“የሶማሌን ህዝብ ያስጨፈጨፉት አባይ ጸሃዬና ጀነራል ኳርተር ናቸው፡፡” ክቡር አቶ ሙስጠፌ ሙህመድ ኡመር የሶማሌ ክልል ም/ፕሬዘዳንት

  • ሁለቱ የሶማሌ ህዝብ ዘላለማዊ ጠላት ናቸው
  • 100 ሺ ሄክታር መሬት በመከላከያ ባለስልጣነት ተወስዷል

በሶማሌ ክልል ባለፈው አመት ሃምሌ በተፈጠረ ከፍትኛ ግጭት በርካቶች ህይወታቸው አልፏል፡፡ በማንነት ላይ ያነጣጠረ ከፍተኛ ጥቃት የደረሰ ሲሆን ሰዎች ከነህይወታቸው ተቃጥለዋል፣ ተደፍረዋል፣ ብሎም ለከፍተኛ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነልቦናዊ ጉዳት የተዳረጉም ቁጥራቸው ብዙ ነው፡፡ ዛሬ ላይ በክልሉ ዋና ከተማ ጅግጅጋ አብይ ይውረድ፣ አብዲ መሪያችን ነው፣ እና ሌላም የሚሉ  በግጭቱ ወቅት ሄጎ በተባለው ቡድን  በቀለም የተፃፉ ፅሁፎች በየግርግዳው እና በሩ ላይ ይስተዋላሉ፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ላይ ያን ክፉ ወቅት በጭንቅ ያለፉት የከተማዋ ነዋሪዎች ጅግጅጋን ወደሰላሟና አንድነቷ ለመመለስ በየፊናቸው ሲታትሩ ተመልክተናል፡፡ አዲሱ የክልሉ መንግስትም የጅግጅጋንና ሌሎች አካባቢዎችን ለመቀየር ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን ይናገራል፡፡

በክልሉ ለደረሰው ውድመት እና ጥፋት እጃቸው አለበት በሚል የተጠረጠሩት የቀድሞው ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ ኢሌ ስልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ ስልጣኑን የተረከቡት ሙስጠፌ ሙህመድ ኡመር በ 3 ወር ቆይታቸው በክልሉ በርካታ ለውጦችን እያስመዘገቡ እንደሆነ በነዋሪው ዘንድ ይነገርላቸዋል፡፡ የሶማሌ ክልል መንግስትና ህዝብ ያ አስከፊ አጋጣሚ እንዳይመለስ እያደረጉ ያለው ጥረት ምን ይመስላል፣ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ከደረሰው ችግር በተጨማሪም ከኦሮሚያ ክልል ጋር ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት ለመፍታት ምን እየተሰራ ነው፣ እንዲሁም በክልሉ ሲፈጠሩ የነበሩ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ምንጫቸው ምን እንደነበርና አሁን እየተወሰዱ ያሉ የመፍትሄ እርምጃዎች ምን እንደሚመስሉ መልስ የሚሰጥ መሰናዶ በዛሬው ቆይታ አምዳችን ይዘናል፡፡ ሰሞኑን በክልሉ የተገኘው የሸገር ታይምስ ዋና አዘጋጅ ሰለሞን ታደሰ  በነዚህና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ በጅግጅጋ ቤተ-መንግስት ከ ም/ርዕሰ መስተዳደሩ ጋር ቀጣዩን ቆይታ አድርጓል፡፡

***************************************

ሸገር ታይምስ፡- ከሀገር የወጡት በምን ምክንያት ነበር፤ በውጭ ቆይታዎ ወቅት በፖለቲካ ተሳትፎዎ አክቲቪስት ነበሩ?

አቶ ሙስጠፌ:- መደበኛ አክቲቪስት አልነበርኩም፡፡ እንደምታውቀው እኔ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ ነበር የምሰራው፡፡  በተባበሩት ድርጅት ውስጥ ሆነህ በፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባት አይቻልም፡፡ በወቅቱ የምፅፋቸው ፅሁፎች አቀራረቤ ላይ እንደ አክቲቪስት አልነበረም፡፡ ነግር ግን የዚህ ክልል ተወላጅ እንደመሆኔ ህዝባችን ላይ ይደርስ የነበውን ጭፍጨፋ፣ ሰቆቃ እና እንግልት ለህሊና በጣም ይከብድ ነበር እኔ በፈረንጆች አቆጣጠር በ2007 ነው ለህይወቴ በመስጋት ነበር ከሀገር የወጣሁት፡፡

በወቅቱ የነበረው ስርአት ነፃ አውጪዎችን ለማጥፋት በሚል ምክንያት የታጠቀውንም ሆነ ያልታጠቀውን ባለየ መልኩ በህዝቡ ላይ ከፍተኛ አፈና፣ስቃይ፣ እና አንግልት ያደርስ ነበር ፡፡ በወቅቱ የዩኤን አንድ ቡድን መጥቶ ጥናት  በማድረግ በክልሉ ያለውን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ሪፖርት አውጥቶ ነበር ያንን ሪፖርት የፃፈው እሱ ነው በሚል ሊያስሩኝ ሲሉ ነው የተሰደድኩት፡፡ በህዝባችን ላይ የሚደርሰውን  በደል ግፍና መከራ እያየን ዝም የምንልበት ወይም ወፍራም ደሞዝ አለኝ እና ምን አገባኝ የምትልበት ህሊና አይኖርህም ፡፡ ይሄንንም መታገል አለብኝ በሚል ነው ፅሁፎችን ማቅረብ የጀመርኩት፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ህይወትም ስላለ ስራዬንም ማጣት ስለሌለብኝ በብዕር ስም በእንግሊዘኛም በሶማሊኝም በርካታ ፅሁፎችን አቅርቤ ያለሁ፡፡ አብዛኛዎቹ በወቅቱ በህዝቡ ላይ ይደርሱ የነበሩ ግፍ እና ሰቆቃዎችን ለውጩ አለም የሚያጋልጡ ነበሩ፡፡ በብእር ስም ስም ስትፅፍ ትልልቅ የሆኑ እና ታዋቂ የሆኑ ገጾች እና ሚዲያዎች  ፎቶ እና ትክክለኛ ስምህን ይዘው መውጣት ስለሚፈልጉ ከባድ ፈተና ሆኖብኝ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በሶማሌ ዌብ ሳይቶች እና እንደ ናዝሬት ዶት ኮም በመሳሰሉት ላይ በተለያዩ የብዕር ስሞች ያለውን ሁኔታ እየተከታተልኩ እፅፍ ነበር፡፡ እዚህ ያሉት መረጃ የሚሰጡኝ ሰዎች እና ሀገር ውስጥ የነበሩ ሰዎች ግን በብእር ስሜም ቢሆን ያውቁኝ ነበር፡፡

ሸገር ታይምስ፡- ምን አይነት ፅሁፎችን ነበር የሚያቀርቡት?

አቶ ሙስጠፌ፡- አብዛኞቹ ፅሁፎች ምሁራዊ እና ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ናቸው፡፡ በተለይ የተጨቆነ ማህበረሰብ ምንድነው ባህሪያቱ፣ በእኛ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው በደል ምንድነው፣ የጨቋኝ መሪ እና መንግስታት ባህሪ ምን ይመስላል፣ በደል እና ስቃይ የህዝባችን እጣ ፋንታ አይደለም ከዚህ እንዴት መውጣት ይቻላል? ማንስ ነው ይህን በደል እያደረገብን? ያለው የሚሉ እና ሌሎችንም  ሀሳቦች በማንሳት ህዝቡ እውቀት እንዲኖረው እና የተጣለበትን የግፍ ቀንበር አሽቀንጥሮ በመጣል የራሱን ዲሞክራሲያዊ እና የተፈጥሮ መብቱን እንዲያስከብር የሚያነሳሱ እና የሚያነቁ ፅሁፎችን ነበር የማቀርበው፡፡  እንደምታወቀው የእኛ ማህበረሰብ  ከማንበብ ይልቅ በፌስ ቡክ እና በተለያዩ ሶሻል ሚዲያዎች ላይ ስለሚያተኩር ፅሁፎቹም ይበልጥ ተደራሽ እንዲሆኑ በትክክለኛው ስሜ የፌስ ቡክ አካውንት በመክፈት አንዳንድ ፅሁፎች እና ዜናዎችን ሼር በማድረግ  በቀልድም በቁም ነገርም  በክልሉ የሚደረገውን ግፍ እና እስር አጋልጥ ነበር፡፡ እንዳልኩህ ከምሰራበት መስሪያ ቤት ጋ እንዳያጋጨኝ ፖለቲካ ውስጥ አትግባ የሚለውን የመስሪያ ቤቱን ህግ በማክበር  ነገር ግን በተለይ በሰዎች ላይ እየደረሰ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት እና ግፍ ማጋለጥን ተቋሙ ስለማይከለክል ያንን በመጠቀም የፖለቲካ ፓርቲ አባልም ተሳታፊም ሳልሆን የመነጋር ነፃነት መብቴን በመጠቀም በርካታ ፅሁፎችን ሳቀርብ ነበር፡፡

በተባበሩት መንግስታት ህግ በፖለቲካ ውስጥ መግባት የምትከለከለው እና ጥብቅ የሆነው በምትሰራበት ሀገር ላይ ነው፡፡  እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ዜጋ እንደመሆኔ ስለ ሀገሬ እንዳላወራ የሚከለክለኝ ህግ  የለም፡፡ የእኔ አለቆች ስለ ትራምፕ እና ሂላሪ ያወራሉ ይህ ስለማያስጠይቃቸው እንደፖለቲካ አያዩትም እኔ መንግስትን የሚወቅስ ፅሁፍ በመፃፌ ለኔ የተለየ ህግ መውጣት የለበትም በሚል ተከራክሬ የመፃፍ መብቴን አስከብሬ ቆይቻለሁ፡፡  በዚህም በርካታ ወጣቶች ገጹን ይከተሉ ነበር በክልሉ መንግስት ባለስልጣናት ግን ከፍተኛ ተቃውሞ ፣ማስጠንቀቂያ እና ዛቻዎች ይደርሱኝ ነበር፡፡

ሸገር ታይምስ፡-  ከዛቻ እና ማስጠንቀቂያው ውጪ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ መደለያ ቀርቦልዎት እንደነበር ሰምተናል ይሄ እውነት ነው?

 አቶ ሙስጠፌ፡- ትክከል ነህ፡፡ ወደ መጨረሻ አከባቢ አቡዳቢ ለዩኤን ምክትል ቢሮ ሃላፊ ሆኜ እየሰራሁ በነበረበት ወቅት ከዚህ ተደውሎልኝ ጅግጅጋ ግባ አንድ ሚሊየን ዶላር እና መሬት ይሰጥሃል ብለው የፕሬዝዳንቱ አማካሪዎች ጭምር መደለያ አቅርበውልኝ ነበር፡፡ ፊትለፊት መጋፈጡም አደጋ ስለነበር ቆይ አስብበታለሁ ምናምን እያልኩ ጥያቄያቸውን በዘዴ ስገፋ ነበር፡፡ ይሄን ጥያቄ ባለመቀበሌ እና ፍቃደኛ ባለመሆኔ እንደ ንቀት ስለተቆጠረ ልኩን ማሳየት አለብን ተብሎ ኦክቶበር 19 /2016 ከዚሁ ተደውሎልኝ ያልንህን አልቀበልም ስላልክ የምናደርገውን እናሳይሃለን ብለው በዛቱብኝ በሳምንቱ አዲስ አበባ 6 ኪሎ ዩኒቨርስቲ ምሩቅ የነበረውን ታናሽ ወንድሜንና አባቴን ከከተማ ውጭ ወስደው ወንድሜን ገድለው አስክሬኑን ለአባቴ ውሰድ ብለው ነው የሄዱት፡፡ በክልሉ የሚሰራው ግፍ እና መከራ ከዚህም የከፋ ነበር፡፡

ሸገር ታይምስ፡- ወንድምዎት ከመኪና ተወርውረው እንደተገደሉ ሰምተናል፡፡ ከዛ በፊት የደረሰዎት ማስጠንቀቂያ ከማንና እንዴት ነበር?

አቶ ሙስጠፌ፡- ይሄን ነገር በፊስ ቡክ ገጼ ላይ ፅፌው ነበር፡፡ ትዝ ይለኛል ኦክቶበር 19 ቀን ነበር የተደወለልኝ፡፡ ስልኩን የደወለው ሰው አሁንም እዚሁ ክልል ደጋህቡር ከተማ ውስጥ ይኖራል፡፡ እና ደውሎ ፌስ ቡክ ላይ አትፃፍ አልተባልክም ወይ? አለኝ እኔም ቤተሰቦቼን እንገድላችኋለን እህቴንም እንደፍርሻለን እያሉ ማስፈራራያ እና ዛቻ እንደሚያደርሱባቸው ስለማውቅ አትፃፍ ሳይሆን መንግስትን አትቃወም ነው የተባልኩት የፃፍኩትም የምርምር እና እውቀት ላይ የተመረኮዙ ፅሁፎች ናቸው ብዬ መለስኩለት፡፡ በወቅቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀ ልክ በአስረኛው ቀን ነበር፡፡

ሰውየው አሁን ሀገሪቱ ላይ አስቸኳይ አዋጅ ታውጇል ማንንም ሰው መግደል እንደምንችል አታውቅም ወይ?ሲለኝ አስቸኳይ አዋጅ ባይታወጅም ድሮም ትገሉ ነበር እኮ ብዬ መለስኩለት፡፡ ይህ ሰው የእኔ ጎሳ አባል ነው፡፡ እኔ አንተን ከመርዳት እና ከመጠበቅ አንፃር ነው የምትፅፈውን ነገር ተውና ከፕሬዝዳንቱ ጋር ላገናኝህ ሁለታችሁ በስልክ ተነጋገሩ አለኝ፡፡ እኔ በወቅቱ ፍቃደኛ ሳልሆን ቀረሁ የምሰራው ዩኤን ውስጥ ነው ፖለቲካ ውስጥ የለሁበትም፡፡ እናንተው ልታስሩኝ ስትሉ ሀገሩን ለቅቄ ወጥቼላችኋለሁ ተውኝ አልኳቸው፡፡ በማግስቱ በድጋሚ ደውሎ ብንመክርህም ብንነገርህም እንቢ ብለሃል እርምጃ እንወስዳለን በማለት ሲናገረኝ ቤተሰብም እየደወለ እየደረሰባቸው ያለውን ዛቻ እና ማስፈራሪያ ይነግሩኝ ስለነበር በቃ እሺ አልፅፍም በማለት መለስኩለት፡፡ ከሶስት ቀናት በኋላ ይሄው ሰው ደውሎ የተነጋገርነውን አልፈፀምክም አለኝ፡፡

ሸገር ታይምስ፡- ምንድን ነበር የተነጋገራችሁት?

አቶ ሙስጠፌ፡- እኔም የጠየቅኩት ይሄንኑ ነው፡፡ በቃ እንዳትፅፍ አላችሁኝ  አልፃፍኩም ከዚህ ውጭ  ምንድን ነበር የተነጋገርነው? ስለው አለመፃፍ ብቻ ሳይሆን በፌስቡክህ ፕሬዝዳንቱን እንድታሞግስ እንፈልጋለን እሳቸው የልማት አባት እንደሆኑ እና አንተ ይሄ እንዳልታየህ መግለፅ አለብህ፣ እንዲሁም ከግንቦት ሰባት እና ሌሎች አሸባሪዎች ጋር በመሆን ክልሉን ስትጎዳ እንደነበር አምነህ መጸጸትህን በመግለፅ ልማቱን አሞግስ አለኝ፡፡ እኔም በጭራሽ ይሄንን አላደርግም ብዬ በግልፅ ተቃወምኩ እንቢ ካልክ የምናደርገውን እናሳይሃለን ሲሉም ዛቱብኝ ልክ በዛ ቀን አባቴንና ወንድሜን አመሻሹ ላይ ከቤት ይዘዋቸው በመሄድ ለ6 ሰአት ያህል ሁለቱንም ገርፈው ለቀቋቸው ምሽት ላይ ቤት ስደውል አባቴ ሁሉንም ደብቆኝ ጣቢያ ተወስደው ቃል ሰጥተው ብቻ እንደተመለሱ ነገረኝ፡፡ መገረፋቸውን እና መሰቃየታቸውን የአባቱ ሁለተኛ ሚስት ነበር የነገረችኝ፡፡

ይህንኑ የዛኑቀን ፌስ ቡክ ላይ ፃፍኩት በግል ቂም የተነሳ አባቴ እና ወንድሜ ታስረው መገረፋቸውንም ይፋ አደረኩ በምናገረው መጠየቅ ያለብኝ እኔ እንጂ አባቴ  ለምን ይገረፋል ስልም የመጣው ይምጣ ብዬ ግድያ እና እስር መች ነው የሚቆመውስልም ፃፍኩ  ለካ ይሄ ልጅ ተው ብንለውም አላቆምም በሚል ከኦክቶበር 23 አስከ ኦክቶበር 28 በየቀኑ እህቶቼ  ጅግጅጋ እየተጠሩ ዛቻ ይደርስባቸው ነበር፣ ንብረታቸው በየቀኑ ይፈተሻል ለቤተሰቦቼ የገቢ ምንጭ የነበሩት እና ለወንድሞቼ የገዛኋቸው ሶስት መኪኖችም ተወሰዱ ይሄ ሁሉ ግፍ በእኔ የተነሳ ነበር ሲደርስባቸው የነበረው፡፡ እኔም ሀሳባቸውን ልቀበል እና ያሉትን እንደማላደርግ ሲያውቁ ኦክቶበር 29 ከለሊቱ ስምንት ሰዓት አባቴንና ታናሽ ወንድሜን በመያዝ አባቴን መኪና ውስጥ ወንድሜን ደግሞ ክፍት መኪና ላይ ከላይ አድርገው ከደጋህቡር ከተማ ወደ ጎዴ ወስደው ደናን ከሚባለው 15 ኪሎ ሜትር ገባ እንዳሉ ደምስሮቹን ቆራርጠው እና አንቀው ከገደሉት በኋላ ከመኪና ላይ በመወርወር አባቴን ራሱን ከመኪና ላይ ወረወረ እብድ ነው አስክሬኑን ይዘህ ሂድ አሉት፡፡ ከዚያ በኋላም በስህተት ነው ወደ ሀገርህ ተመለስ እና ካሳ እንሰጥሀለን በሚል ሊያግባቡ ሞክረው ነበር ነገር ግን በእንቢተኝነቴ ነው የቀጠልኩት፡፡

ሸገር ታይምስ፡- ከዚያ በኋላ እንዴት ነበር ቤተሰቦችዎ ከሀገር ሊወጡ የቻሉት?

አቶ ሙስጠፌ፡- እነሱ ሁሉንም ቤተሰቡን ሁሉ ይዞ ይወጣል የሚል ግምት አልነበራቸውም፡፡ እንዲየውም ወንድሙ ከተገደለ በኋላ ይሰበራል መፃፉንም ያቆማል የሚል ግምት ነበራቸው እኔ ግን አቅሙም ስለነበረኝ ሙሉ ቤተሰቦቼን በመጀመሪያ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ካደረኩ በኋላ ወደ ናይሮቢ በመውሰድ የተለያዩ ቤቶችን ተከራይቼ እዛው አስቀመጥኳቸው፡፡ ይህንን ሲያወቁ ንብረታችን ተወሰደ ፣ ቤታችንም ታሸገ በእነዛ ሁለት ዐመታት ያን ሁሉ ቤተሰብ ማስተዳደር ከባድ ቢሆንም የራሴን በመቀነስ ቤተሰቦቼን ከግድያ እና ከእስር  ለአንድ አመት ከግማሽ  በናይሮቢ በማቆየት ማዳን ችያለሁ፡፡ ሁኔታው በጣም ከባድ  ነበር፡፡ እኔ ትክክለኛ ነገር ሰርቻለሁ ብዬ  አምናለሁ፡፡ ነገር ግን አንዳንዴ የወንድሜን ሞት ሳስብ ራሴን እንደምከንያት ቆጥሬ የምወቅስበት እና እኔ ብሞት ይሻል ነበር የምልበት ሁኔታ አለ፡፡ እኔ እውነት በመናገሬ እሱ ተገደለ ይህ አልፎ አልፎ ጸጸት ይፈጥርብኛል፡፡

ሸገር ታይምስ፡-  ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ  በክልሉ ስለተፈመው የሰብአዊ መብት ሰምቼው ዘግንኖኛል የሚሉት የቱን ነው?

አቶ ሙስጠፌ፡- በጣም በርካታ ነው፡፡ አንዱ የሰው ልጅን ከጅብ እና ነብር ጋር የማሰሩ ጉዳይ ነው፡፡ ሌላኛው በሴቶች ብልት ውስጥ በርበሬ በመጨመር አንዲቃጠሉ የማድረግ ነገር እንደነበርም ሰምቻለሁ የቤተሰብ አባላትን እና ሴቶችን ራቁት ማድረግ  የመሳሰሉትን ስሰማ እውነት ይህ ሁሉ ከሰው ልጅ ጭንቅላት የመጣ ነው ብዬ አስብ ነበር፡፡ በቀደም እለት አንድ ሽማግሌ ደጋህቡር ላይ የነገሩኝን ልንገርህ  በክፍት መኪና ተጭነን ስንሄድ ከመሀላችን አንድ ህፃን ልጅ የተቃፈች አራስ ሴትን ፖሊሶች ጸረ ሰላም ናት ብለው መኪናው ላይ ይዘዋት ይወጣሉ፡፡ ታዲያ ጉዞ እንደጀመሩ ህፃኑ አምርሮ ሲያለቅስ ፀጥ አሰኚው ብለው ፖሊሶች ያዛሉ፡፡ እናትየው ለማባባል ብትሞክርም ህፃኑ አምርሮ ማልቀሱን ቀጠለ፡፡ ፖሊሶቹ ይህን ጸረሰላም ልጅሽን ዝም አታስብይም በማለት ደጋግመው እናትየውን ቢናገሩ እና እናትም ለማባበል ብትሞክር ህፃኑ ለቅሶውን ቀጠለ ፡፡በዚህ የተበሳጨው አንዱ የፖሊስ አባል አይናችንን እያየ ህፃኑን ተቀብሎ ከመኪናው ላይ ወረወረው ነበር ያሉኝ፡፡ ይሄ ዘግናኝ እና ከሰማሁት ሁሉ በላይ ጭካኔ ነው ፡፡ ክልሉ ላይ ዞረህ ብትሰማ  ከዚህ የበለጡ እጅግ ዘግናኝ እና ለጆሮ የሚከብዱ ግፎች ነው የተፈፀሙት፡፡

በኃምሌ 28 ረብሻ የተደፈሩ 10 ሴቶችን አሁን ቤት ተከራይተን አስቀምጠናቸዋል፡፡ ከተደፈሩት እነዚህ ሴቶች መካከል አንደኛዋ የ60 ዓመት አዛውንት ናቸው ይታይህ አንግዲህ የ60 አመት እናትን የሚደፍር ምን አይነት ህሊና ያለው ሰው ቢሆን ነውይሄን ሲያደርጉ የነበሩ ሰዎች አሁንም ውስጣችን አሉ ሌላው ቀርቶ ያ ስልክ በመደውል ሲዝትብኝ የነበረው ግለሰብ ራሱ አሁን እዚሁ ክልል ውስጥ አለ፡፡ በቀደም ይረብሻል በሚል አስረውት እኔ ራሴ ነኝ አንዲለቀቅ ያደረኩት ፡፡ በግል ቂም በቀል  ወይም ከእኔ ጋር በመደዋወሉ ሳይሆን ወንጀል ሰርቶ ከተገኘ ነው መጠየቅ ያለበት ብዬ ነው ያስለቀቅኩት፡፡

ሸገር ታይምስ፡- ለዚህ ሁሉ ግፍ እና ስቃይ ሃላፊነት የሚወስደው (ተጠያቂው) ማነው ይላሉ?

አቶ ሙስጠፌ፡- እንዲህ ሲያደርጉ የነበሩ እና ህዝባችንን ሲጨፈጭፉየነበሩ ሰዎችን ከለላ ሰጥቶ ጭራሽ ሞዴል ናቸው እያሉ ሲሸልሙ የነበሩ  በስም የሚታወቁ የመከላከያ ሹማምንት እና አንዳንድ የፖለቲካ መሪዎች  አሉ፡፡ ነፍሰ በላየሆኑ ሰዎቸችን ሲንከባከቡ እና በምስራቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢትዮጵያዊነትን እያሰረጸ ያለ ጀግና እያሉ ሲያሞካሹ የነበሩ ሰዎች አሉ እነዚህ ሰዎች ሳይጠየቁ መቅረታቸው እና አስካሁን በፈፀሙት ግፍ በህግ አደባባይ አለመቆማቸው እጅግ በጣም ያሳዝናል፡፡

ሸገር ታይምስ፡- እነዚህን ሰዎች በህግ ለመጠየቅ  ለምን አልተቻለም?

አቶ ሙስጠፌ፡- አስካሁን የተደረገ ጥረት የለም ፡፡ ምክንያቱ ድግሞ ሊፈርስ የነበረ ክልል እንደመሆኑ የማረጋጋት ስራ ላይ ነው ያለነው፡፡ ትኩረታችን መዋቅር መዘርጋት፣ ደህና ደህና የሚባሉ ሰዎችን እስከ ወረዳ ድረስ መመደብ፣ በጎሳዎች መካከል ሊነሱ ይችሉ የነበሩትን ግጭቶች መፍታት በወደቀው ሃይል በገንዘብ ጭምር እየተደገፉ የሚነሱ ብጥብቶችን ማረጋጋት እና  የሞተው ሞተ ብለን ሌላ ህይወት እንዳይቀጠፍ እና ህይወት የማዳን ስራ ላይ ንን፡፡ ከተረጋጋ እና ስርአት ከያዘ  በኋላ  ወደተጠያቂነቱ ማተኮራችን አይቀርም፡፡

ሸገር ታይምስ፡-  በክልሉ  ከ 100 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ በመከላከያ ሹማምንት እና በአንዳንድ ባለስልጣናት ተወሰደብን የሚል ስሞታ ሲቀርብልዎ ሰምቻለሁ…

አቶ ሙስጠፌ፡- እውነት ነው፡፡ ያው አንተም እንደሰማኃው ነዋሪው ይህን ነገር አቅርቧል ቦታውንም ሄደን እንደተመለከትከው አጠቃላይ 100 ሺህ ካሬሜትር አከባቢ ነው፡፡ ይሄን ቦታ የወሰዱት ምስራቅ እዝ ከነበሩ የመከላከያ ሹማምንት ጋር ቤተሰባዊ ትስስር የነበራቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ስለሚታወቅ አሁን ዘር መጥቀሱ አስፈላጊ አይደልም፡፡ ቦታ ከተሰጣቸው መካከል የመንግስት ባለስልጣነት ልጆች ሁሉ እንደሚገኙበት ሰምተናል፡፡ በህገውጥ መንገድ ተገፍተን እና ተባረን ነው መሬቱ የተወሰደው የሚለውን ስሞታም ሲያቀርቡ ነበር ይሄ ደግሞ ከባድ ነው፡፡ 

መሬትን ለኢንቬስተር ስትሰጥ ህዝቡን አሳምነህ እና የአካባቢውን ነዋሪ ተጠቃሚ በሚያደርግ ጉዳይ መሆን ነበረበት፡፡ ህዝቡ የበይ ተመልካች መሆን የለበትም እሱ እየተራበ ሌላውን አምጥተህ ልታሰፈርበት አይገባም ኢንቬስተርም ከተባለ እዛው አከባቢ ያሉ በርካታ ኢንቬስተሮች ነበሩ፡፡ በአጠቃላይ በቦታው ላይ ያሉት ጎሳዎች በዚህ ምሬት ራሳቸውን ወደ ማስታጠቅ የገቡበት  ሁኔታ  ነበር፡፡ ዞሮ ዞሮ ጉዳዩ የግጭት መንስኤ መሆኑ አይቀርም ነበር፡፡ በክልሉ የፖለቲካ ግጭት ቢያቆም እንኳን ይሄ የመሬቱ ጉዳይ ሌላ የፖለቲካ ግጭት ማስነሳቱ አልያም ሰዎችን መንገድ ላይ ማረድ፣ ቦምብ ማፈንዳት እና ህገወጥነት ሊጀመር ነበር ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ተዘርፈናል ብለው ነው የሚያምኑት፡፡ የዝርፊያው ብዛት እና የክፋቱን መጠን ሳስበው ከዚህ ተጠቅመው ሚሊየነር የሆኑ ሰዎች እነሱ ባስቀመጡት ሰው የሶማሌ ህዝብ ሲገደል ማየታቸው አይገርመኝም፡፡ ምክንያቱም አቅላቸውን የሳቱ ከሰውነት ተራም የወጡ ህሊና ቢሶች ናቸው፡፡ እኛ የምንኖር ከሆነ ሌላው ድብን ይበል የሚሉ ህሊናቸው በገንዘብ የታወረ የምንንም ህዝብ የማይወክሉ ስበስቦች ናቸው ህዝቡን ሲዘርፉ እና ሲገድሉ የትኛውንም ብሄር አማክረው አይደለም የግል ጥቅማቸውን ለማስፈጸም ሲሉ ብቻ ነው ፡፡

በእኛ በኩል በየትኛውም ብሄር ላይ በተለይ እኔ ቅሬታም ሆነ ቂም ይዤ አላውቅም፣ የለብኝም፡፡ ነገር ገን ይሀን የፈፀሙ የመከላከያም ሹማምንት ሆነ  ከመከላከያ የማይርቁ የፖለቲካ አመራሮች የሶማሌ ህዝብ የዘላለም ጠላቶች ናቸው፡፡  በሀውዜን ጭፍጨፋ  ሰው በላ እየተባሉ የእነ ለገሰ አስፋው ስም እንደሚያነሱት ሁሉ ከሃውዜን ጭፍጨፋ ያላነሰ ግፍ በሶማሌ ህዝብ ላይ የፈጸሙ ከፍተኛ አመራሮች አሉ፡፡

ሸገር ታይምስ፡- ክቡር ፕሬዝዳንት እንደው ሹማምንት ብቻ እያልን ከምናልፍ በስም ብንጠቅሳቸውስ?

አቶ ሙስጠፌ፡- በህዝባችን ላይ ከፍተኛ ግፍ እና ጭፍጨፋ ከፈፀሙት መካከል በዋናነት የሚጠቀሱት  የምስራቅ እዝ አዛዥ የነበረው ጀነራል አብርሃ ኳርተር እና ከእነሱ ጀርባ ድግሞ እነ አባይ ፀሃዬ ናቸው እነዚህ የሶማሌ ህዝብ ዘላለማዊ ጠላት እና በፍጹም የማንረሳቸው ደመኞቻችን ናቸው፡፡

ሸገር ታይምስ፡- ተወሰደ የሚባለውን ቦታ ጎብኝተናል፡፡ ምንም አይነት ኢንቨስትመንትም አልተደረገበትም፡፡ ምከንያቱ ምንድነው?

አቶ ሙስጠፌ፡- ማን ስንት ወሰደ የሚለውን ገና አላጣራንም እንጂ እነዚህ ሰዎች ቦታውን ከወሰዱ በኋላ መሬቱን በማስያዝ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ገንዘብ ከባንክ እንደወሰዱ መረጃዎች አሉን፡፡ ሰዎቹ ዝም ብለው መጥተው መሬት ለክተው የኔ ነው ይላሉ ከዛም ከባንክ ብር ወስደው ይጠፋሉ፡፡ እንደተመለከትከው በቦታው ላይ ህዝብን የሚጠቅም አንዳችም ኢንቨስትመንት አልሰሩም፡፡ሌላስም ፈፅሞ ልትሰጠው አትችልም ይህ በግልፅ ሌብነት ነው፡፡ ይሄን ጉዳይ አንድ ኮሚሽን አቋቁመን በስርአት እና ከስሜት በወጣ ሁኔታ አጣርተን ህጋዊ የሆነውን እና ያልሆነውን ለይተን እርምጃ በቅርቡ እንወስዳለን፡፡

ሸገር ታይምስ፡- በኦሮምያ እና ሶማሌ ግጭት ላይ ዋናው የጦርነቱ ቀስቃሽ የሶማሌ ክልል የቀድሞው አመራር ነው ሲሉ ሰምቻለሁ ስለዚህ ጉዳይ ትንሽ ቢያብራሩልን?

አቶ ሙስጠፌ፡- ይሄም ጉዳይ ቅድም ከጠቀስኳቸው ሰዎች አያልፍም በሀገር አቀፍ ደረጃ የፖለቲካ ሽኩቻ እና መገፋፋት ሲፈጠር ታዳጊ ክልሎች የሚባሉ እና በወቅቱ በአሀአዴግ የተያዙ ነበሩ ከነዚህ አንዱ የሶማሌ ክልል ነው፡፡  ሶማሌ ክልልን ሲያሽከረክሩ የነበሩ ሰዎች በወቅቱ በነበረው  የኦሮሞ መነሳሳት ላይ ጫና ለመፍጠር በምስራቅ በኩል ጦርነት ለመክፈት ያቀዱት ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህን በግልፅ የምናገረው ነገር እና አዲስ ነገር አይደለም፡፡ በሶማሌና በኦሮሞ መካከል የድንበር ጥያቄ እዚህም እዚያም ነበሩ ፣ይኖራሉም በእንዲህ አይነት አሰፋፈር ሰዎች ሲኖሩም በአለም ላይ የሚያጋጥም ነገር ነው፡፡ በእርሻ፣ በግጦሽ የመጋጨት ነገር ይገጥማል፡፡ እኛ ክልል ላይ የተፈጠረው ግን ይሄ አይደልም፡፡ ከማስተር ፕላን ጋ ተያይዞ አዲስ አበባ ውስጥ ከፍተኛ ተቃውሞ መነሳት ሲጀምር ይህንን ተቃውሞ ለማዳከም በምስራቅ በኩል ሌላ የጦርነት ግንባር እንክፈት ከሚል የፖለቲካ ቀመር የመጣ ጥቃት ነበር በዋናናት የዚህ አስፈፃሚ የነበሩት የሶማሌ ክልል ሹማምንት የነበሩ እና ሀረር ከሚገኘው የመከላከያ አዛዥጋ እጅና ጓንት የሆኑ መሆናቸውን ተራው ህዝብም የሚያወቅው ጉዳይ ነው፡፡  በኋለ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ ከዚህም ከዚያም ሰው ሲሞት ነገሩ በነዋሪው መካካልም እየተስፋፋ ሄደ  እንጂ የመጀመሪያ መነሾው ግን እንዳልኩህ በመከላከያ እና የፖለቲካ ባልስጣናት ቀመር የተነሳ  ግጭት ነው፡፡

ሸገር ታይምስ፡- እርስዎ እና ካቢኔዎ  አሁን ምን እየሰራችሁ ነው?

አቶ ሙስጠፌ፡- ላለፉት አስር አመታት ክልሉ በአንድ ሰው የበላይነት እና አንባገንንነት ሲመራ የኖረ ነበር፡፡ ይህ ሲፈርስ ደግሞ ወይ በሌላ ጠንካራ ሰው ተክቶ መስራት  አልያም ጠንካራ የመንግስት መዋቅር መዘርጋት ነው፡፡ ይህን ለመዘርጋት ደግሞ ግዜ ይፈልጋል፡፡ እሱ ላይ በጥልቀት እየሰራን ነበር፡፡ መዋቅሩን በተማሩ እና ከራሳቸው ይልቅ ለህዝብ ጥቅም የሚኖሩ እንዲሁም ለሚጠየቁት ጥያቄ በጥይት ሳይሆን በትህትና እና በአገልጋይነት ስሜት ምላሽ የሚሰጡ የተማሩ ወጣቶችን እና ባለሙያዎችን ከላይ እስከ ታች መዘርጋት እና የህዝቡን የፍትህ፣ የመብት፣ የተጠቃሚነት ጥያቄ በአግባቡ ምላሽ ያገኝ ዘንድ እየሰራን ነው፡፡ በዚህም ጥሩ ደረጃ ላይ ብንደርስም ሁሉንም አሳክተናል ማለት ግን አንችልም አልፎ አልፎ እዚህም እዚያም ጥያቄዎች ቢኖሩም በአጭር ግዜ ውስጥ ስርአቱን ለመዘርጋት እና ሀገሪቷን  በስርአት ለመምራት እየሰራንም ነው፡፡

ሸገር ታይምስ፡- የመጨረሻ የክልሉ መሪ እሆናለሁ ብለው አስበው ያውቁ ነበር?

አቶ ሙስጠፌ፡- እኔ ወደዚህ ስመጣም እንደ አክቲቪስት የህዝቡን ቁጭት እና ህዝባችን መገደል የለበትም የሚለውኝ ይዤ ነው እንጂ ወደ ፖለቲካ ገብቼ ክልል ሄጄ አመራር ሆኜ እቀመጣለሁ የሚል ሀሳብ አልነበረኝም፡፡ ኦገስት ላይ ነው ወደ ሀገር ቤት የመጣሁት ጁላይ ላይ  ከነበርኩበት ወደ ናይጄሪያ ስራ ልቀይር እየተዘገጃጀሁ  ነበር በአንድ ወር ውስጥ ለምንድነው ለውጥ የመጣው የሚለውን ካነሳህ በወቅቱ በክልሉ ላይ ለውጥ እንደሚመጣ ግልፅ ነበር የነበረው ሀገራዊ ለውጥም  የህዝቡም ፍላጎትም በደንብ ይታይ ነበር፡፡ የምናስተባብራቸው ህዝቦች እየበዙ ሲሄዱ ወጥ የሆነ የፖለቲካ ፎርም መያዝ አልቻሉም፡፡ በዛ መልክ ከድሮው የማይሻል ለህዝቡ የማያስቡ አመራሮች ከመጡ እንደገና 10 አመት አክቲቪስት ሆኜ ልቀጥል ነው ወይብዬ ያሰብኩበት ወቅት ነበር፡፡ ነገር ግን በየቀኑ  ይሄ አልተደረገም፣ የአሁኑ አመራር ከድሮው አይሻልም፣ እንዲህ አደረገ ከምል ልምን ራሴ አልሞክረውም በሚል ግፊት ተነሳስቼ ነው ቅስቀሳ አድርገን ህዝቡን አገናኝተን ለውጡ የሚመጣበትን ሮድ ማፕ አስቀምጠን ከፌደራል  መንግስቱ ጋ ግንኙነት ፈጥረን በሂደት ነው  ለውጡ እንዲመጣ እና እንዲሳካ ያደረግነው፡፡

ሸገር ታይምስ፡-  ክቡር ፕሬዝዳንት ከሸገር ታይምስ ጋር ላደረጉት ቆይታ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

****************************************

© እባክዎ ይህን ቃለ መጠየቅ ሲወስዱ  ከታች የተቀመጡትን የፅሁፉን ባለቤት መጠቀስ አይዘንጉ

https://www.facebook.com/shegertimesmag/

www.shegertimesmegazine.com

Share your thoughts on this post

%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram