fbpx
AMHARIC

የቀድሞ የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊ ከእስር ተፈቱ

ታምሩ ጽጌ

በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊና አማካሪ የነበሩት አቶ ወልደ ሥላሴ ወልደ ሚካኤል፣ የእስር ጊዜያቸውን አጠናቀው ተፈቱ፡፡

በሙስና ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ በእስር ላይ የነበሩት አቶ ወልደ ሥላሴ፣ ተፈርዶባቸው የነበረውን የእስራት ቅጣት አጠናቀው ከእስር የተፈቱት ከሁለት ሳምንት በፊት ነው፡፡

አቶ ወልደ ሥላሴ ደንቡን ተከትሎ ፈቃድ ከሚሰጥ አካል ፈቃድ ጠይቀው መያዝ ሲገባቸው ሳያስፈቅዱ ታጣፊ ክላሽ፣ ኡዚ ጠብመንጃና የጭስ ቦምብ በቤታቸው ውስጥ አስቀምጠው በመገኘታቸው፣ ተመድበው ይሠሩበት ከነበረው መሥሪያ ቤት ይከፈላቸው ከነበረው ደመወዝ ጋር የማይጣጣም በ175 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ባለ ሦስት ፎቅ ሕንፃ ገንብተው በ50 ሺሕ ብር አከራይተው በመገኘታቸውና ‹‹ሽብርተኝነት በአፍሪካ ቀንድ›› የሚል መጽሐፍ ጽፈው ድርጅቶችና ግለሰቦች በግዳጅ እንዲያሳትሙላቸውና መጽሐፉንም እንዲወስዱ በማድረግ፣ የመንግሥትን ተሽከርካሪና ነዳጅ በመጠቀም ግለሰቦችን ወደ ተለያዩ ክልሎች መላክ የሚሉ ክሶች ቀርበውባቸው ሰፋ ያለ ክርክር ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

አቶ ወልደ ሥላሴ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበባቸውን ክስ በሰነድና በምስክሮች የተከላከሉ ቢሆንም፣ የቀረበባቸውን ክስ ሊያስተባብሉ እንዳልቻሉ ተገልጾ፣ ጥፋተኛ መባላቸውና በሥር ፍርድ ቤት በአሥር ዓመታት እስራት እንዲቀጡ ተወስኖባቸው ነበር፡፡

የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ በመቃወም ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብለው የእስር ቅጣቱ ወደ ሰባት ዓመታት ተቀንሶላቸው ነበር፡፡ በመሆኑም አቶ ወልደ ሥላሴ ከአራት ዓመታት በላይ በእስር በማሳለፋቸው፣ በማረሚያ ቤት የነበራቸው ባህሪና ሌሎች መሥፈርቶች ታይተው አመክሮ ስለተፈቀደላቸው እስራታቸውን አጠናቀው ከእስር ተፈተዋል፡፡

ከአቶ ወልደ ሥላሴ ጋር እህታቸው፣ ወንድማቸውና ሌላ ግለሰብ ተከሰው በነፃ መሰናበታቸው አይዘነጋም፡፡

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram