fbpx
AMHARIC

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን አዲስ አበባ ገቡ

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን ለማድረግ አዲስ አበባ ገብተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት አቀባበል አደርገውላቸዋል።

ሬክስ ቲለርሰን በቆየታቸው ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር ተገናኝተው ይወያያሉ።

በውይይታቸውም በንግድ እና ኢንቨስትመንት፣ በቀጠናው ሰላምና ደህንነት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ፀረ ሽብር ትግል ዙሪያ ይመክራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

ከዚህ ባለፈም ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሃማት ጋር በወቅታዊ የአፍሪካ የደህንነት ስጋቶች እና የምጣኔ ሀብት አማራጮች ዙሪያም ይወያያሉ።

በተለይ የደቡብ ሱዳን፣ የሶማሊያ እና የቻድ ሃይቅ አካባቢ ሀገራት የፀጥታ ጉዳይ ቀዳሚ የመወያያ ነጥቦች ይሆናሉ ነው የተባለው።

ቲለርሰን የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን እንዳጠናቀቁ፥ በጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ናይጄሪያ እና ቻድ ተመሳሳይ ጉብኝት የሚያደርጉ ይሆናል።

ኢትዮጵያና አሜሪካ ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላለፉት 72 አመታት የቦይንግ ኩባንያ ቋሚ ደንበኛ ሆኖ ቀጥሏል።

አየር መንገዱ ከሚጠቀምባቸው 96 አውሮፕላኖች መካከል 69ኙ ቦይንግ ሰራሽ ናቸው።

ባለፉት ጥቂት አመታት አየር መንገዱ ከቦይንግ ኩባንያ በአውሮፕላንና በአውሮፕላን ሞተር ግዥ 21 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ያክል ወጪ አድርጓል።

ይህም ወደ 115 ሺህ ለሚጠጉ አሜሪካውያን የስራ እድል እንዲፈጥር እንዳስቻለው ከኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram