fbpx
AMHARIC

የአሜሪካ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጥሮ ጋዝን ወደ ድፍድፍ ነዳጅ የሚቀይር ፋብሪካ ለማቋቋም ጥያቄ አቀረቡ

ግሪንኮም እና ኢኖቬቲቭ ክሊር ቾይስ ቴክኖሎጂስ (ICCT) የተባሉ ሁለት የአሜሪካ ኩባንያዎች፣ የተፈጥሮ ጋዝን ወደ ሰው ሠራሽ ድፍድፍ ነዳጅ የሚለውጥ ፋብሪካ ኢትዮጵያ ውስጥ ለማቋቋም ጥያቄ አቀረቡ፡፡

ኩባንያዎቹ የኢትዮጵያ ማዕድን፣ ነዳጅና ባዮፊውል ልማት ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር የነዳጅ ፋብሪካውን ሶማሌ ክልል ውስጥ በሁለት ቢሊዮን ዶላር ወጪ ለመገንባት ዕቅድ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ የማዕድን፣ ነዳጅና ባዩፊውል ኮርፖሬሽን የነዳጅ ፍለጋና ልማት ዳይሬክተር አቶ አንዳርጌ በቀለ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ግሪንኮምና አይሲሲቲ ጂቲኤል በተባለ ቴክኖሎጂ የተፈጥሮ ጋዝን ወደ ድፍድፍ ነዳጅ በመቀየር የተለያዩ የነዳጅ ውጤቶችን ለማምረት የሚያስችል ፋብሪካ ለመገንባት የሚያስችል ዕቅድ አቅርበዋል፡፡ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ከሚመረተው ድፍድፍ ነዳጅ ቤንዚን፣ ናፍጣ፣ የአውሮፕላን ነዳጅ፣ ነጭ ጋዝ፣ ቡታ ጋዝና የሞተር ቅባቶች ማምረት እንደሚቻል አቶ አንዳርጌ ገልጸዋል፡፡

ግሪንኮምና አይሲሲቲ፣ አክሰን ቴክኖሎጂ ግሩፕና ቴክኒፕ የተሰኙ የፈረንሣይ ኩባንያዎች ቴክኖሎጂ ተጠቅመው የጂቲኤል ነዳጅ ፋብሪካ ለመገንባት እንዳቀዱ ታውቋል፡፡ የኢንጂነሪንግና ግንባታ ሥራዎቹን የሚያካሂዱት የፈረንሣይ ኩባንያዎች ሲሆኑ፣ የፕሮጀክቱን ፋይናንስ የሚያቀርቡት ሜሪል ሊንችና ዌይስት ሞርላንድ ኢኩቲ ፈንድ የተባሉ ኩባንያዎች እንደሆኑ ተገልጿል፡፡

ግሪንኮምና አይሲሲቲ ከኢትዮጵያ ማዕድን፣ ነዳጅና ባዮፊውል ልማት ኮርፖሬሽን በጋራ ተባብሮ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡ ኩባንያዎቹ ያቀረቡትን ዕቅድ የገመገሙት የኮርፖሬሽኑ ባለሙያዎች የጂቲኤል ቴክኖሎጂን ለማጥናት ወደ ፈረንሣይ ፓሪስ ተጉዘው፣ በአክሰን አይኤፍፒ ቴክኖሎጂ ኩባንያ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ ባለሙያዎቹ የኩባንያዎቹን ገጸ ታሪክ፣ ያቀረቡትን የአዋጭነት ጥናትና ቴክኖሎጂ መገምገማቸውን አቶ አንዳርጌ  ተናግረዋል፡፡ ‹‹የቴክኒክ፣ የፋይናንስና የሕግ ጉዳዮችን ተመልክተናል፤›› ብለዋል፡፡ ግሪንኮምና አይሲሲቲ ባቀረቡት ዕቅድ መሠረት ለነዳጅ ፋብሪካው ግንባታ የሚያስፈልገውን ቴክኖሎጂና ገንዘብ የሚያቀርቡ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ለፋብሪካው ግንባታ የሚውል መሬትና የኢንቨስትመንት ዋስትና ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡፡

ግሪንኮምና አይሲሲቲ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመተባበር በሚያቋቁሙት የአክሲዮን ኩባንያ 85 በመቶ ድርሻ ለመያዝ፣ ለመንግሥት በነፃ 15 በመቶ ድርሻ ለመስጠት ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

በሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ኦጋዴን ተፋሰስ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት መገኘቱ ይታወቃል፡፡ የአሜሪካ ኩባንያዎች ያቀረቡትን የነዳጅ ፋብሪካ ግንባታ ተግባራዊ ለማድረግ፣ በኦጋዴን በነዳጅ ፍለጋና ምርት ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች ይሁንታ ያስፈልጋል፡፡

በካሉብ፣ በሂላላና በገናሌ የሚገኘው የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ፖሊ ጂሲኤል በተባለው የቻይና ኩባንያ ይዞታ ሥር የሚገኝ ሲሆን፣ በኤልኩራን ያለው የጋዝ ክምችት ኒው ኤጅ በተባለ የእንግሊዝ ኩባንያ ይዞታ ሥር የሚገኝ በመሆኑ፣ እነዚህ ኩባንያዎች ሊገነባ ለታሰበው የነዳጅ ፋብሪካ የተፈጥሮ ጋዝ ለማቅረብ መስማማት ይኖርባቸዋል፡፡ በካሉብና በሂላላ አራት ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ፣ በገናሌ 0.6 ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ፣ በኤልኩራን 1.4 ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ በአጠቃላይ 6.1 ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ የሚገመት የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ይገኛል፡፡

በካሉብና በሂላላ የሚገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ለማልማት የሚያስችለውን የፔትሮሊየም ልማትና የምርት ክፍፍል ስምምነቶች ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር እ.ኤ.አ. 2013 የተፈራረመው ፖሊ ጂሲኤል፣ የጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ ጂቡቲ ወደብ ድረስ በመዘርጋት ወደ ቻይና ኤክስፖርት ለማድረግ ያለውን ዕቅድ አቅርቧል፡፡ ኩባንያው በጂቡቲ የጋዝ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ እንደሚነባ ገልጾ፣ በአጠቃላይ አራት ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

ፖሊጂሲኤል እ.ኤ.አ. በ2017 የጋዝ ምርት ኤክስፖርት ማድረግ እንደሚጀምር ገልጾ የነበረ ቢሆንም፣ እስካሁን የጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ ዝርጋታው እንዳልጀመረ ታውቋል፡፡

የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በዕቅድ ደረጃ የቀረበው የጂቲኤል ፋብሪካ ግንባታ እንዲሳካ ሚኒስቴሩ ከፖሊ ጂሲኤልና ኒው ኤጅ ጋር ተደራድሮ የተወሰነ መጠን ያለው የጋዝ ምርት አዲስ ለሚቋቋመው የነዳጅ ፋብሪካ እንዲሸጡ ማግባባት ይጠበቅበታል፡፡ ‹‹ፖሊ ጂሲኤል የጋዝ ምርቱን ወደ ቻይና ለመላክ ከፍተኛ ጉጉት ያለው በመሆኑ፣ አዲስ ለሚገነባው ፋብሪካ ጋዝ እንዲሸጥ ማሳመን ከባድ ሥራ ሊሆን ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

ሊገነባ የታቀደው የጂቲኤል ፋብሪካ 1.4 ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ የተፈጥሮ ጋዝ ማግኘት ቢችል በየቀኑ 35,000 በርሜል ነዳጅ ለ17 ዓመታት ያህል ማምረት እንደሚችል የገለጹት አቶ አንዳርጌ፣ የኢትዮጵያ የዕለት የነዳጅ ፍጆታ 70,000 በርሜል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹አገራችን ለነዳጅ ግዥ በየዓመቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የምታወጣ በመሆኑ፣ አገር ውስጥ ነዳጅ ማምረት ጊዜ ሊሰጥ የሚገባው ጉዳይ አይደለም፡፡ የኢነርጂ ዋስትና ማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በግሪንኮምና አይሲሲቲ የቀረበውን ዕቅድ የኢትዮጵያ ማዕድን፣ ነዳጅና ባዮፊውል ልማት ኮርፖሬሽን ከገመገመ በኋላ ለኮርፖሬሽኑ ቦርድ አቅርቧል፡፡ የዳይሬክተሮች ቦርዱ የተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና የብሔራዊ ባንክ በአባልነት የሚገኙበት ኮሚቴ ጉዳዩን እንዲመለከተው አድርገዋል፡፡

የሚኒስትሮች ኮሚቴ የተለያዩ ዳይሬክተሮች የሚገኙበት የቴክኒክ ቡድን ተቋቁሞ የቀረበውን ዕቅድ በዝርዝር አጥንቶ ሪፖርት እንዲያቀርብ በሰጠው መመርያ መሠረት፣ የቴክኒክ ቡድኑ ከሁለት ሳምንት በፊት ሪፖርቱን ማቅረቡ አቶ አንዳርጌ አስረድተዋል፡፡ የቀረበውን ሪፖርት ተመልክቶ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ ከፍተኛ የፔትሮሊየም ጂኦሎጂስት የታቀደው የጂቲኤል ፕሮጀክት ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት የጎላ አስተዋጽኦ ሊኖረው እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ ‹‹የውጭ ምንዛሪ እጥረት ፈታኝ ችግር በመሆኑ የተፈጥሮ ጋዝን እንዳለ ወደ ውጭ ከመላክ በአገር ውስጥ አምርቶ መጠቀሙ የበለጠ አዋጭ ሊሆን ይችላል፤›› ብለዋል ባለሙያው፡፡

ኢትዮጵያ በዓመት ከሦስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ ነዳጅ የምታስገባ ሲሆን፣ ከ2.8 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ታደርጋለች፡፡

ምንጭ፡- ረፖርተር

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram