fbpx
AMHARIC

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበርና የቦርድ አባላት ተከሰሱ

  • ክሱን በሥር ፍርድ ቤት ያዩት ዳኛ የዲሲፕሊን አቤቱታ ቀረበባቸው

ከፍትሐ ብሔር ሕግ አንቀጾች ድንጋጌና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር መመርያ ደንብ ውጪ፣ በሕገወጥ መንገድ ከአባልነታቸው መታገዳቸውንና መባረራቸውን የገለጹ አባላት ማኅበሩንና የቦርድ አባላቱን ከሰሱ፡፡

በማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብና በሕግ የተጣሉባቸውን መሠረታዊ ግዴታዎች በመተላለፍ የስፖርት ማኅበሩን የሚጎዱ ተግባሮችን ፈጽመዋል የሚል እምነት ስላደረባቸው ያሏቸውን ቅሬታዎች፣ አስተያየቶችና ሐሳቦችን ለቦርዱ በማቅረባቸው፣ ከማኅበሩ አባልነታቸው የታገዱትና ከዚያም በሕገወጥ መንገድ መባረራቸውን ‹‹ሕግን ያልተከተለና በሕግ ሊታረም የሚገባው ነው፤›› በማለት በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃና ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፍትሐ ብሔር ክስ የመሠረቱት አቶ ተስፋዬ ነጋሽ፣ አቶ ዳንኤል ካሳ፣ አቶ ታደሰ መሸሻና አቶ አንተነህ ፈለቀ ናቸው፡፡

የሥልጣን ዘመናቸው ካለፈ ከሁለት ዓመታት በላይ የሆናቸውና ቦርዱ ሳይሰበስብ እንደተሰበሰበ በማስመሰል፣ እንዲሁም ሥልጣን ሳይኖራቸው በጠሩት ጠቅላላ ጉባዔ ምልዓተ ጉባዔው ሳይሟላ ተሟልቶ ውሳኔ ያስተላለፈ በማስመሰል፣ ሕገወጥ ዕግድ በመጣልና ከማኅበሩ ከሳሽ አባላትን አባረዋል በማለት ክስ የቀረበባቸው ደግሞ፣ የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ አብነት ገብረ መስቀል፣ ዶ/ር ደምበል ባልቻ፣ አቶ ንዋይ በየነ፣ አቶ ካሳሁን በየነ፣ አቶ ታፈሰ በቀለ፣ ፕሮፌሰር እሸቱ ወንጨቆ፣ አቶ ኢሳያስ ሀደራ፣ አቶ ዓለማየሁ ኃይሌና አቶ ዳዊት ውብሸት ናቸው፡፡

ከሳሾች ለፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቂርቆስ ምድብ ሁለተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ባቀረቡት የክስ ማመልከቻ እንዳብራሩት፣ ከላይ ስማቸው የተጠቀሰው የቦርድ አባላት (ከአቶ ዳዊት ውብሸት በስተቀር) የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ሥራ አመራር ቦርድ የነበሩ ቢሆንም የማኅበሩን መተዳደሪ ደንብ ተላልፈዋል፡፡ ከዚህም ተጨማሪ ከአራት ዓመታት በላይ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ መጥራት ሲገባቸው አልጠሩም፡፡ አጠቃላይ የስፖርት ማኅበሩን የሥራ እንቅስቃሴ፣ ኦዲትና የወደፊት የሥራ ዕቅድ ለአባላቱ ሪፖርት ማቅረብ ቢኖርባቸውም አላቀረቡም፡፡ አቶ አብነትን ጨምሮ ሁሉም ተከሳሾች በ2006 ዓ.ም. የቦርድ አመራርነት ጊዜያቸው የተጠናቀቀ ቢሆንም፣ በሕገወጥ መንገድ እስከ ግንቦት 28 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ የቦርድ አመራር ሆነው ቀጥለዋል፡፡ ግንቦት 28 ቀን 2008 ዓ.ም. በሌላቸው ሥልጣን ጠቅላላ ጉባዔ በመጥራት የሥልጣን ዘመናቸውን ለአራት ዓመታት ማራዘማቸውንም በክሱ ጠቅሰዋል፡፡

በቦርድ ሰብሳቢው አቶ አብነት፣ በምክትል ሰብሳቢው ዶ/ር ደምበል ባልቻ፣ በጸሐፊው አቶ ንዋይ በየነና በቀሪዎቹ ተከሳሾች አባልነት የተዋቀረው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር የሥራ አመራር ቦርድ፣ የማኅበሩን መተዳደሪያ ደንብና በሕግ የተጣሉበትን ግዴታዎች መወጣት ባለመቻሉ፣ ክስ ያቀረቡት አባላት ጥያቄ ማንሳታቸውን ክሱ ያብራራል፡፡ የታገዱና የተባረሩ አባላት ቦርዱ ግንቦት 28 ቀን 2008 ዓ.ም. ስለሚያደርገው የቦርድ አባላት ተጨማሪ የሥልጣን ዘመን፣ የክለቡን ሥራ አስኪያጅ የመተዳደሪያ ደንብ መሻሻልን፣ የደጋፊ ማኅበርን፣ የክለቡን አደረጃጀትን የገቢ ምንጭ መፍጠርንና ስፖንሰርሺፕን በሚመለከት አጀንዳ እንዲያዝላቸው መጠየቃቸውን በዝርዝር አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን ቦርዱ በቡድንም ሆነ በተናጠል ከሳሾች ላቀረቧቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሳይሰጥ ከደንቡ ውጪ ስብሰባውን በማድረግ፣ ቦርዱ ለተጨማሪ አራት ዓመታት እንዲቀጥል አድርጓል፡፡ የ2007 ዓ.ም. ኦዲት ሪፖርትን ተቀብሎ በማፅደቅ መሠረታዊ የማኅበሩን ችግር ሳያነሳ እንዳለፈው በክሱ ብራርቷል፡፡

ጠቅላላ ጉባዔ ተደርጓል በተባለበት በሁለት ቀናት ውስጥ ግንቦት 30 ቀን 2008 ዓ.ም. የሥራ አመራር ቦርዱ ሳይሰበሰብ እንደተሰበሰበ በማስመሰልና ከሳሾች ተሰብስበው ለምን ጥያቄ አነሱ በሚል፣ የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ አብነት ከማኅበር አባልነታቸው እንዳገዷቸው በክሱ አብራርተዋል፡፡ አቶ አብነት፣ ‹‹ቦርዱ ተሰብስቦ ከሳሾች እንዲታገዱ ውሳኔ አስተላልፏል፤›› ከማለታቸው ውጪ፣ ሰኔ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ቦርዱ ተሰብስቦ ውሳኔ ስለማሳለፉ፣ ውሳኔ ስለመኖር አለመኖሩ፣ ውሳኔውን እነማን እንዳሳለፉትና የታገዱት (ከሳሾች) አባላት እነማን እንደሆኑ የቦርዱ አባላት እንደማያውቁ አክለዋል፡፡ የሥራ አመራር ቦርዱ ስብሰባ ቃለ ጉባዔ ለከሳሾቹ ሊሰጥ የሚገባ ቢሆንም፣ እንዳልተሰጣቸው አስረድተዋል፡፡ የቦርዱ ሰብሳቢም ሆኑ አባላቱ የሥራ ዘመናቸው ካለፈ ሁለት ዓመታት በላይ ስለሆነው መሰብሰብም ሆነ ማባረር የማይችሉ ቢሆንም፣ እነሱ ግን በሌላቸው ሥልጣን ሕገወጥ ተግባር መፈጸማቸውን ጠቁመዋል፡፡ የማኅበሩን ህልውና ለማስቀጠል ያስችላል ብለው ጥያቄና ሐሳብ በማቅረባቸውና አስተያየት በመስጠታቸው ምክንያት፣ ከማኅበር አባልነታቸው መታገዳቸው ያላግባብ መሆኑንና አጠቃላይ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት የፈጸሙት ተግባር፣ የማኅበሩን መተዳደሪያ ደንብና ሕግን የሚቃረን ስለሆነ፣ እንዲታረምላቸው ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል፡፡ የሥራ አመራር ቦርዱ ሰብሳቢ አቶ አብነት ሰኔ 3 ቀን 2008 ዓ.ም. የጻፉት ዕግድም እንዲሰረዝና የፈጸሙት ተግባር የሥልጣን ዘመናቸው ካለፈ በኋላ በመሆኑ ሕገወጥ ነው እንዲባልላቸው ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ የቦርዱ ሰብሳቢም በአጭር ጊዜ ጠቅላላ ጉባዔ ጠርተው ገለልተኛ ባለሙያ በመሾም፣ ከሳሾች የታገዱበት ምክንያት አግባብ ለማኅበሩ ጠቅላላ ጉባዔ በአጀንዳነት ቀርቦ ያለምንም ተፅዕኖና ጣልቃ ገብነት ግልጽ ውይይት ከተደረገ በኃላ፣ ጠቅላላ ጉባዔው ውሳኔ እንዲሰጥ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸውና በሌሎች ጉዳዮችም ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡

የቀረበለትን የፍትሐ ብሔር ክስ የመረመረው የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቂርቆስ ምድብ ሁለተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት፣ ሁለቱን ወገኖች አከራክሯል፡፡ ከሳሾች ከላይ የተዘረዘረውን ክስ ሲያቀርቡ፣ ተከሳሾች ደግሞ ባቀረቡት መቃወሚያ በከሳሾች ላይ የወሰዱት ዕርምጃ በግላቸው ሳይሆን ማኅበሩን ወክለው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ያስተላለፉትም የዲሲፕሊን ቅጣት በመሆኑ የተላለፈው ቅጣት የሚፀናው ወይም ውድቅ የሚደረገው፣ በማኅበሩ ጠቅላላ ጉባዔ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ጠቅላላ ጉባዔውም ገና ስላልተደረገ ከሳሾች ክስ ለመመሥረት የሚያስችላቸው የክስ ምክንያት የላቸውም ብለዋል፡፡ በመሆኑም ጉዳዩም በፍርድ ቤት ሊታይ የሚችል ባለመሆኑ፣ የማየት ሥልጣን የለውም ብለው ተከራክረዋል፡፡ በተጨማሪም ቅጣት በተጣለባቸው አንድ ወር ውስጥ እንዲሻርላቸው ስላልጠየቁም፣ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 448(2) መሠረት በይርጋ የታገደ መሆኑን በመግለጽ፣ መዝገቡ እንዲዘጋ ጠይቀዋል፡፡ ጣልቃ ገብቶ የተከራከረው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበርም ተመሳሳይ መልስ ሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ አራት ጭብጦችን ማለትም ከሳሾች ክስ ለመመሥረት መብትና ጥቅም አላቸው? የላቸውም? የክስ ምክንያት አለ? ወይስ የለም? ፍርድ ቤቱ ክሱን የማየት ሥልጣን አለው? የለውም? እና ክሱ በይርጋ ሊታገድ ይገባል? ወይስ አይገባም? በማለት መርምሮ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ለጭብጦቹ የተለያዩ ብይኖች ሰጥቷል፡፡ የቦርዱ አባላት የምርጫ በማለፉ ያላግባብ በተከሳሾች ላይ ያሳለፉት የዕግድ ውሳኔ አሳማኝ ካልሆነ፣ የሥራ አመራር ቦርዱ ውሳኔ ሊሻር ወይም ሊፀና ይችላል፡፡ ይኼ የሚሆነው ደግሞ ሕጋዊ የሆነ ጠቅላላ ጉባዔ ሲኖር ነው፡፡ በውሳኔው ላይ ቅር የተሰኘ የማኅበር አባል ወደ ፍርድ ቤት መሄድ እንደሚችል ደግሞ፣ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 448(1) ላይ ተደንግጓል፡፡ በመሆኑም ከሳሾች የቀረበባቸውን ዕግድ ማፅደቅና መሻር የሚችለው ጠቅላላ ጉባዔው በሚሰጠው ውሳኔ መሠረት መሆኑን ፍርድ ቤቱ ገልጾ፣ ጠቅላላ ጉባዔው ገና ስላልተሰበሰበ ከሳሾች ጉባዔው እስከሚካሄድ ድረስ ክስ ማቅረብ እንደማይችሉ ገልጾ፣ ክሱን ዘግቶታል፡፡ በሌሎቹ ጭብጦች ላይ ብይን ሰጥቶ፣ ከሳሻቹ ‹‹ጠቅላላ ጉባዔ ይጣራልን፤›› በማለት ባቀረቡት አማራጭ የዳኝነት ጥያቄ ላይ፣ ግራ ቀኙን ለማከራከር ለጥቅምት 13 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱ ለክርክር ለጥቅምት 13 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቶ እያለ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ቦርድ ጠቅላላ ጉባዔ ለማድረግ ለመስከረም 14 ቀን 2010 ዓ.ም. ጥሪ አድርጓል፡፡ ከሳሾች ጠቅላላ ጉባዔው መጠራቱን ባይቃወሙም፣ እነሱ የታገዱበት ምክንያት በጠቅላላ ጉባዔው ላይ በአጀንዳነት እንዳይቀርብ ለፍርድ ቤቱ መቃወሚያ በማቅረብ እንዲታገድላቸው ጠይቀዋል፡፡ ነገር ግን ወቅቱ ፍርድ ቤቶች ዕረፍት ላይ የነበሩበት ጊዜ በመሆኑ፣ የዕግድ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ተከሳሾች ያቀረቡትን አቤቱታ የተመለከቱት የቂርቆስ ምድብ ሁለተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ዳኛ፣ ‹‹በተዘጋ ነጥብ ላይ የዕግድ ጥያቄ ማቅረብ አይቻልም፤›› በማለት አቤቱታቸውን ውድቅ በማድረጋቸው የሥራ አመራር ቦርዱ ጠቅላላ ጉባዔውን አድርጎ ዕግዱና ማባረሩ እንዲፀና ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም ከሳሾች የዳኛዋን ስም ጠቅሰው የዲሲፕሊን ጥሰት መፈጸማቸውን በመግለጽ፣ ለፌዴራል ዳኞች አስተዳደር የዲሲፕሊን ክስ አቅርበው ውሳኔ እየተጠባበቁ ነው፡፡

በሌላ በኩል ለቂርቆስ ምድብ ሁለተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ባቀረቡት ክስ ላይ ከሳሾች የጠየቁት ዳኝነት ውድቅ መደረጉን ተከትሎ፣ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ፍትሐ ብሔር ችሎት በአዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 13 መሠረት ይግባኝ ማቅረባቸውንና ፍርድ ቤቱም ክሱን መርምሮ ያስቀርባል በማለት ለክርክር ለሚያዝያ 10 ቀን 2010 ዓ.ም. መቅጠሩን ሰነዶች ያሳያሉ፡፡ በተመሳሳይ የስፖርት ማኅበሩ ከአባልነት ማሰናበቱ ሕገወጥ ድርጊት መሆኑን በመግለጽና ጠቅላላ ጉባዔው መስከረም 14 ቀን 2010 ዓ.ም. ተሰብስቦ ከሳሾችን ከማኅበሩ መሰናበት ያፀደቀ ስለሆነ፣ ለቂርቆስ ምድብ ችሎት በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 424 መሠረት በፍርድ እንዲሻርላቸው ክሳቸውን አሻሽለው በማቅረባቸው፣ ለመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡ በቀረበው የከሳሾች ወደ አባልነት የመመለስ ጥያቄ የሥር ፍርድ ቤት ለማየት ሥልጣን የሌለ ስለመሆኑ፣ በድጋሚ የቀረበ ክስ ስለመሆኑ፣ ክሱ በይርጋ የታገደ መሆኑንና አባላቱ ከማኅበሩ የተሰናበቱት በሕጉ አግባብ ስለመሆኑ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር በጠበቃው አማካይነት ዝርዝር ምላሽ ለቂርቆስ ምድብ አንደኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ሰጥቷል፡፡

 

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram