fbpx

HT

ሐበሻ ታይምስ ሚዲያ

AMHARIC

የሳፋየር ማዕድን ለከፍተኛ የኮንትሮባንድ ንግድ ተጋልጧል ተባለ

በዓለም ገበያ ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጣውና በኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት በትግራይ የተገኘው የሳፋየር ማዕድን ለከፍተኛ የኮንትሮባንድ ንግድ ተጋልጧል ተባለ።

የትግራይ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ከማዕድኑ ተገቢውን የውጭ ምንዛሬን ለማግኘት ለህጋዊ አዘዋዋሪዎች ፍቃድ የተሰጠ ቢሆንም የኮንትሮባንድ ንግዱ ሰፊ ቦታን ይዟል ሲል ለፋናብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጿል ።

በዚህም ከማዕድኑ የታሰበው ውጤት እንዳልተገኘ ነው ኤጀንሲው የገለጸው።

የማዕድን ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትሩ አቶ መለሰ አለሙ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት በጥቅሉ የከበሩ ማዕድናት ግብይትን ከችግር ለማውጣት ተቋማዊ አሰራሮችና አስተዳደር ላይ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።

ባለፈው ዓመት በትግራይ ክልል በመካከለኛ፣ ሰሜን፣ ምዕራብና ምስራቃዊ ዞኖች ባሉ መረብ ለኸ፣ መደባይ ዛና እና ሌሎች ወረዳዎችም መገኘቱ ሲሰማ ከስራ ፈጠራና ከውጭ ምንዛሬ ግኝት አንጻር መልካም ዜና ነበር።

በወቅቱ የትግራይ ክልል የማዕድንና ኤነርጂ ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያስጅ አቶ ማዕረግድ ሓዱሽ ጅምሩ መልካም ነበር ብለውናል።

ከዓመት በኃላ ማዕድኑ ለከፍተኛ ህገ ወጥ ንግድ መጋለጡን የሚናገሩት ደግሞ የኤጀንሲው የማዕድን ፈቃድና አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ፍስሀ መረሳ ናቸው።

ባለፈው ዓመት ማዕድኑ እንድተገኘ ለማስተዋወቂያ ተብሎ በኪሎ 10 ሺህ ዶላር ሂሳብ 24 ኪሎ ግራም ወደ ውጭ ተልኮ 240 ሺህ ዶላር ተገኝቶ ነበር።

ይህን ግኝት ለማስፋፋት ለ30 ላኪዎች ፍቃድ ተሰጥቶ የነበረ ሲሆን፥ አሁን ያለው ነገር ግን የተገላቢጦሽ ነው ምክንያቱም ማዕድኑ ለሰፊ ኮንትሮባንድ ተጋልጧል ብለዋል።

በክልሉ ይህ ማዕድን አሁን ላይ በአርሶ አደሮች ነው እየተቆፈረ የሚወጣው።

እነዚህ አርሶ አደሮች ያወጡትን ማዕድን ለላኪዎች የሚያቀርቡ ለ100 ህጋዊ አዘዋዋሪዎች ክልሉ ፍቃድ ቢሰጥም ከአርሶ አደሩ የሚመጣው ማዕድን መዳረሻው ህጋዊ አዘዋዋሪው ጋር አይደለም ብለዋል አቶ ፍሰሐ።

ከዚህ ህገ ወጥ ንግድ ጀርባ የሀገር ውስጥ ህገ ወጥ ደላሎችና የውጭ ዜጎች እንዳሉበት መረጃ አለን ይላሉ አቶ ፍሰሀ።

የዛሬ ዓመት አካባቢ ማዕድኑን በድብቅ ሲገበያዩ የነበሩ ሁለት የውጭ ሀገር ዜጎች በክልሉ ታስረው እንደነበረ ተገልጿል።

እንዲሁም በክልሉ ለጉብኝት ሄደው በዚህ ህገ ወጥ ንግድ ላይ የመሰማራት አዝማሚያ የሚታይባቸው የውጭ ሀገራት ዜጎች እንዳሉም ይናገራሉ።

መንግስት ለውጭ ሀገራት ዜጎች ይህንን ማዕድን ከኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡት ፍቃድ ባይሰጥም የእስራኤል፣ የቻይና፣ የህንድና ስሪላንካ ዜጎች በሰፊው ከትግራይ እስከ አዲስ አበባ ባለ ትስስር ማዕድኑን በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር እንደሚያወስጡ መረጃ አለን ብለዋል አቶ ፍሰሐ።

አቶ ፍስሀ ነገሩ ከኛ አቅም በላይ ነው የዘርፉ ትኩረት ማጣት ማሳያም ነው ብለውናል።

ይህ የሚፈጸመው የሳፋየር ማዕድን ንግድ ፍቃድ ያላቸው የሀገር ውስጥ ዜጎችን ፍቃድ ሁሉ በመከራየት ነው ይላሉ አቶ ፍስሀ።

በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በቦሌ አለማቀፍ አየር መንገድ በኩል በህገ ወጥ መንገድ ሊወጡ ካሉ 1500 ግራም የከበሩ ማዕድናት ውስጥም ሳፋየር እንደሚገኝበትና በዚህም ምክንያት በቁጥጥር ስር የዋሉ እንዳሉ የደረሰን መረጃ ያሳያል።

በዚህ ዓመት ዘጠኝ ወራት በህጋዊ መንገድ የተላከው ሳፋየር እጅግ ጥቂት ግራም የተገኘው ገቢም እዚህ ግባ የሚባል ነገርግን ማዕድኑ ከአርሶ አደሩ እጅ ቢወጣም የሚገኘው ገቢ ግን አይመጣጠንም ተብሏል።

ከዚህ ቀደም እንደ ኦፓልና ኤመራልድ ዓይነት ማዕድኖች ቢገኙም በግብይት ስርዓት ችግር ለሀገሪቱ ጥቅም ማስገኘት አልቻሉም።

በካሳዬ ወልዴ – ኤፍ.ቢ.ሲ

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram