የሲሚንቶ ዋጋ እየናረ ነው
ፋብሪካዎች የዋጋ ጭማሪ ሊያደርጉ ነው
የችርቻሮ ሲሚንቶ ዋጋ በአዲስ አበባና ክልል ከተሞች እየናረ እንደመጣ ተገለጸ፡፡ ሪፖርተር ባደረገው የገበያ ቅኝት በአዲስ አበባ ገበያ ከ210 እስከ 220 ብር የነበረው የአንድ ኩንታል ሲሚንቶ ዋጋ፣ ከ250 እስከ 260 ብር እንደደረሰ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በክልል ከተሞች ዋጋው እየጨመረ እንደሄደ ታውቋል፡፡ በአዳማ ከተማ የሲሚንቶ ዋጋ በኩንታል 270 ብር ሲሆን፣ ራቅ ባሉ የክልል ከተሞች 280 እስከ 300 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ በባህር ዳር ላይ የአንድ ኩንታል ሲሚንቶ ዋጋ 300 ብር እንደሆነ ታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ የሚገኙ ሲሚንቶ ነጋዴዎች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ጭማሪው ሊከሰት የቻለው በአገሪቱ በተፈጠረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት ነው፡፡ በተለይ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ቦታዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት ሲሚንቶ ከፋብሪካ ወደ ገበያ ማመላለስ ባለመቻሉ በገበያ ውስጥ በተፈጠረ እጥረት፣ የሲሚንቶ ችርቻሮ ዋጋ ሊጨምር እንደቻለ ነጋዴዎች አስረድተዋል፡፡
የችርቻሮ ዋጋ የጨመረው የሲሚንቶ ፋብሪካዎቹ ጭማሪ ሳያደርጉ ነው፡፡ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የዋጋ ማስተካከያ ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የዳንጎቴ ሲሚንቶ የሽያጭና ማርኬቲንግ ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን አበራ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በአሁኑ ወቅት ትልቅ ፈተና ገጥሟቸዋል፡፡ የ15 በመቶ የብር ምንዛሪ ለውጥ ከተደረገ በኋላ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከውጭ በሚያስገቧቸው የድንጋይ ከሰል፣ የፋብሪካ መለዋወጫዎችና የሲሚንቶ ከረጢት ላይ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ለውጥ ማምጣቱን አቶ መስፍን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በግብዓትነት የሚጠቀሙባቸውን ፑሚስ፣ ክሌይና ላይምስቶን በቶን ከ15 እስከ 20 ብር ለወጣት ማኅበራት እንዲከፍሉ በመደረጉ፣ የማምረቻ ወጪያቸውን እንደጨመረው አቶ መስፍን አስረድተዋል፡፡ የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ እስካሁን እነዚህን ወጪዎች ራሱ እየሸፈነ እንደቆየ ገልጸው፣ እያደገ የመጣውን የማምረቻ ወጪ ተሸክሞ መቀጠል እንደማይችል ገልጸዋል፡፡
የዋጋ ማስተካከያ ጥናት ተሠርቶ ለማኔጅመንቱ መቅረቡን የገለጹት አቶ መስፍን፣ ፋብሪካው በቅርብ ቀን ከአሥር እስከ 15 በመቶ ጭማሪ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የዳንጎቴ ሲሚንቶ የፋብሪካ መሸጫ ዋጋ 218 ብር ነው፡፡
የሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ በበኩሉ ከመጋቢት 7 ቀን ጀምሮ የ11 በመቶ ጭማሪ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ የሐበሻ ሲሚንቶ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን አቢ (ኢንጂነር) ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ከብር ምንዛሪ ለውጥ በኋላ እየጨመረ የመጣውን የማምረቻ ወጪ ለመቋቋም ፋብሪካው የዋጋ ማስተካከያ ለማድረግ ተገዷል፡፡ ‹‹የድንጋይ ከሰል የምናስገባው ከደቡብ አፍሪካ ነው፡፡ ከአጠቃላይ የምርት ወጪያችን የድንጋይ ከሰል 70 በመቶ ይይዛል፡፡ ከምንዛሪ ለውጡ በተጨማሪ የዓለም የድንጋይ ከሰል ዋጋ በመጨመሩ፣ በአጠቃላይ በድንጋይ ከሰል ወጪያችን ላይ የ25 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፤›› ብለዋል፡፡
አቶ መስፍን የመለዋወጫና የሲሚንቶ ከረጢት ግዢ ከምንዛሪ ለውጡ ጋር ተያይዞ በመጨመሩ በፋብሪካዎች ላይ ጫና እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል፡፡ አምራቾች እስካሁን የዋጋ ጭማሪ ሳያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸው፣ ከዚህ በኋላ በነበረው ዋጋ መቀጠሉ ወደ ኪሳራ የሚያስገባ በመሆኑ የተከሰተውን የምርት ወጪ ጭማሪ ያህል ባይሆንም፣ ሐበሻ ሲሚንቶ አነስተኛ የዋጋ ማስተካከያ እንዳደረገ ተናግረዋል፡፡ የሐበሻ ሲሚንቶ የፋብሪካ መሸጫ ዋጋ በኩንታል 195 ብር የነበረው ከሐሙስ መጋቢት 6 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ 218 ብር ሆኗል፡፡
የአንድ ኩንታል ሲሚንቶ ዋጋ እስከ 1994 ዓ.ም. ድረስ 60 ብር ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን የኮንስትራክሽን ዘርፍ በፍጥነት እያደገ በመምጣቱ የሲሚንቶ ዋጋ እየናረ ሄዶ፣ የኢትዮጵያ ሚሊኒየም በተከበረ ማግሥት 500 ብር ደርሶ ነበር፡፡
ደርባ ሚድሮክ ሲሚንቶ ፋብሪካ በ2004 ዓ.ም. ምርት ሲጀምር የሲሚንቶ ገበያውን ማረጋጋት ችሏል፡፡ የደርባ ሲሚንቶ ምርት ወደ ገበያ ውስጥ ሲገባ የአንድ ኩንታል ሲሚንቶ ዋጋ ወደ 200 ብር ሊያሽቆለቁል ችሏል፡፡
የደርባ ሲሚንቶ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይሌ አሰግዴ ለሪፖርተር እንደናገሩት፣ 210 ብር የነበረው የአንድ ኩንታል ሲሚንቶ ዋጋ በአሁኑ ወቅት ሲሚንቶ አምራቾች ዋጋ ሳይጨምሩ በችርቻሮ ገበያ ላይ አንድ ኩንታል ሲሚንቶ 270 ብር ድረስ እየተሸጠ ነው፡፡ ‹‹በተፈጠረው የትራንስፖርት መቆራረጥ ፋብሪካዎች ምርታቸውን ማውጣት አልቻሉም፡፡ ሠራተኞቹ ወደ ፋብሪካ ለሥራ መግባት አልቻሉም፡፡ በዚህ ምክንያት በምርት አቅርቦት ላይ በተፈጠረ መስተጓጎል በችርቻሮ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ታይቷል፤›› ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሲሚንቶ አምራቾች ማኅበር ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ኃይሌ የ15 በመቶ የብር ምንዛሪ ለውጥ፣ የድንጋይ ከሰል ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ የ20 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ በሲሚንቶ ፋብሪካዎች ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ለወጣት ማኅበራት በምናመርተው ጥሬ ዕቃ የምንከፍለው ክፍያ አለ፡፡ አገሪቱ ውስጥ በአጠቃላይ የኑሮ ውድነት አለ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ እየጠየቁ ነው፡፡ የእኛ ሠራተኞች ለአሥር ቀናት የሥራ ማቆም አድማ አድርገው ነበር፡፡ እነዚህ ምክንያቶች የማምረቻ ወጪያችን አንረዋል፡፡ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች የዋጋ ጭማሪ ባለማድረጋቸው በጣም እየተጎዱ ነው፡፡ በዚህ ላይ ፋብሪካዎች የዋጋ ማስተካከያ ሳያደርጉ የችርቻሮ ገበያው ላይ የዋጋ ጭማሪ መደረጉ ትልቅ ችግር ነው የፈጠረው፤›› ብለዋል፡፡
የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የማምረቻ ወጪ ከ25 እስከ 30 በመቶ መጨመሩን የገለጹት አቶ ኃይሌ፣ ይህ ጭማሪ ሙሉ በሙሉ ወደ ሸማቹ ይተላለፉ ቢባል የሲሚንቶ ፍላጎት በከፍተኛ መጠን እንደሚቀንስ አስረድተዋል፡፡ ‹‹የሲሚንቶ ዋጋ በከፍተኛ መጠን ሲጨምር የሲሚንቶ ሽያጭ ይቀንሳል፣ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ይጎዳል፡፡ ይህ ደግሞ ሁላችንንም ችግር ውስጥ ይከተናል፡፡ የተወሰነውን ጭማሪ ፋብሪካዎች ራሳቸው፣ የተወሰነውን ሲሚንቶ ነጋዴዎች፣ የተወሰነውን ሸማቹ ኅብረተሰብ መቻል አለበት፡፡ የተጠና መፍትሔ ያስፈልገናል፤›› ብለዋል፡፡
ደርባ ሲሚንቶ የዋጋ ማስተካከያ ጥናት እያካሄደ መሆኑን የገለጹት አቶ ኃይሌ፣ ምን ያህሉን ጭማሪ ፋብሪካው ይቻል፣ ምን ያህሉን ወደ ደንበኞች ያስተላልፍ የሚለው ገና እንዳልተወሰነ ገልጸዋል፡፡
የአይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ገመቹ ዋቅቶላ (ዶ/ር)፣ የሲሚንቶ ኢንዱስትሪ በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የምንዛሪ ለውጥ፣ የፖለቲካ አለመረጋጋትና በርካታ ችግሮች ተደራርበውበት ኢንዱስትሪው በአሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው፤›› ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ አገሪቷ ውስጥ በተፈጠረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት ትልልቅ የመንግሥት ግንባታ ፕሮጀክቶች መቀዛቀዛቸውን ተናግረዋል፡፡
‹‹መንግሥት አገር በማረጋጋት ሥራ በመጠመዱ የግንባታ ሥራ ቀዝቅዟል፡፡ መንግሥት ዋና ገንቢ በመሆኑ የመንግሥት የግንባታ ወጪ ሲቀንስ በሲሚንቶ ፍላጎት ላይ መቀነስ ይታያል፤›› ብለው፣ የምንዛሪ ለውጡ የፋብሪካዎችን የማምረቻ ወጪ እንዳናረው አስረድተዋል፡፡
የግንባታ ብረት ዋጋ መናር የኮንስትራክሽን ዘርፉን በመጉዳት ላይ መሆኑን፣ በአጠቃላይ የተከሰተው የዋጋ ግሽበት በኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ በሲሚንቶ ፍጆታ ላይ ቅናሽ እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡
የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የዋጋ ማስተካከያ ሳያደርጉ በችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ ጭማሪ መከሰቱ፣ ፋብሪካዎቹ የዋጋ ማስተካከያ ሲያደርጉ በሲሚንቶ መሸጫ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ የሚፈጥር ስለሆነ፣ በኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ የጎላ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
ከፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ፋብሪካዎች ምርት በሚያቆሙበት ወቅት የማይቋረጡ ወጪዎች መኖራቸውን ገልጸው፣ በአጠቃላይ የሲሚንቶ ኢንዱስትሪውን እየተፈታተኑት ያሉት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ከአምራቾቹ አቅም በላይ ስለሆኑ ከፖሊሲ አውጪዎች ጋር ቁጭ ብሎ መመካከር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
‹‹የአይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት በሚዘጋጃቸው ዓመታዊ የሲሚንቶ ጉባዔ ላይ የሲሚንቶ ፍላጎት ለመጨመር የሲሚንቶ ዋጋ መቀነስ አለበት ብለን ስንከራከር ነበር፡፡ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የማምረቻ ወጪያቸው ከፍተኛ በመሆኑ አማራጭ የኃይል ምንጭ በመጠቀም ወጪያቸውን መቀነስ እንደሚኖርባቸው ስንመክር ቆይተናል፡፡ አሁን ጭራሽ የማምረቻ ወጪያቸው በከፍተኛ መጠን በመጨመሩ የሲሚንቶ ዋጋ ሊጨምር ነው፡፡ ይህ የሲሚንቶ ፍላጎትን ይጎዳል፤›› ብለዋል፡፡
የዋጋ ጭማሪው በሪል ስቴት፣ በመንግሥት ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክቶችና በአጠቃላይ በኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡
የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ልማት ኢንስቲትዩት ጉዳዩን እንደሚከታተለው አስታውቋል፡፡ የሲሚንቶና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃዱሽ ጥዑም፣ የድንጋይ ከሰል ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ጨምሯል መባሉ አዲስ መረጃ በመሆኑ ኢንስቲትዩቱ ለማጣራት ጥረት እንደሚያደርግ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
‹‹የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የዋጋ ማስተካከያ ሳያደርጉ የችርቻሮ ነጋዴዎች የተከሰተውን የትራንስፖርት መቆራረጥ ተገን በማድረግ የዋጋ ጭማሪ ማድረጋቸው ሕገወጥ ድርጊት ነው፤›› ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የማምረቻ ወጪያቸው ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት አቶ ሃዱሽ፣ ኢራን ውስጥ የአንድ ቶን ሲሚንቶ የማምረቻ ወጪ 30 ዶላር ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ 90 ዶላር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ይህ ሊሆን የቻለበት ዋነኛ ምክንያት የአገር ውስጥ ፋብሪካዎች በኃይል ምንጭነት የሚጠቀሙበት የድንጋይ ከሰል ከደቡብ አፍሪካ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገዛ በመሆኑ ነው፡፡ የአገር ውስጥ የድንጋይ ከሰል መጠቀም ቢችሉ ወጪያቸውን በከፍተኛ መጠን መቀነስ ይችላሉ፤›› ያሉት አቶ ሃዱሽ፣ የአገር ውስጥ የድንጋይ ከሰል ክምችቶችን ጥቅም ላይ ለማዋል ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የተለያዩ ጥናቶች እየተካሄዱ ነው፡፡ ትልቅ ፕሮጀክት በመሆኑ የመንግሥት ተሳትፎን የሚጠይቅ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ 20 የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ይገኛሉ፡፡ ዓመታዊ የማምረት አቅማቸው 17 ሚሊዮን ቶን ሲሆን፣ ዓመታዊ የሲሚንቶ ፍጆታ ደግሞ ስምንት ሚሊዮን ቶን እንደሆነ ይገመታል፡፡