fbpx
AMHARIC

የብልት ኪንታሮቶች ምንድንናቸዉ?

የብልት ኪንታሮቶች ከቆዳ የሚነሱ ትንንሽ እንክብል ነገሮች ሲሆኑ በሴት ብልት፣ በወንድ ብልት ወይም በፊንጢጣ አከባቢ ይወጣሉ። የብልት ኪንታሮቶች ሂዮማን ፓፒሎማ ቫይረስ ወይም (ኤችፒቪ) በተባለ ቫይረስ ኢንፌክሽን ምክኒያትየሚከሰቱ ናቸው። የቫይረሱ ዋና መተላለፍያ መንገድ የግብረ ስጋ ግንኙነት ቢሆንም በመነካካት እና በመተሻሸትም ሊተላለፍ ይችላል።
ሂዮማን ፓፒሎማ ቫይረስ ወይም (ኤችፒቪ) አደገኛ ነውን?
አብዛኛውን የብልት ኪንታሮት አይነት የሚያስከትሉ የኤችፒቪ ዓይነቶች አብዛኛውን ጊዜ አደገኛ አይደሉም። ሌሎች የኤችፒቪ አይነቶች ግን የማህጸን በር ካንሰር፣ የወንድ ብልት ካንሰር ወይም የፊንጢጣ ካንሰር ሊያስከትሉ ይችላሉ ።
የብልት ኪንታሮቶች የህመም ሰሜት አላችው ?
አብዛኛዎቹ የበሽታው ተጠቂዎች በብልትና በፊንጢጣቸው አከባቢ ኪንታሮት ከመኖሩ በስተቀር ብዙውን ጊዜ የህመም ስሜት የላቸውም። አንዳንድ ሰዎች ግን የማሳከክ ፣ የማቃጠል ወይም የህመም ሰሜት ይኖራቸዋል።
ኪንታሮት መሆኑ ለማወቅ ምርመራ ያስፈልጋል?
አይ ምንም ምርመራ አያስፈልግም ። ሐኪም ወይም ነርስ እንዲሁ በማየት ኪንታሮት መሆኑን መናገር ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ ከኪንታሮቱ ትንሽ ናሙና (ባዮፕሲ) በመውሰድ ሊመረምሩ ይችላሉ። አብዛኛውን ጊዜ ግን አስፈላጊ አይደለም።
በሽታው ከቂጢኝ ለመለየት እና ሌሎች የአባላዘር በሽታዎች አለመኖራቸው ለማጣራት የደም ምርመራ ሊደረግ ይችላል።

የብልት ኪንታሮቶች እንዴት ይታከማሉ?
● በመድሃኒት
ኪንታሮቶችን ለማስወገድ የሚረዱ ብዙ መድሃኒቶች አሉ። አንዳንዶቹ መድሃኒቶች ቀስ በቀስ ኪንታሮቶቹን በማጥፋት ይሰራሉ ፤ ሌሎቹ ደግሞ የሰውነት በሽታን የመከላከያ ዘዴ በማጠናከር ኪንታሮቶችን በማጥቃት ይሰራሉ።
አብዛኛዎቹ መድሃኒቶች በክሬም ፣ በቅባት ወይም በፈሳሽ መልክ የተዘጋጁ ናቸው። ለበርካታ ሳምንታት በሳምንት አንድ ጊዜ ወይም ከዚያ በላይ ኪንታሮቶቹን ብቻ ለይቶ በስንጥር መቀባት ያስፈልጋል። አንዳንድ መድሃኒቶች በሀኪም ወይም በነርስ መቀባት አለባቸው።
● በቀዶ ጥገና
በመድሃኒት ያልጠፉ ፣ በጣም ትልቅ የሆኑ ወይም በጣም ብዙ ኪንታሮቶች ያላቸው ሰዎች ፤ ኪንታሮቶቹ በቀዶ ጥገና እንዲወገዱ ሊደረግ ይችላል። ይህ በተጨማሪም ካንሰር ሊሆኑ የሚችሉ ኪንታሮቶች ላላቸው ሰዎችም የተሻለ አማራጭ ነው።
ሌሎች የብልት ኪንታሮቶች የህክምና አማራጮች የሚከተሉትን ያጠቃልላሉ
● ክራዮቴራፒ
● ኤሌክትሮኮተሪ
● ላሰር ስርጀሪ
● አልትራሳውንድ ሰርጀሪ
እርጉዝ ከሆንኩስ?
እርጉዝ ከሆኑ የብልት ኪንታሮቶች መድሃኒት ከመውሰድዎ በፊት ለሐኪምዎ መንገርዎን ያረጋግጡ ፤ አንዳንድ መድኃኒቶች በእርግዝና ወቅት ጥቅም ላይ የሚውሉ ሲሆኑ ሌሎቹ ግን አይደሉም።
ህክምናው ከጨረስኩኝ በኋላስ?
ህክምናው ከጨረሱ በኋላ ምንም አይነት ኪንታሮት ማየት ባይችሉም እንኳ የበሽታው አምጪ ቫይረስ (ኤችፒቪ) በሰውነትዎ ሊኖር እንደሚችል ማወቅ ይኖርብዎታል።
ይህ ማለት ኪንታሮቶቹ በማንኛውም ጊዜ ተመልሰው ሊመጡ ይችላሉ ማለት ነው። ኪንታሮቶቹ ተመልሰው ከመጡ ለሌላ ሰው ሊያስተላልፉ ይችላሉ።
የብልት ኪንታሮቶችን እንዴት መከላከል ይቻላል?
● የኤችፒቪ ክትባት መውሰድ
ነገር ግን ክትባቶች ሊከላከሉ የሚችሉት ኪንታሮቶቹ ከመውጣታቸው በፊት ከተወሰዱ ብቻ ነው።
● በኤችፒቪ በሽታ ከተያዘ ሰው ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነት ሳይፈጽሙ ራስዎን መጠበቅ
ነገር ግን ይሄ ከባድ ነው ምክንያቱም ሰዎች ሁልጊዜ ቫይረሱ እንዳለባቸው አይገነዘቡም
● ኮንዶም መጠቀም በኤችፒቪ የመያዝ ስጋትን ለመቀነስ ይረዳል ፤ ነግርግን ሙሉ በሙሉ አይከላከልም። ምክንያቱም ቫይረሱ እና ኪንታሮቶቹ በኮንዶም የማይሸፈኑ ቆዳዎች ላይ ሊኖሩ ስለሚችሉ ነው።

ዶ/ር መስፍን ገ/እግዚአብሔር
ጆይ የጽንስና የማህጸን ልዩ ክሊኒክ
አድራሻ:- ቀበና ኮከበጽባሕ ት/ቤት ፈትለፊት

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram