fbpx

የሴት ብልት የፈንገስ ኢንፌክሽን

የሴት ብልት የፈንገስ ኢንፌክሽን (Vulvovaginal yeast infection)

የሴት ብልት የፈንገስ ኢንፌክሽን ምንድን ነው?

የሴት ብልት የፈንገስ ኢንፌክሽን በሴት ብልት የውጨኛው ቆዳ ላይ የመቆጣት እና የማሳከክ ስሜት የሚያስከትል ኢንፌክሽን ነው።

ይህ ኢንፌክሽን የሚከሰተው ካንዲዳ(candida) በመባል በሚጠራው የፈንገስ ዝርያ ነው።

የሴት ብልት የፈንገስ ኢንፌክሽን ምልክቶችና የህመም ስሜቶች ምንድን ናቸዉ?

ምልክቶቹ የሚከተሉትን ያካትታሉ

● የሴት ብልት የውጨኛው ቆዳ ማሳከክ

● የሽንት ማቃጠል

● የሴት ብልት እና የሴት ብልት የውጨኛው ቆዳ ማቃጠል፣ መቅላት ወይም መቆጣት

● በወሲብ ወቅት ህመም

● የሴት ብልት ፈሳሽ

አንዳንድ የሴት ብልት የፈንገስ ኢንፌክሽን ያላቸው ሴቶች ከሴት ብልት ውስጥ ትንሽ ፈሳሽ ሊኖራቸው ይችላል። ይህ ፈሳሽ በአብዛኛው ነጭና እንደ አይብ የሚበጣጠስ ነው። ነገር ግን ቀጭን እና እንደ ውሃም ሊሆን ይችላል።

ምልክቶቼ በፈንገ ኢንፌክሽን ምክንያት መሆኑን እንዴት አውቃለሁ?

አብዛኛዎቹ ሴቶች የምልክታቸው መንስኤ የሴት ብልት የፈንገስ ኢንፌክሽን ይሁን ወይም ሌላ ነገር ይሁን ሊያውቁ አይችሉም ። የሴት ብልት የፈንገስ ኢንፌክሽን ምልክቶች ከሌሎች የሴት ብልት ኢንፌክሽን ምልክቶች ጋር ተመሳሳይ ናቸው ፤ ስለዚህ ምርመራ ሳያደርጉ በዚህ ምክንያት ነው ብሎ ለመናገር በጣም አስቸጋሪ ነው። እርግጠኛ ለመሆን ሃኪም ወይም ነርስጋ ቀርቦ መታየት እና ከማህጸን ፈሳሽ ናሙና ተወስዶ የላቦራቶሪ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል።

የሴት ብልት የፈንገስ ኢንፌክሽን እንዴት ነው የሚከሰተው?

የሴት ብልት የፈንገስ ኢንፌክሽን የሚያመጣው ፈንገስ አብዛኛውን ጊዜ በአንጀት ውስጥ እና በሴት ብልት ውስጥ ይኖራል። ይሁንና የፈንገሱ ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ አብዛኛውን ጊዜ የበሽታ ምልክቶች አይኖርም።
የተወሰኑ መድሃኒቶች (በተለይም አንቲባዮቲክስ) ፣ ጭንቀትና ሌሎች ምክንያቶች ፈንገሶቹ እንዲባዙ ሊያደርጉ ይችላሉ። ይህ በሚሆንበት ጊዜ የማህጸን የፈንገስ ኢንፌክሽን ምልክት መታየት ይጀምራ።

ከስር የተዘረዘሩት ለሴት ብልት የፈንገስ ኢንፌክሽን
የሚያጋልጡ ሁኔታዎች ናቸዉ

●የአንቲባዮቲክስን መጠቀም

●የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎች መጠቀም

●የስኳር በሽታ

●እርግዝና

●የተዳከመ የሰውነት የበሽታ መከላከያ ስርዓት (የኬሞቴራፒ ሕክምና፣ኤች አይ ቪ)

የሴት ብልት የፈንገስ ኢንፌክሽን እንዴት ይታከማል?

ለሴት ብልት የፈንገስ ኢንፌክሽን የሚሆኑ መድኃኒቶች ​​ሊወስዱ ይችላሉ። መድኃኒቶች የሚዋጡ ወይም በሴት ብልት ውስጥ የሚቀመጡ ሊሆኑ ይችላሉ። በሴት ብልት ውስጥ የሚቀመጡት መድሃኒቶች በክኒን ወይም በክሬም መልክ ሊመጡ ይችላሉ። ለሴት ብልት የፈንገስ ኢንፌክሽን የሚወሰዱ ሁሉም መድሃኒቶች ኢንፌክሽኑን የሚያስከትሉ ፈንገሶችን በመግደል ይሰራሉ።

ጥሩ ስሜት የሚሰማኝ መቼ ነው?

ሕክምና እንደጀመሩ በጥቂት ቀናት ጊዜ ውስጥ ጥሩ ስሜት ሊሰማዎት ይችላል። ህክምናን ካጠናቀቁ በኋላ ካልተሻለዎት ​​ዶክተርዎን ወይም ነርስዎን እንደገና ማየት አለብዎት ፤ ተጨማሪ መድሃኒት መውሰድ ወይም ሌላ መድሃኒት መውሰድ ይኖርብዎት ይሆናል።

ባለቤቴስ ህክምና ማድረግ ይጠበቅበታል?

የሴት ብልት የፈንገስ ኢንፌክሽን በግብረ ስጋ ግንኙነት የሚተላለፍ አይደለም ። አልፎ አልፎ ከአንዱ ወደ አንዱ የመጋባት ሁኔታ ቢስተዋልም ፤ ባለሙያዎች የወሲብ ጓደኛ ህክምና እንዲያደርግ አይመክሩም።

በስነተዋልዶ ጤና ዙሪያ ጠቃሚ መረጃዎች ለማግኘት ገጻችን ይከታተሉ(like ያድርጉ)።

ዶ/ር መስፍን ገ/እግዚአብሔር
ጆይ የጽንስና የማህጸን ልዩ ክሊኒክ

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram