fbpx

የት ነበርን? ወዴትስ እየሄድን ነው?

መንግሥት የጀመረው የለውጥ ሂደት ፈለጉን አይለቅም!!

አገራችን ኢትዮጵያ በለውጥ ሂደት ላይ እንደምትገኝ ብዙ የተባለለት ጉዳይ ነው፡፡ ለውጡ በተለይ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ዜጎቻችንና ሕዝቦቻችን ሁለንተናዊ ሕይወት ውስጥ እስካሁን ያመጣው መሻሻል ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ይሁንና ለውጡ በአንድ ጀንበር ክስተት የሚፈጸም ባለመሆኑ አሁንም በሂደት ላይ ይገኛል፡፡ ቀደም ሲል ብዙ ያልተጠበቁና ያልታሰቡ የሚመስሉ ነገሮች በመከሰታቸው፤ አሁንም በመከሰት ላይ በመሆናቸው “የት ነበርን? ወዴትስ እየሄድን ነው?” የሚሉ ጥያቄዎች ሲነሱ ይደመጣል፡፡ የዚህን የለውጥ ሂደት ምንነት፤ አዝማሚያና አቅጣጫ በተመለከተ ያለው ግንዛቤና አስተያየት ግን ከተመልካች ተመልካች ይለያያል፤ አልፎ አልፎም ይቃረናል፡፡

በመንግሥት እምነት የለውጥ ሂደቱን አንጥሮ ለመገንዘብ በተገቢው የጊዜ አውድ ውስጥ ማየት ጠቃሚ ነው፡፡ የለውጥ ሂደቱ መታየት ያለበት በዕለትና በአንድ ሰሞን ብቻ ሳይሆን በረዥም የጊዜ አውድ ውስጥ ጭምር እንደሆነ መንግሥት ያምናል፡፡ ትላንት ከሕገ-መንግሥት በሚቃረኑ አዋጆችና ደንቦች ከለላነት በዜጎች ላይ ይፈጸም የነበረው ግፍ ምን ያህል ሰብዓዊ ጥፋት እንዳስከተለ ግልጽ ነው፡፡ ይህን ከተጎጂዎቹ በመቀጠል ከማንም በላይ የሚረዳው መንግሥት ዛሬ ዜጎችና ሕዝቦች ሰብአዊና ዲሞክራሲዊ መብቶቻቸው እንዲከበርላቸው አስፈላጊውን ሕጋዊና ተቋማዊ እርምጃዎች ወስዶ የሰብዓዊና የፖለቲካ ምህዳሩን አስፍቷል፡፡ ትላንት የተፈጸሙ ወንጀሎችንና ጥፋቶችን እንደየሁኔታው በሕግ አግባብ የሚስተናገደውን በሕግ አግባብ እያስተናገደ ነው፡፡ ለይቅርታ የሚመጥኑት በደሎችና ስህተቶችም በልባዊ ይቅርታ ይስተናገዳሉ፡፡ ይህ የለውጥ ሂደት በቁርጠኝነት ተጀምሯል፤ ነገም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

በርግጥ እዚህም እዚያም ከለውጡ ጋር አብረው የማይሄዱ ጊዚያዊ ኹነቶች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፤ የለውጡ ሂደት ግን ፈለጉን አይለቅም፡፡ ዛሬ ከሕግ ውጭ ሰዎች አይታሰሩም፤ በማረሚያ ቤት ያሉትም ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ድርጊት አይፈጸምባቸውም፡፡ ዜጎች ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን ተጠቅመው በሕጋዊ መንገድ አሳባቸውን በነጻ ይገልጻሉ፤ ይሰበሰባሉ፤ ሰላማዊ ሰልፍ ያደርጋሉ፤ ይደራጃሉ፤ በመሰላቸው የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ይሳተፋሉ፡፡ ማዶና ማዶ በባላንጣነት ይተያዩ የነበሩ ዜጎች እንዲቀራረቡ ጥረት ተደርጓል፤ በተቋማት ተለያይተው የነበሩም ተፎካካሪዎችም እርቅ እንዲያወርዱ ተደርጓል፡፡ በአገራቸው ብቻ ሳይሆን ከአገራቸው ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ጉዳይ ቀጥታ ተሳታፊ እንዲሆኑ ታሪካዊ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ በአገራዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይም በቀጥታም በተዘዋዋሪም በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡ ከዚህ ባሻገርም ዜጎች መብቶቻቸውንና ጥቅሞቻቸውን የሚያስከብርላቸው ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችሏቸውን ተቋማት ነጻ መሆናቸውና ገለልተኝነታቸው እንዲረጋገጥ መንግሥት በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

ይህ የለውጥ ሂደት ተጀምሯል፤ ነገም ይቀጥላል፡፡ በርግጥ አልፎ አልፎ ከለውጡ ጋር የማይጣጣሙ ወቅታዊ ጉዳዮች በአንዱ ወይ በሌላ ወገን ሊፈጸሙ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ መንግሥት የፖለቲካ ልዩነቶችን በሰላማዊ፤ በሕጋዊ መንገድ የመፍታት አቋምና እርምጃዎችን ለማስተጓጎል በሕዝብ መሀል ተሰግስገው ግጭቶችና ትንኮሳዎች በየአካባቢው ለማቀጣጠል ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፤ መንግሥትንም ወደማይፈልገው ወታደራዊ መፍትሄ እየጎተቱት ይገኛሉ፤ ጊዚያዊ የጸጥታ ችግሮች በሰላማዊና በፖለቲካዊ ድርድር እልባት ቢያገኝ ወይም በወታደራዊ ዘመቻዎች መንገድ ቢፈታ የለውጥ ሂደቱ ግን ፈለጉን አይለቅም፡፡ ትላንት በታላላቅ መንግሥታዊ የልማት ፕሮጀክቶች ስም ኢትዮጵያ ያላት የተፈጥሮና የካፒታል ሀብት ያለተጠያቂነት ሲመዘበር ቆይቷል፡፡ በተለይ የልማት ኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ከእቅዳቸው አንስቶ እስከአፈጻጸማቸው በውሸት ሪፖርት ተጀቡኖ የሕዝቦች ላብና ድካም የጥቂት ግለሰቦች ሀብት ማካበቻ ሆኖ ትውልድን ተስፋ እንዲቆርጥ አድርጓል፡፡

ትላንት የመንግሥት ሥልጣንን ተገን ያደረገ የፋይናንስ ሸፍጥና ዓይን ያወጣ የኮንትሮባንድ ንግድ አገሪቷን ራቁቷን አስቀርቶ ሲያበቃ ለአገር ውስጥና ለውጭ እዳ ዳርጓታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሥራ አጥነት እንዲስፋፋ፤ የኑሮ ውድነት እንዲባባስ፤ የዋጋ ንረት እንዲጦዝ ምክንያት ሆኗል፡፡ ዛሬ የመንግሥትን ሥልጣን ከለላ በማድረግና የሕዝብን አደራ በመብላት በልማት ሥም መዝረፍ አይቻልም፡፡ ከዚህ በፊት በአገር ሀብት ዝርፊያ የተጠረጠሩም ሥርዓቱን ጠብቆ በሕግ ፊት እንዲቆሙ ተደርገዋል፡፡ ያለ ሕግ አግባብ የተያዙ የሕዝብ ሀብቶችም እንዲመለሱ በመደረግ ላይ ነው፡፡ ዛሬ በዋናነት ሥራ አጥነትን መቅረፍ፤ የዋጋ ንረትን ማረጋጋትና የውጭ ምንዛሬ እጥረትን መቅረፍ ዓላማው ያደረገ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለውጥ (Economic Reform) ተቀርጾ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡

ይህ የለውጥ ሂደት ታስቦበት ተጀምሯል፤ ነገም ያለማቋረጥ ይቀጥላል፡፡ በርግጥ የታቀዱም ያልታቀዱም ከለውጡ ጋር አብረው የማይሄዱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችና ዝንባሌዎች ይኖራሉ፤ በተለይ ሆን ተብለው በየድንበሩና በየአውራ ጎዳናው ግጭት በመፍጠር የሚፈጸሙት የንግድና የፍጆታ ሸቀጥ አሻጥሮችና ሰሞነኛ ግርግሮች መከሰታቸው እየታየ ነው፤ መንግሥት የጀመረው ዘላቂ የለውጥ ሂደት ግን ፈለጉን አይለቅም፡፡ ትላንት በኢትዮጵያና በኤርትራ መንግሥታት መካከል በነበረው የባላንጣነት ግንኙነት ምክንያት የአፍሪካ ቀንድ በቀውስና ባለመረጋጋት ውስጥ ተዘፍቆ እንደቆየ ይታወቃል፡፡ በሁለቱ አገራት መካከልም በነበረው አስከፊ ጦርነት ሰበብ በአስር ሺዎች መተኪያ የሌለ ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ አካላቸው ጎድሏል፤ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ይባስ ብሎም የእልቂት አደጋ ተጋርጦባቸው ኑሮአቸውን “በሞት አልባ ጦርነት” በስጋትና በሰቀቀን ሲመሩ ቆይተዋል፡፡ ዛሬ ይህ አሉታዊ ሁኔታ በአፍሪካ ቀንድ እንዲቀየር ወሳኝ ምዕራፎች ተጀምረዋል፤ ሕዝቦቹም ተስፋቸው እየለመለመ ነው፡፡ ይህ የለውጥ ሂደት ተጀምሯል፤ ነገም ይቀጥላል፡፡ በርግጥ በቀጠናው ውስብስብነት የተነሳ አልፎ አልፎ ደራሽ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ፤ ሂደቱ ግን ፈለጉን አይለቅም፡፡

እውነታውና ጠቅላላ ሥዕሉ ይህ ሆኖ እያለ መንግሥት የተያያዘውን የለውጥ ሂደት በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ በዕለታዊና ሰሞናዊ አውድ ውስጥ ብቻ ተመልክቶ በጥርጣሬ የመጓዝ አዝማሚያ እንዳለ መንግሥት በአንክሮ ተመልክቶታል፡፡ በዚህ ረገድ በየዕለቱና በየሰሞኑ በሚፈጠሩ አልፎ ሂያጅ ኹነቶች ምክንያት ጊዚያዊ የፈንጠዝያ ስሜት ወይም ዕለታዊ የተስፋ መቁረጥ ድባብ አልፎ አልፎ ሲፈጠር ተመልክቷል፡፡ ይህ ዝንባሌ በርግጥ ቢያንስ ሶስት ምክንያቶች አሉት፡፡

በአንድ በኩል የለውጥ ሂደቱን ለማደናቀፍ ቀን ከሌሊት በተገኘው አጋጣሚ ጥረት የሚያደርጉ ኃይሎች በሕዝብና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ተሰግስገው በሚፈጥሩት የለየለት ጦርነት፤ ሁከትና የኢኮኖሚ አሻጥር ምክንያት ሰላማዊና ልማታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲስተጓጎሉ በማድረጋቸው የሚፈጠር ጊዜያዊ ሁኔታ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር መንግሥት ሁሉንም ሰላማዊና ሕጋዊ አማራጮች ሁሉ አሟጦ ከተጠቀመ በኋላ በቂና ተመጣጣኝ አስተዳደራዊ፤ ሕጋዊና ወታደራዊ እርምጃ በመውሰድ ላይ እንደሚገኝና ይህንንም አጠናክሮ የሚቀጥልበት እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡

ሁለተኛው ምክንያት የለውጥ ሂደቱን መሬት በማውረድ ጥረት ውስጥ የሚኖር ድካምና ልፋትን የማይሹ የተወሰኑ ልፍስፍስ ወገኖች በእቅድና በሪፖርት ሰበብ በዘዴ ለመጀቦን በመምረጣቸው በሚፈጠር የሥራ ክፍተት ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ በእቅድና በሪፖርት የመጀቦን አባዜ ጥቂት በማይባሉ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ የኖረና የከረመ የአንዳንድ ኃላፊዎችና የሠራተኞች አክሳሪ ጠባይና ግብር እንደሆነ መንግሥት ይረዳል፡፡ መፍትሔውም በያቅጣጫው በሥራ እየገፉ መቀጠል እንደሆነም ያምናል፡፡ መንግሥት የሚታገለው የጦርነትና የሁከት መወራጨቶችን፤ የኢኮኖሚ ምዝበራን፤ የሸቀጦችን አሻጥር፤ የሰብዓዊና ዲሞክራሲዊ መብቶች ገፈፋ ብቻ ሳይሆን በ“አሠራር” ሥም የተሸሸገን ቢሮክራሲያዊ ትብታብንም (Bureaucratic Red-Tape) ጭምር ነው፡፡

ሶስተኛው ምክንያት ደግሞ የለውጡን ትልቅ ሥዕል (Bigger Picture) እና ታሪካዊ ስፍራውን ማየት ካለመቻል የተፈጠረ እንደሆነ ይገመታል፡፡ የለውጡን ትልቅ ሥዕል ሥንመለከት ዜጎች በተለይ በኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ያለ ሞግዚት ጣልቃ ገብነት ራሳቸው ስለራሳቸው የመወሰን ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ መድረሳቸውን እናያለን፡፡ እዚህ ምዕራፍ ላይ ለመድረስ ግን ሕዝቦች በሁሉም የአገሪቱ ማዕዘኖች በድምሩ ከሀምሳ ዓመታት በላይ የወሰደ አኩሪ መስዋእትነት የተሞላበት ትግል አካሂደዋል፡፡ እናም የለውጡ ዋጋ ይህንን አንጸባራቂ የዜጎችና የሕዝቦች የዘመናት ገድል ይጨምራል፡፡

መንግሥት የለውጡን ሂደት ተከታታይ ትውልዶች በትግላቸው ከደረሱበት ከዚህ ታሪካዊ ምዕራፍ አንጻር በመመልከትና ትልቅ ሥዕልነቱን በመቀበል ያለበትን ሕዝባዊ ኃላፊነት በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡ ትላንት የት ነበርን? ወዴትስ እየሄድን ነው?” ለሚሉ ጥያቄዎች መልስ የሚሆነው መንግሥት የተያያዘው የለውጥ ሂደት የራሱ የሆነ መነሻና መድረሻ እንዳለው አስረግጦ ሂደቱ ፈለጉን እንደማይለቅ በተግባር ማሳየት ነው፡፡

ለየትኛውም ፖለቲካዊ አለመግባባትና ልዩነቶች መንግሥት ወታደራዊ አማራጭ መፍትሔ ነው ብሎ አያምንም፡፡ ይልቁንም ለሕጋዊና ሰላማዊ መፍሔዎች ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ ይህ የጸና የለውጥ አቋሙንና እርምጃዎቹን ተከትሎም የተረጋጋ አገራዊ ኢኮኖሚ በመገንባት እና የፖለቲካ ምህዳርን በማስፋት የዜጎችን እና የሕዝቦችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዲሁም የሰብአዊና የዲሞክራሲያዊ መብቶች የማስከበር ግብ አስቀምጧል፤ እየሠራበትም ነው፡፡

ከዚህ አንጻር የለውጥ ሂደቱ አንድ አካል የሆኑት የፖሊሲዎች፤ የአዋጆች፤ የደንቦች፤ የመመሪያዎችና የእቅዶች ፍተሻና ክለሳ በሚፈለገው መልኩ እየተፈጸመ ነው፡፡ ይሁንና የለውጡ ሂደት በፖሊሲ፤ በሕግና በእቅድ ማዕቀፎች ብቻ ውጤታማ ሊሆን አይችልም፡፡ ሥራ ይፈልጋል፡፡

የሥራ ቅድመ ሁኔታ ደግሞ ሰላምና ጸጥታ ነው፡፡ ይህን ለሥራ ብቻ ሳይሆን ለዜጎች ደህንነት ሲል በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ማረጋገጥ የመንግሥት ኃላፊነትና ግዴታ እንደሆነ ከቶም ቢሆን የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም አንዳንድ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተጨባጭ ሥራዎችን ሳይሰሩ ሥለ እቅድና ሪፖርት መለፈፋቸውን ቢቀጥሉ ለውጡን ያደነዝዘዋል እንጂ የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ መንግሥት በየእርከኑ ካሉ ኃላፊዎችና ሠራተኞቻቸው የሚጠብቀው ተጨባጭ ሥራ እንጂ የወንበር ማቆያ ቃለ መሃላ አይደለም፡፡

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram