fbpx

HT

ሐበሻ ታይምስ ሚዲያ

AMHARIC

የሰንደቅ አላማ እና ብሔራዊ አርማ ጉዳይ

ቀስተ ደመና ምድር ላይ የተነጠፈ እስኪመስል ድረስ አገሩን ሰንደቅ ዓላማ አድምቆታል። ወትሮ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በብዛት የሚታየው አትሌቶች ሜዳሊያ ሲያገኙ አልያም ከዓመታት በፊት እንደሆነው በሰላሳ አንድ ዓመትም ቢሆን ኢትዮጵያ የአፍሪካን ዋንጫ ስትቀላቀል ነበር። ታድያ በዚህ ጊዜ ሳቢ የሆነው ሰንደቅ ዓላማ በብዛት መያዙ ብቻ አይደለም፤ የተያዘው ሰንደቅ ዓላማ ብሔራዊ ዓርማ የሌለውና ልሙጥ መሆኑ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

አዲስ አበባን ጨምሮ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ከተሞች እንዲሁም በውጭ ሀገራት በሰንደቅ ዓላማ ደምቀው የድጋፍ ሰልፉን አድምቀውታል። ይህ የሆነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ወደስልጣን በመጡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያሳዩትና እውን ያደረጉት ለውጥ ያስደሰተው ሕዝብ ይደግፋቸው ዘንድ ድምጹንም ለማሰማትና ለመደገፍ በወጣ ጊዜ ነው። ታድያ ከአስደማሚው የሕዝብ አንድነትና የድጋፍ ሰልፍ በተጓዳኝ የሰንደቅ ዓላማው ያለዓርማ መውጣት ያሳሰባቸው ነበሩ።ሕገመንግስቱ ተጥሷልም ሲሉ የሞገቱ ነበሩ።

መዛግብት እንደሚያስረዱት፤ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለም የአራት ማዕዘን ቅርጽ ይዞ በቋሚነት ጥቅም ላይ የዋለው ከ1890ዎቹ በኋላ በተለይም በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ነው። ከዚያም በየዘመናቱ የመጡ ነገስታት በሰንደቅ ዓላማው መካከል ላይ ስርዓቱን የሚወክል ብሔራዊ ዓርማ ያኖራሉ። ከዚህም ውስጥ ዘንግ የያዘ አንበሳ፣ በዘንጉ ጫፍ ላይ መስቀልና በአንበሳው ዙሪያ አምስት  ባለአምስት ጫፍ ከዋክብት ያሉበት፣ በኋላም አንበሳውና ዘንጉ ቀርተው ከዘንጉ ጫፍ ላይ የሰንደቅ ዓላማ ምልክት ያረፈበት ዓርማ በዋናነት የሚታወሱት ናቸው።

ቆይቶ ዘንባባ እንዲሁም በደርግ ዘመነ መንግስት የዶማና የማጨድ ምስል ዓርማ ሆኖ አገልግሏል። እነዚህና ሌሎች የተለያዩ ዓርማዎች በሳምንታትና በጥቂት ዓመታት እድሜ የተለወጡበትም ጊዜ አለ። በኋላም ኢህአዴግ አገሪቷን እንደተረከበ ሁሉንም ሊወክልና ሊገልጽ ይችላል በሚል እሳቤ የኮከብ ምልክት ብሔራዊ ዓርማ ሆኖ በሕገመንግስት ተደግፎ በአዋጅ ፀድቆ ስራ ላይ ውላል።

«ብሔራዊ ዓርማ የሌለበት ልሙጡ ሰንደቅ ዓላማ በደርግ እንዲሁም በኃይለሥላሴ፤ አልፎም በኢህአዴግ የሽግግር ዘመን አገልግሏል» ያሉን ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህግና አስተዳደር ትምህርት ኮሌጅ የሰብዓዊ መብት ረዳት ፕሮፌሰር ናቸው። በገለጻቸው ብሔራዊ ዓርማ እና ሰንደቅ ዓላማ እንደሚለያዩና ሰንደቅ ዓላማ አገርን ሲወክል፤ ዓርማ ግን ስርዓቶቹን እንደሚያሳይ ያስረዳሉ።

ዶክተር ሲሳይ መለስ ብለው ሲያስቃኙ በየዘመኑ የነበረው ብሔራዊ ዓርማ እንደየዘመኑ ቅሬታ ይነሳበት ነበር። በኃይለሥላሴ ዘመን የነበረው የአንበሳ ምስል በተለያየ ኅብረተሰብ የተለያየ ትርጓሜ መስጠቱ ብዙዎች እንዳይቀበሉት አድርጓል። እንደዛው ሁሉ በደርግ ዘመነ መንግስትም የካፒታሊስት ስርዓትን የሚቀበሉ ሰዎች በሰንደቁ ላይ ያለው ዓርማ ወካይ እንዳልሆነ ይገልጹ ነበር።

እንደውም ከነዚህ አንጻር አሁን ያለው የኮከብ ብሔራዊ ዓርማ ብዙ ልዩነት ባለመፍጠር የተሻለ እድል ያለው መሆኑን ይጠቅሳሉ። ነገርግን በተለያዩ ከተሞች የድጋፍ ሰልፉን ተከትሎ ሕዝቡ ይዞ የወጣው ሰንደቅ ዓላማ ብሔራዊ ዓርማ የሌለው መሆኑ፤ ብሔራዊ ዓርማው ተቀባይነት እንዳላገኘ ያመላክታል። «ልሙጡን የእኔ ነው ብለው ያስቡ ስለነበር ኮከቡ ሲጨመር ብዙዎች ቅሬታ ነበረባቸው። መንግስት በሕዝብ ተመርጦ ነውና ያለው ሕዝብ ያልፈለገውን መተው አለበት። ሕገመንግስቱ ስለብሔራዊ ዓርማ መኖር ከተናገረ በዛ ሁኔታ አዋጁን ብቻ ውድቅ ማድረግ አይቻልም። ስለዚህ ከሕገመንግስቱ ጀምሮ መሻሻል አለበት» ይላሉ።

በሰንደቁ መካከል ያለውን ብሔራዊ አርማ የሚፈልግና የሚቀበል ሊኖር ይችላል። ይህንንም በማመዛዘን አብላጫው የኅብረተሰቡን ስሜት አይቶ፣ ከላይ እስከ ታች ተደራሽ በሆኑ ሁኔታ አስመርጦ የሕዝብን ፍላጎት ማሟላት ከመንግሥት የሚጠበቅ መሆኑንም ይገልጻሉ።

ሰንደቅ ዓላማውን ያለብሔራዊ ዓርማ ይዞ መንቀሳቀስ አያስቀጣም ወይ? ስንል ጠየቅን። አቶ ሲሳይ እንዳሉት «አንድን ሰንደቅ ዓላማ ማራከስ፣ ከሚገባው ክብር በታች ማድረግና መቅደድ በወንጀል ያስጠይቃል። ከዛ ውጪ ግን ኮከብ ያለበትን ሰንደቅ ዓላማ ይዘህ ካልዞርክና ካላውለበለብክ የሚል ሕግ የለም። በመንግስት ተቋማትና መሰል ድርጅቶች ሊውለበለብ ይችላል። ሕዝብ ግን የሚፈልገውን ይዞ መንቀሳቀስ፣ ቤቱ ማስቀመጥና በአደባባይ ማውጣት ይችላል። በዚህ የኔ ሰንደቅ ዓላማ ይህ ነው እያለ ነው። ይህ ወንጀል ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፤ የሚፈልገውን ስሜት መግለጽ መብቱ ነው» ይላሉ።

ሕዝቡ በነጻነት የሚፈልገውን መግለጽ መጀመሩ ትልቅ ለውጥ መሆኑንም ሳይገልጹ አላለፉም። ይሁንና ህጋዊ ያልሆነ ሰንደቅ ዓላማ ተውለብልቧል የሚል መረጃ የሚያቀብሉ መገናኛ ብዙኃንም ሳይቀሩ ልክ አለመሆናቸውን ይናገራሉ «ይህ በመሰረቱ ስህተት ነው። ልሙጡ ባንዲራ የዚህች አገር ሰንደቅ ዓላማ ነው። አገሪቱን ወክሎ በሊግ ኦፍ ኔሽን የተመዘገበውም ልሙጡ ባንዲራ ነው» ሲሉም ወደኋላ ታሪክን አጣቅሰው ያስታውሳሉ።

አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ናቸው። የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ በአግባቡ በሕግ የተደነገገ ስርዓት ያለው በመሆኑ እስከአሁንም ድረስ በዛ መሰረት አገልግሏል ይላሉ። ታድያ በአሁኑ ሰዓት ያለው ብሔራዊ ዓርማ የብሔር ብሔረሰቦች እና ሃይማኖቶች እኩልነት ብሎም በአንድነት የመኖር ያለን ተስፋ የሚያሳይ እንጂ አንድነት ላይ ሌላ ዓላማ ያለው አለመሆኑንም ይጠቅሳሉ።

በተለያዩ ከተሞች የተደረጉ ሰልፎችን ተከትሎ ጥቂት የማይባሉት ጋር የታዩ ብሔራዊ ዓርማ የሌላቸው ሰንደቅ ዓላማዎች መታየታቸውን አቶ ጴጥሮስም ሳይታዘቡ አልቀሩም። ታድያ በንግግራቸውም «እንደ ኢትዮጵያዊነት ስርዓት ያለን ሕዝቦች ነን፤ ሕግ ሲወጣ እንዲሁም ሲሻሻል የምንከተለው ስርዓት አለ፤ ያንን ተከትሎ ጥያቄ ካለ አቅርቦ ውይይት ተደርጎ በዚህ በዚህ ምክንያት ነው ዓርማውን ያልፈለግነው የሚል አሳማኝ ምክንያት አቅርበው በውይይት መፍታት ይቻላል። አብዛኛው ሰው የሚያምንበት ከሆነ የማይለወጥ ነገር አይኖርም» ብለዋል።

ያ ሁሉ ሕዝብ ታድያ ብሔራዊ ዓርማውን ያልተቀበለበት ምክንያት ይኖራል። ይህ ክፍተት እንደ አቶ ጴጥሮስ እምነት፤ የሰንደቅ ዓላማውን እንዲሁም የብሔራዊ ዓርማውን ነገር በሚገባ ካለመረዳት የመነጨ ነው። «ዓርማው ብሔረሰቦች አብረው ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንጸባርቅ ስለመሆኑ እኛም በሚገባ አላስረዳንም፤ ከመገናኛ ብዙኅን ጋር እዚህ ላይ አልሠራንም። ችግሩ ይህ ከሆነና በዛ በኩል ክፍተት ካለ እሱን ማየት ይኖርብናል» ሲሉም ገልጸዋል።

« አዋጁ የሰንደቅ ዓላማን አያያዝ በሚመለከት ካስቀመጠው ውጪ መጠቀም ያስጠይቃል በሚል በዝርዝር አስቀምጧል። ዋናው ነገር ግን መቅጣት ሳይሆን አሁን በያዝነው የመደመር መንፈስ መዝለቅና አንድነት ላይ እየሠራን ሳለ የአንድነታችን ምልክት የሆነው ሰንደቅ ዓላማና ብሔራዊ አርማ ለምን እንዲቀየር ተፈለገ የሚለው ላይ ውይይት ማድረግ ነው» ብለዋል።

ከዚሁ ጋር አያይዘው ለብሔራዊ መግባባት ቅድሚያ መስጠት እንደሚያስፈልግና በሁሉም ነጥብ እየተለያዩ መሄድ ጠቃሚ እንዳልሆነና በዛ መሰረት ተደማምጦ መፍትሄ እናምጣ የሚለውን መያዝ እንደሚሻል ይገለፃሉ።

አቶ ንጉሱ ጥላሁን የአማራ ክልል የኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በዚህ ጉዳይ ላይ ተጠይቀው ለተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ምላሽና አስተያየት መስጠታቸው ይታወሳል። በምላሻቸውም ሕዝብ ፍላጎቱን እስከአሁን ሊገልጽ ያልቻለውና የፈለገውን ሰንደቅ ዓላማ በስፋት ይዞ ያልወጣበትን ምክንያት ሲገልጹ፤ «እኛ ኅብረተሰቡ ማንኛውንም ነገር እንዲያደርግ አልፈቀድንለትም፤ ተፅዕኖ አሳድረንበታል። ስለዚህ ሕገ መንግስታዊ በሆነው ሰንደቅ ዓላማ ላይ አልተግባባም፣ አልተቀበለንም ማለት ነው» ብለዋል። ዴሞክራሲ ማለት በሁሉም ጉዳይ ላይ ተመካክሮ አብዛኛው ይሁን ያለውን መቀበል ነውና ይህ ጉዳይ የሕዝቡን ውይይት መጠየቁ አይቀሬ ነው ማለታቸው ይታወሳል።

ዜና ሐተታ
ሊድያ ተስፋዬ – የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram