወደፊት ለመስራት ይቸገራል ተብሎ አይታመንም፡፡ ይሁን እንጂ ከመንግስት ስራም ሆነ ሀላፊነት ውጪ ያሉ ሰዎችን ባሰባሰበው፤ ከተጠያቂነት ለመሸሽ የሚጥሩና ምቾት የነሳቸውን ለውጥ ለመቀልበስ የቆረጡ ሰዎች የፈጠሩት የአክሱም ሆቴሉ ቡድን የትግራይ ቴሌቪዥንን ለራሱ መገልገያ ሊያደርገው ማሰፍሰፉን ነው ሁኔታውን በቅርበት የታዘቡት የነገሩን፡፡ ይህ ቡድን ለመጨረሻ የተስፋ መቁረጥ ውጊያው የክልል መንግስቱን ሚዲያ ከማዋል ባለፈም የዶ/ር ደብረጽዮንን አስተዳደር በእጅጉ እየፈተነ እንደሚገኝ ነው የሚገመተው፡፡ የደህንነት ዋስትና ማግኘትና ከተጠያቂነት የማምለጥ ጥያቄ ያለበት ቡድኑ የደብረጽዮን አስተዳደር ከለላ ካልሰጠው በክልሉ መንግስትና ህዝብ ላይም ከመዝመት አይመለስም በማለት ነው በስፍራው ተገኝተው የነበሩ የመረጃ ምንጮቻችን የገለጹት፡፡

Sheger Times Magazine

Share your thoughts on this post

%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram