fbpx

HT

ሐበሻ ታይምስ ሚዲያ

AMHARIC

የሩሲያው ዓለም ዋንጫ አስገራሚ ክስተቶች

ከሰኔ 7 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በሩሲያ አስተናጋጅነት ሲካሄድ የቆየው 21ኛው የዓለም ዋንጫ ዛሬ ፍጻሜውን ያገኛል።

በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ በሜዳና ከሜዳ ውጭ የተለያዩ ያልተጠበቁ ክስተቶች ተስተናግደዋል።

ያለፈው ዓለም ዋንጫ አሸናፊ የነበረችው ጀርመን ከምድቧ ሳታልፍ ከዘንድሮው ውድድር በጊዜ መሰናበቷ የመጀመሪያው ያልተጠበቀ ክስተት ነበር።

ጀርመን በዓለም ዋንጫው በሜክሲኮና በደቡብ ኮሪያ ተሸንፋ ስዊድንን አሸንፋ ከምድቧ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ነበር ከሩሲያ የተሰናበተችው።

በምድብ ጨዋታ እንግሊዝ ፓናማን ስድስት ለአንድ ባሸነፈችበት ጨዋታ ላይ የፓናማው ፊሊፕ ባሎይ አዲስ ታሪክ ለአገሩ አስመዝግቧል።

ፊልፕ ባሎይ በዓለም ዋንጫው ለመጀመሪያ ጊዜ ለተሳተፈችው ፓናማ በዓለም ዋንጫ የመጀመሪያውን ጎል ያስቆጠረ ሲሆን ይህም ለፓናማ ደጋፊዎች ትልቅ ደስታን የፈጠረ ነበር ማለት ይቻላል።

ስፔንና ፖርቹጋል ባደረጉት ጨዋታ ፓርቹጋላዊው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር የዓለም ዋንጫውን የመጀመሪያ ሀትሪክ የሰራ ሆኖ ተመዝግቧል። በዓለም ዋንጫ ታሪክ በእድሜ አንጋፋ በመሆን ሶስት ግቦችን ያስቆጠረ ተጫዋችም ለመሆን በቅቷል።

እንግሊዝ እና ቤልጂየም ባደረጉት ግጥሚያ አድናን ያኑዛይ የቤልጂየምን የማሸነፊያ ጎል ካስቆጠረ በኋላ ቤልጂየማዊው አጥቂ ሚቺ ባትሹዋይ ደስታውን ለመግለጽ ኳሱን ድጋሚ ወደ መረቡ ለመምታት ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቶ ኳሱ የግቡን ቋሚ ገጭቶ የባትሹዋይን ፊት የመታችበት አጋጣሚ አነጋጋሪ የሚባል የዓለም ዋንጫው ክስተት ነበር።

በኳሱ ፊቱን የተመታው ሚቺ ባትሹዋይ መጠነኛ ህክምና ተደርጎለት ወደ ጨዋታው ተመልሷል።

አርጀንቲና በመጨረሻ የምድብ ጨዋታዋ ናይጄሪያን ባሸነፈችበት ወቅት የአርጀንቲና የቀድሞ ተጫዋች ዲያጎ ማራዶና የመሐል ጣቶቹን አውጥቶ የተሳደበት አጋጣሚ የእግር ኳስ አፍቃሪውን ያሳዘነ ተግባር ሆኖ አልፏል።

ዲያጎ ማራዶና ለፈጸመው ተግባር ይቅርታ ቢጠይቅም ተግባሩ እዳ አምጥቶበታል። ይኸውም እጩ ከነበረበት የፊፋ የበጎ ፈቃድ አምባሳደር እንዲቀነስ ሆኗል።

በተንቀሳቃሽ ምስል የተደገፈ ዳኝነት በዓለም ዋንጫ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ የተደረገው በዘንድሮው ውድደር ላይ ነው።

በግብጽ፣ሴኔጋል፣ሞሮኮ፣ናይጀሪያና ቱኒዝያ የተወከለችው አፍሪካ ከምድባቸው አለማለፋቸው አፍሪካዊያኖችን ያሳዘነ ትልቁ ክስተት ነበር።

ፈረንሳይና አውስትራሊያ ባደረጉት ጨዋታ ፈረንሳይ ፍጹም ቅጣት ምት ያገኝቸው በዚሁ ቴክኖሎጂ በተላለፈው ውሳኔ መሰረት ነው።

በተንቀሳቃሽ ምስል በተደገፈ ዳኝነት የሚሰጡ የፍጹም ቅጣት ምቶች በጣም አከራካሪና አወዛጋቢም ነበሩ ማለት ይቻላል።

በዘንድሮው ዓለም ዋንጫ 28 የፍጹም ቅጣት ምቶች የተሰጡ ሲሆን ይህም በዓለም ዋንጫው ታሪክ ትልቁ የሚባል ነው።

በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ከጨዋታዎች ውጪ ሌሎች አስገራሚ ክስተቶችም ታይተዋል።

የጃፓን ብሔራዊ ቡድን ደጋፊዎች ከእያንዳንዱ ጨዋታ በኋላ በስታዲየሙ የሚገኘውን ቆሻሻ በማጽዳት ሲያከናውኑ የነበረው ተግባር ብዙዎችን የሳበ መልካም ተግባር ነበር።

በተለይም በጥሎ ማለፉ ጃፓን በቤልጂየም በተሸነፈችበት ጨዋታ ላይ ሁለት የጃፓን ደጋፊዎች ቆሻሻ እየለቀሙ ፌስታል ውስጥ ሲከቱ የተነሳው ምስል ለጃፓን ደጋፊዎች አድናቆት ያስቻረ ነበር።

በሌላ በኩል ኡራጓይና ግብጽ ባደረጉት ጨዋታ ከስታዲየሙ ውጪ ባለው ግዙፍ ስክሪን በዊልቸር የሚንቀሳቃስ ግብጻዊ ዜጋን የኮሎምቢያና የሜክሲኮ ደጋፊዎች ዊልቸሩን ከፍ አድርገው ደጋፊው ጨዋታውን እንዲከታታል ያደረጉለት ድጋፍ የብዙዎችን ቀልብ የሳበ አጋጣሚ ሆኖ ተመዝግቧል።

ኮሎምቢያዊው ደጋፊ ሴዛር ዳዛ መስማት የተሳነውንና ማየት የማይችለውን ጓደኛው ጆሴ ሪቻርድ ካሌሆን ለመርዳት የምልክት ቋንቋ ትምህርት በመማርና በእጁ ንክኪ የተለያዩ ምልክቶችን በመፍጠር ጨዋታውን እንዲከታተል የሰጠው ድጋፍ አድናቆት አስችሮታል።

በሌላ በኩል የሴኔጋል ተጫዋቾች ልምምድ በሚያደርጉበት ወቅት በቡድን ሆነው ያሳዩት የነበረው የዳንስ ትርኢት አዝናኝ የሚባል ነበር።

በአጠቃላይ ከላይ የተጠቀሱት ክስቶች የዓለም ዋንጫው ልዩ ክስተቶች ናቸው።

ዛሬ በዓለም ዋንጫው የፍጻሜ ጨዋታ ፈረንሳይና ክሮሺያ በእግር ኳስ ትልቁን ሽልማት ለማግኘት ይጫወታሉ።

በሩሲያ አስተናጋጅነት ከሰኔ 7 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የነበረው 21ኛው የዓለም ዋንጫ ዛሬ ይጠናቀቃል።

81 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ሉዚኒስኪ ስታዲየም ከምሽቱ 12 ሰአት ላይ ክሮሺያና ፈረንሳይ ይገጥማሉ።

ከቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ተገንጥላ ነፃ ሀገር ከሆነች የ26 ዓመት እድሜ ያላት ክሮሺያ የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ በመድረስ በእግር ኳስ ታሪኳ ትልቁን ውጤት አግኝታለች።

በዓለም ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ከመመራት ተነስታ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድንን ሁለት ለአንድ በማሸነፍ ለፍጻሜ ቀርባለች።

የ51 ዓመቱ የክሮሺያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዝላትኮ ዳሊች በዓለም ዋንጫ ፍጻሜ የምናገኘው ውጤት የትኛውም ይሁን የክሮሺያ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ህዝብ እጅግ በጣም ደስተኛ እንደሚሆን ገልጸዋል።

በፍጻሜው ጨዋታ ክሮሺያ ካሸነፈች የአገሪቷ ህዝብ ደስታውን እንዴት እንደሚገልጽ አላውቅም በክሮሺያ ጎዳናዎች በሚኖረው የደስታ አገላለጽ “የመሬት መንቀጥቀጥ” ሊነሳ ይችላል ሲሉ የህዝቡን ስሜት ተናግረዋል።

ባለፉት 10 ዓመታት የክሮሺያ ብሔራዊ ቡድን ትልቁ አጥቶት የነበረው ነገር እንደ ቡድን መጫወት አለመቻልና ጥቂት በሚባሉ ብቃት ያላቸው ተጨዋቾች ላይ መንጠልጠሉ ነው ብለዋል።

ብሔራዊ ቡድኑን ከተረከብኩ ጀምሮ ያመጣሁት ለውጥ ቡድኑ ጠንካራ መንፈስ እንዲኖረው ማድረግና እንደ ቡድን እንዲጫወት ማደርግ ነው በማለት አስረድተዋል የ51 ዓመቱ ክሮሺያዊ አሰልጣኝ።

የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ብዙ እንግዳ ነገር አሳይቶናል በፍጻሜው ጨዋታ ምን ሊፈጠር አይታወቅም ብለዋል።

እ.አ.አ በ1998 ዓለም ዋንጫ ፈረንሳይ የዓለም ዋንጫውን አስተናግዳ ራሷ አሸናፊ ስትሆን የብሔራዊ ቡድኑ አምበል የነበረው የአሁኑ የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዲዲየር ዴሻምፕስ ናቸው።

የ49ኝ ዓመቱ አሰልጣኝ በቡድኔ ውስጥ ያለው ጠንካራ መንፈስ ተራራን ማንቀሳቀስ የሚችል ነው ያሉ ሲሆን ብሔራዊ ቡድኑ ወጣት ተጫዋቾች ከመሆናቸው አንጻር በቀጣይ አራት ዓመት ውሰጥ ብሔራዊ ቡድኑ ከዚህ በላይ ጠንካራ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ለመሆን የሚያስችለንን እድል ፈጥረናል ግን አላሳካነውም ነገር ግን ዛሬ ግባችን ለማሳካት ቡድናቸው እንደሚጫወት ተናገረዋል።

በትኩረት፣በራስ መተማመንና በመረጋጋት ከተጫወቱ የዓለም ዋንጫን ማግኘት እንደሚችሉ ለተጫዋቾቻቸው እንደነገሯቸው ገልጸዋል።

የክሮሺያ ተጫዋቾች በትልልቅ ክለቦች ውስጥ የረጅም ጊዜ ልምድ አላቸው እንደ ብሔራዊ ቡድን በደንብ ተቀናጅተዋል ያም ቢሆን በዓለም ዋንጫው እስካሁን ብዙ ልምድ ካላቸው ቡድኖች ተጫውተናል ብለዋል።

ፈረንሳይና ክሮሺያ አስካሁን አምስት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ፈረንሳይ ሶስት ጊዜ ስታሸንፍ ሁለት ጊዜ አቻ ወጥተዋል።

በዓለም ዋንጫ መድረክ ሲገናኙ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን እ.አ.አ በ1998 ፈረንሳይ ባስተናገደችው የዓለም ዋንጫ በግማሽ ፍጻሜው ፈረንሳይ ክሮሺያን ሁለት ለአንድ አሸንፋ ወደ ፍጻሜ አልፋ የዋንጫው ባለቤት ሆናለች።

ፈረንሳይ ከ20 ዓመት በኋላ ሁለተኛዋን ዓለም ዋንጫ ለማንሳት ክሮሺያ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ዋንጫን ለማንሳት ይፋለማሉ።

የ43 ዓመቱ አርጀንቲናዊ ኔስቶር ፒታና የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ በመሐል ዳኝነት ይመራሉ። አርጀንቲናዊው የቀድሞ የፊልም ተዋናይ በሩሲያና በሳዑዲ አረቢያ መካከል የተደረውን የዓለም ዋንጫ የመክፈቻ ጨዋታ መምራታቸው የሚታወስ ነው።

የዓለም ዋንጫውን ኮከብ ግብ አግቢነት እንግሊዛዊው ሀሪ ኬን በስድስት ጎሎች እየመራ ሲሆን በቅርብ ርቀት የሚከተሉት ተጫዋቾች ከዚህ በኋላ ጨዋታ የማያደርጉ በመሆኑ የኮከብ ግብ አግቢነቱን ሽልማት ይወስዳል ተብሎ ይጠበቃል።

የዓለም ዋንጫው ኮከብ ተጫዋችነት ሽልማት ወደ ፈረንሳዊው ኬይለን ምባፔ ወይም ክሮሺያዊ የመሐል ክፍል ተጫዋች ሉካ ሞድሪች ያመራል የሚለው የእግር ኳስ ተንታኞች ግምት ነው።

ቤልጂየማዊው ኤደን ሀዛርድና ፈረንሳዊው የመሐል ተጨዋች ንጎሎ ካንቴ ኮከብ ተጫዋች የመሆን እድል አላቸው እየተባለ ይገኛል።

የሁለቱ ቡድኖች ከመጀመሩ 30 ደቂቃ በፊት የመዝጊያ ስነ ሰርአት የሚኖር ሲሆን አሜሪካዊው ዘፋኝና የፊልም ተዋናይ ዊሊ ስሚዝ ከአሜሪካዊው ኒኪ ጃምና ከኮሶቮዋዊቷ ኢራ እስትሪፊ ጋር የዓለም ዋንጫውን ይፋዊ መዝሙር “ሊቭ ኢት አፕ”ን ያቀናቅናሉ።

በተጨማሪም የደቡብ ኮሪያው የሙዚቃ ባንድ ኢኦኤክስ ስራቸውን በማቅረብ በሉዚኒስኪ ስታዲየም ታዳሚዎችን ያዝናናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram