fbpx

የሶማሌ ያገር ሽማግሌዎች መንግሥትን እየተማጸኑ ነው

የሶማሌ ክልል የአገር ሽማሌዎች አቤቱታቸውን ለኢትዮጵያ መንግሥት ለማቅረብ አዲስ አበባ ገብተዋል። በክልሉ ተንሰራፍቷል ስላሉት ሙስና፤ በሕዝቡ ላይ ይደርሳል ያሉትን በደል ለኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና ለጠቅላይ አቃቤ ሕግ ፅህፈት ቤት አቤቱታ ማቅረባቸውን ተናግረዋል። የተቃውሞ አራማጆች በበኩላቸው አሁንም ግድያና እስር ቀጥሏል ሲሉ ተናግረዋል።

የጅጅጋው ሱልጣን አብዱራህማን እና አደም አላሌ አሊ ጨምሮ ከሶማሌ ክልል ወደ አዲስ አበባ የዘለቁ የአገር ሽማግሌዎች ለጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ አቤቱታቸውን ለማቅረብ እየተጠባበቁ ነው። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ያገር ሽማግሌዎች እንደሚሉት በቁጥር ከ150 በላይ ይሆናሉ። ሱልጣን አብዱራህማን አቤቱታቸውን ለኮማንድ ፖስቱ ፤ለመከላከያ ሚኒስቴር እና ለፌድራል ጠቅላይ አቃቤ-ሕግ ፅህፈት ቤት ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

ካለፉት ሶስት ሳምንታት ወዲህ ተቃውሞ ከተጫነው የሶማሌ ክልል የተውጣጡት የአገር ሽማግሌዎች በክልሉ እስራት እና ግድያ በዝቷል፤ ሙስና እና የመልካም አስተዳደር እጦትም በርትቷል የሚል ሮሮ አላቸው። ካገር ሽማግሌዎቹ መካከል አንዱ የሆኑት አቶ አደም አላሌ አሊ ለችግሮቹ የክልሉ ርዕሰ-መሥተዳድር አቶ አብዲሙሀመድ ኡመር እና የሚመሩትን መንግሥት ተጠያቂ ያደርጋሉ። “ቅሬታችን ብዙ ነው። ክልል አምስትን የሚመሩት አብዲ ዑመር የክልሉ ፕሬዝዳንት ብቻ አይደሉም። የክልሉ ንጉስ ነው። የክልሉ ፋይናንስ ኃላፊ ነው። የክልሉን ሥራ በሙሉ የሚያዙት እርሳቸው ናቸው” ሲሉ ይናገራሉ። ከ10,000 በላይ የክልሉ ነዋሪዎች በኦጋዴን እስር ቤት እንደሚገኙ የሚናገሩት አቶ አደም “እኛ ተበድለናል። ችግር ውስጥ ነን። ሕዝባችንን እየገደሉት ነው። በክልል አምስት የተጀመረው እንቅስቃሴ በሽንሌ ዞን ነው የተጀመረው። ይኸ እንቅስቃሴ የአብዲ ኢሌ አስተዳደር አንፈልግም። አብዲ ኢሌ ይሒድልን የሚል ነው” ሲሉ ያስረዳሉ።

የሶማሌ ክልል ያገር ሽማግሌዎች ከአዲሱ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ብርሐኑ ጸጋዬ ባለፈው አርብ ተገናኝተው ሲመክሩ በቀብሪ ደሓር ከተማ ተፈጽሟል የተባለው ግድያ ተጨማሪ ውጥረት ፈጥሯል። ታያሲር ኦመር ፎድ መሐመድ የተባለችው ወጣት በክልሉ ልዩ ፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋለችው ፎቶ ግራፍ አንስተሻል በሚል ውንጀላ እንደሆነ የክልሉን ተቃውሞ  የሚከታተሉት ሻለቃ አሊ ሰሜሪ ይናገራሉ። ሻለቃ አሊ እንደሚሉት በቀብሪ ደሓር ከተማ የቀበሌ 05 ሰራተኛ የነበረችው ወጣት ባለፈው አርብ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ገደማ ተገድላ ተገኝታለች።

አቶ አደም አላሌ አሊ በበኩላቸው “የእርሷ አጎት እኛ ጋ እዚህ አዲስ አበባ ነው ያለው። የተቃወሙት ሽማግሌዎች ውስጥ ነው። በዚያ ምክንያት ነው ልጅቷን የገደሉት” ሲሉ የክልሉን መንግሥት ተጠያቂ ያደርጋሉ።

የወጣቷ ሞት ከተሰማ በኋላ ቀብሪ ደሓርን ጨምሮ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ቁጣ ቀስቅሷል። ሻለቃ አሊ ሰሚሬ “ሕዝቡ በዛ ተናደደ። ሰላማዊ ሰልፍ አደረገ። ከ400 በላይ ሰዎች ነበር የታሰሩት። ከ60 በላይ ሰዎች ተደብድበዋል። በዱላ እና በጥይት ጉዳት ደርሶባቸዋል። ከእነዛም ውስጥ ሐሰን የሚባለው ሰው ቅዳሜ ለት ሊሞት ችሏል” ሲሉ አስረድተዋል። በሽንሌ፣ ቶጎ ውጫሌ፤ ሐረሮች ተቃውሞዎች እንደነበሩ ያገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውንም አክለው ገልጸዋል።

ለአቤቱታ ወደ አዲስ አበባ ከዘለቁት የአገር ሽማግሌዎች ጋር የተገናኙት የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ብርሐኑ ጸጋዬ አቤቱታውን የሚያጣራ “ኮሚቴ እልካለሁ” ሲሉ ቃል እንደገቡላቸው ሱልጣን አብዱራህማንን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር አዲሱ ገብረእግዚዓብሔር በበኩላቸው “አቤቱታው ደርሶናል። በተቻለ መጠን በአጭር ጊዜ ለመጨረስ መርማሪዎች ወደ ሥፍራው ተንቀሳቅሰዋል” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ዶክተር አዲሱ ማመልከቻው ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከደረሰ አንድ ሳምንት እንደማይሞላው ገልጸው ምርመራው እንደተጠናቀቀ “ከሚመለከተው አካል ጋር እንነጋገርበታለን” ሲሉም አክለዋል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ – DW 

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram