fbpx

የምስራቅ ወለጋው ፓስተር ውርደት

ከኢየሱስ በፊት ቢዝነስ ለማግኘት የሚሯሯጡ ነቢያቶች… | አሳዬ ደርቤ 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሐይማኖትን የመደበቂያ ዋሻ በማድረግ የሚሽሎከለኩ ተኩላዎች እየበዙ ነው፡፡ እነዚህ ተኩላዎች በፈጣሪ ስም የሚነግዱ ሌቦች ሲሆን አንዳንዶቹ በህጋዊነት ቀሪዎቹ ደግሞ በድፍረት የነቢይነትን ካባ የደረቡ ናቸው፡፡

ተኩላዎቹ በተከታዮቻቻው ላይ የሚፈጽሙትን ማታለል ለማወቅ ወደ ዩ-ቲዩብ ብታገቡ የምታገኙት ድራማ ነፍ ነው፡፡

‹‹በጫማ ጥፊ የምዕመናኑን አንገት እያጣመመ አጋንንትን የሚያስወጣ ነቢይ….. የቀኝ እግርን የሚያስረዝም ነቢይ…. የእግዚአብሔርን ድምጽ በሞባይሉ የቀዳ ነቢይ፣ ‹ደመቀ መኮነን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር እንደሚሆን ኢየሱስ ሹክ ብሎኛል› የሚል ነቢይ…… ‹መስቀል አደባባይ ላይ ቦንብ እንደሚፈነዳ አስቀድሜ አውቄ ነበር› የሚል ነቢይ…. ‹የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ‹በርትታችሁ አጥኑ› በማለት ፈንታ እኔ ከጸለይኩላችሁ ወደ ዩኒቨርስቲ ትገባላችሁ› የሚል ነቢይ….. ‹በዚህ ቀን ጸሐይ ስለማትወጣ አገራችን ጨልማ ትውላለች› የሚል ነቢይ…. ‹የባንክ ደብተሮቻችሁ ላይ በመጸለይ ያላችሁን ገንዘብ አባዛላችኋለሁ› የሚል ነቢይ….. በሞባይሉ ደውሎ ፈጣሪን የሚያወራ ነቢይ……. ምዕመናኑን ሊያጠምቅ ሄዶ በአዞ የተበላ ነቢይ…. ወዘተ ወዘተ ወዘተ (እንዘርዝረው ብንል ልንጨርሰው አይቻለንም፡፡)

በዚህ ሳምንት ደግሞ በምስራቅ ወለጋ አካባቢ የሚኖር አንድ ‹ፓስተር ነኝ› የሚል ግለሰብ ‹‹የሞተ ሰው አስነሳለሁ›› ብሎ መቃብር ካስቆፈረ በኋላ አስከሬኑን በስሙ እየጠራ ‹ተነስ› ቢለው፣ ቢወዘውዘው፣ እላዩ ላይ ተጋድሞ ቢያቅፈው ሊነሳ ስላልቻለ በነቢዩ ድርጊት የተበሳጩት የሟች ቤተሰቦች ባስቆፈረው መቃብር ውስጥ ነቢዩን ለመቅበር ሲያስቡ ፖሊስ ደርሶ ወደ ወህኒ-ቤት እንዳስገቡት እየሰማን ነው፡፡

ይሄም ሆኖ ግን ‹‹ነቢይ በአገሩ አይከበርም›› የሚለው ትንቢት ሃገራችን ላይ እውን ባለመሆኑ እነዚህ ሃሳዊ ነቢያት ከእነ አስቀያሚ ስራቸው ታፍረውና ተከብረው እየኖሩ ነው፡፡ ነቢያት ተቢዮዎቹ የሚሰሩት ድራማ ሐይማኖቱን ከማስናቅና ተከታዮቹን ከማሸማቀቅ የዘለለ ፋይዳ እንደሌለው ግልጽ ቢሆንም የሐይማኖቱ ተከታዮች እነዚህን አጭበርባሪዎች ሲያወግዙ አይታዩም፡፡ ሌላውም ሊተቻቸው ሲነሳ ሐይማኖታቸው የተነካ ስለሚመስላቸው በንደት ይበግናሉ፡፡

እንደ እኔ እምነት ግን አጭበርባሪ ነቢያትን መተቸት ሐይማኖቱን መንካት አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም የፕሮቴስታንት ሐይማኖት ከሌሎች ሐይማኖቶች በተለዬ መልኩ የሚያስተቸው ነገር አለው ብዬ አላስብም፡፡ ይልቅስ ከሌሎች እምነቶች በተለዬ ሊመረመር የሚችለው ሐይማኖቱ ሳይሆን ነቢያቱ ናቸው፡፡

‹‹ለምን?›› ብትሉኝ በቤተ-እምነት ውስጥ ተደብቀው የሚያጭበረብሩ ተኩላዎች በሁሉም ሐይማኖቶች ውስጥ መኖራቸው የሚካድ አይደለም፡፡ ነገር ግን አጭበርባሪዎቹ በፕሮቴስታንት ውስጥ እንዳሉት ሌቦች ድፍረትም ሆነ ዓይን-አውጣትነት የላቸውም፡፡

ቢያምታቱም በስውር እንጂ በትልቅ አዳራሽ ውስጥ የተሰበሰበ ህዝብና የተገጠመ ካሜራ እያያቸው አይደሉም፡፡ ድፍረታቸውም አስከሬን አስነሳለሁ እስከማለት የሚደርስ አይደለም፡፡

የእኒህኞቹ ግን የተለዬ ነው፡፡ በግላጭ ከሚሰሩት ድራማ ውስጥ ተራራ የሚያክል ባዶ ድፍረት እንጂ የሰናፍጭ ቅንጣት ታክል እምነት አይገኝም፡፡ ምክንያቱም ከመጀመሪያው ወደ ሐይማኖቱ የሚገቡት ኢየሱስን ለማግኘት ሳይሆን ቢዝነስ ለማምረት ነው፡፡

ትናንት በአርቲስትነቱ የምናውቀው ‹‹ጌታ ጠራኝ›› ብሎ ወደ አማኝነት ከተሸጋገረ በኋላ ሳምንት እንኳን በጽሞና ሳይጸልይ የነቢይነትን ጸጋ ደርቦ ‹‹ፈጣሪን በሞባይሌ ቀዳሁት›› ሲልህ አምላኩንም ሆነ ምዕመናኑን አይፈራም፡፡

ምዕመናን ደግሞ ወደ አምልኮ ቦታዎች ሲሄድ ሐጢያት የሚሰራበትን ጭንቅላቱን ቤቱ ውስጥ አስምጦ በመሆኑ ተኩላዎቹ ያሻቸውን ነገር ሁሉ ቢለፈልፉ ‹‹አሜን›› ባይ እንጂ ‹‹ለምን›› ባይ የለባቸውም፡፡ ፈጣሪ በእነዚህ በስሙ ለሚነግዱ ሰዎች መዓቱን ካሆነ በቀር ምህረቱን የማይልክ ቢሆንም ሸማቹ ምዕመናን ይሄንን የሚያስብበት አቅም የለውም፡፡ እናም የነቢዩ ድፍረት የምዕመናኑ አላዋቂነት ሆኖ ያርፋል፡፡

‹‹ሳይታመም ተፈውሰሃል፣ ሳይሻለው ድነሃል›› ሲሉት ‹‹አሜን›› የሚል አንደበት እንጂ የሚጠራጠር ጭንቅላት የለም፡፡
‹‹አካውንትህ ተባዝቶልሃል›› ሲባል ‹‹የባንክ አካውንት አለኝ ወይ?›› ብሎ ማሰብ የለም፡፡

‹‹ቀኝ እግርህ ረዝሞልሃል›› ሲባል የነቢዩ ቃል እንድሳካ ግራ እግሩን መሰብሰብ እንጂ ማሰብ የለም፡፡

‹‹የሞተ ልጅህን አስነሳልሃለሁና መቃብሩን ቆፍርልኝ›› ሲባል ዶማ ፍለጋ መሯሯጥ እንጂ ‹‹የሞተን ሰው ማስነሳት የሚችል ነቢይ የመቃብር አፈር ማንሳት አይቃተውምና ‹‹በኢየሱስ ስም ደርምሰህ ውጣ በለው!›› ብሎ መሞገት የለም፡፡

ከዚህ ባለፈ ደግሞ አንድ እናትና አባቱን ሊያከብር የሚገባው የ12 ዓመት ህጻን ‹‹ነቢይ›› የሚል በርኖስ ደርቦ የእናቱንና የአባቱን ሐጢያት ሲዘረዝር ‹‹አሜን›› ማለት እንጂ ‹‹እግዚኦ መሃረነ ክርስቶስ›› ማለት አይታሰብም፡፡
.
እናም የተከበራችሁ ምዕመናን በኢየሱስ ስም ቢዝነስ የሚሰሩትን ሌቦች ከመምከር ይልቅ እናንተን መምከር ይቀላልና…
ወደ አምልኮ ቦታዎች ሄዳችሁ ከሰባኪው እግር ስር ስትቀመጡ ሀጢያታችሁን ለማሰረይ እንጂ ጭንቅላታችሁን ለማሰረዝ አይሁን፡፡

እስካሁን ካየነው ተነስተን ስንናገርም በሃሰተኛ ነቢያቱ ከተፈወሱት ይልቅ የቀወሱት ይበልጣሉና ‹ምርምር-አልባ እምነታችሁ› ለአምልካችሁ እንጂ ለነቢያቶቻችሁ አይሁን፡፡

የመዳን ተስፋችሁን፣ የመበልጸግ ህልማችሁን፣ የመኖር ፍላጎታችሁን፣ ደስታ መሻታችሁን ሁሉ ከደላሎች አንሱና ለፈጣሪያችሁ አስረክቡት፡፡

ከዚያም….. ያለምንም ማስታወቂያና ያለ አንዳች ክፍያ የልብ ንጽህናችሁንና መሻታችሁን ብቻ በማየት የምታሙኑት ፈጣሪ ይሰጣችኋል፡፡ ያውም ከምትፈልጉት ነገር ጋር የሚያስፈልጋችሁንም ጭምር አክሎ!
‹‹ቃለ ህይወት ያሰማልን!›› ማለት ይቻላል፡፡  DireTube

ቪዲዮውን ከታች ይመልከቱ

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram