fbpx

የባንኮች ተቀማጭ ሂሳብ ከ688 ቢሊየን ብር በላይ ደርሷል-ብሔራዊ ባንክ

በኢትዮጵያ የባንኮች አጠቃለይ ተቀማጭ ሂሳብ ከ688 ቢሊን ብር በላይ መድረሱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገለጸ።

በባንኩ የገንዘብና ፋይናንስ ትንተና ዳሬክተር አቶ ሙሉነህ አያሌው እንዳሉት፥ የባንኮችን ተቀማጭ ሒሳብ ለማሳደግ የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደዋል።

የባንኮችን አገልግሎት ተደራሽነት ለማስፋት ከተወሰዱ እርምጃዎች ውስጥም አንዱ መሆኑን ያስቀምጣሉ።

ቆጣቢዎች የሚያገኙትን የወለድ ጥቅም ለመጨመር የወለድ መጠን ከ5 በመቶ ወደ 7 በመቶ ከፍ ማድረጉ ሌላኛው ምክንያት ነው ይላሉ።

በዚህም እስከ መጋቢት 2010 ዓ.ም ድረስ በአገሪቷ የባንኮች አጠቃለይ ተቀማጭ ሒሳብ ከ688 ቢሊየን ብር በላይ መድረሱን ነው የሚናገሩት።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ከ529 ቢሊየን ብር በላይ እንደነበር አስታውሰው፤ በዚህ ዓመት 30 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

ባንኮች ከቁጠባ የሚሰበስቡትን ገንዘብ ለተለያዩ ወጪዎች በብድር መልክ እንደሚሰጡም ይታወቃል።

በመሆኑም የሚሰበስቡት ተቀማጭ ሒሳብ ሲያድግ የማበደር አቅማቸው ከፍ እንደሚል የዘርፉ ምሁራን ያስቀምጣሉ።

እስከ ተጠቀሰው ጊዜም በባንኮች የተሰጠው የብድር ክምችት መጠን ከ646 ቢሊየን ብር በላይ መድረሱንም ነው አቶ ሙሉነህ የገለጹት።

ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ22 ነጥብ 6 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ 18 ባንኮች፣ 13 የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትና ከ18 ሺህ በላይ አነስተኛ የብድርና ቁጠባ ተቋማት እንደሚገኙ መረጃዎች ያሳያሉ።

 

ምንጭ፦ ኢዜአ

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram