fbpx

የማይነበበው የህወሓት ዜና!

የማይነበበው የህወሓት ዜና!  | ሬሞንድ ሃይሉ 

ህወሓት ቤቱን ዘግቶ እየመከረ ነው፡፡ መገናኛ ብዙሃን የፓርቲው የመወያየ አጅነዳ የሰሞኑን የኢህአዴግ ውሳኔዎች ላይ መመከር መሆኑን እየለፈፉ ነው፡፡ እውነት ነው ህወሓት ፌደሬሽኖች ህልው ባደረጓት ኢትዮጵያ ውስጥ የትግራይ ተወካይ በመሆኑ ስለአልጀርሱ ስምምነት ከማንም በላይ ሊጨነቅ ይገባዋል፡፡

ለአብዮታዊ ዲሞክራሲ ማበብ ሲሉ ተሰዉ በርካታ ጓዶች ያሉት በመሆኑም ኢህአዴግ ቤት ያለውን የከፊል ሌበራሊዝም ሀሳብ ሲሰማ ግድ የላችሁም ልምከርበት ቢል አይፈረድበትም፡፡ ህወሓት ድንገት ቤቱን ዘግቶ ከኢህአዴግ ቤት የመነነው ግን ለዚህ ብቻ ነው ብሎ ማሳብ የዋህነት ነው፡፡

ይህ ቢሆን የኢህአዴግ ምክር ቤት ጥናት አጥነትን እንወስን ብሎ በገባባት የሌበራሊዝም ጉዳይ የጠራው ድንገተኛ ስበሰባ ከአንድ ቀን የበለጠ ጊዜ ባልኖረው ነበር፡፡ እኔን ይወክላሉ ብሎ በመረጣቸው ሰዎች ድጋፍ የፀደቀው የከፊል ሌበራላይዜሽንና የአልጀርስ ስምምነትን ያለቅደመ ሁኔታ መቀበልም እንደ ትልቅ አጅንዳ ተቆጥሮ የክተት ጥሪ ባልታወጀበ፡፡

ህወሓት ቤት አንዳች የተረበሸ ነገር አለ፡፡ ይህ ነገር ምን ሊሆን እንደሚችል መገመቱም ከባድ አይመስልም፡፡ የኢህአዴግን ርዕዮተ አለም መርጠው ተከታዮቻቸውን ፖለቲካ ሲያሰጠኑ የኖሩት የቀድሞ ታጋዮች እየሆነ ባለው ነገር ደስተኛ አይደሉም፡፡ እንዳንዶቹ እንደውም ወንድሞቻችን የሞቱለትን መስመር አሳልፈን ከምንሰጥ ሞትን እንመርጣለን የሚል የመረረ አቋምን ስለማያዛቸው እየተወራ ነው፡፡

ወንድሞቻቸው የሞቱለት አቋም ምንድን ነው? ኢህአዴግ ዝንታለም አብዮታዊ ፓርቲ ሁኖ እንደማይኖር እራሱም ደጋግሞ ሲነግረን ኑሯል፡፡ የልማታዊ መንግስት ዕሳቤውም በጊዜ ሂደት እንደሚከስም ተናግሯል፡፡ እንዲህ ከሆነ የፓርቲያቸው ርዕዮተ አለም በከፊል መለወጥ ለምን ያንገበግባቸዋል? ምላሹ ብዙ መላምቶች እንድንሰነዝር ያስገድደናል፡፡

የመጀመሪያው መላምት ከፊል ሌበራሊዝምን በዚህ ጊዜ መከተል ወቅቱን እንዳልጠበቀ ዝናብ በእኛ ዘመን የተመዘገቡ ስኬቶችን ሁሉ ያወድምብናል ከሚል ዕሳቤ ይመነጨል፡፡ ሁለተኛው በአንፃሩ ዕድሜያችንን የሰዋንለት ትግል ከዕጃችን ለምን ወጣ በሚል የታሪክ መብሰልሰል የተገራ መሆኑ አያከራክርም፡፡ ሦስተኛው ደግሞ የአዲሱ የኢህአዴግ አመራር ህዘበኛ የሆነ አቋም ማራመድ ወንድሞቻችን የሞቱለትን ትግል ገደል ከትቷታል በሚል የታጀበ ይመስላል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም የህወሓት አመራሮች በደማችን ፅፈን ለህዝባችን አበረከትንለት የሚሉት ህገ-መንግስትም በአጭር ጊዜ ውስጥ ከአገልግሎት እየወጣ መሄዱ ቁጣቸውን ጣራ አስነክቶታል፡፡

እነዚህ አራት ጉዳዮች በቁም ሲታዩ ተራ የፖለቲካ ዕቃ ዕቃ ጨዋታ ይመስሉ እንጅ መለያየትን የሚወልዱ ናቸው፡፡ መለያየቱ በህወሓት ውስጥ ከዚያም ከፍ ሲል እንደ ኢህአዴግ ሊሆን እንደሚችል ዕሙን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ኢህአዴግን አስኳል የሌለው እንቁላል ያስመስለዋል፡፡

አንዳንድ ወገኖች ህወሓትን እንደ ኢህአዴግ አሰኳል ማየቱ የተጋነነ ሰለመሆኑ ሲከራከሩ እሰማለሁ፡፡ ይህ አመለካካት ግን ስህተት ይመስለኛል፡፡ አንደኛ ህወሓት የኢህአዴግ መሰራች ድርጅት ነው፡፡ ሁለተኛ ድርጅቱን አሁንም መስመር በማስያዝ በኩል የላቀ ሚና እንዳለው እሙን ነው፡፡

ሌላው ቢቀር ሀገር አደጋ ውስጥ ነው ብሎ ከአንድ ወር በላይ ቤተ ዘግቶ መክሮ ሁሉም የኢህአዴግ ዕህት ድርጅቶች እራሳቸውን በደንብ እንዲያ በማድረግ እነ አብይ አህመድን (ዶ/ር) ለስልጣን እንዲበቁ በማድረግ በኩል ቀጥተኛ ያልሆነ ሚናን ተጫውቷል፡፡
ከዚህ በላይም በኢህአዴግ ምክር ቤት ነጥብ ሲሰጥ ሁሉም ዕህት ድርጅቶች የላቀ አፈፃፀም አምጥተሃል ብለው ዕውቅና የቸሩት ድርጅት ሰለመሆኑ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ የህወሓት በኢህአዴግ ላይ የማመፅ ዳርዳርታ በርካታ ችግሮችን እንደሚሰከትል ለመገምት ነብይ መሆን አይጠይቅም፡፡

ህወሓት አሁን እያደረገ ያለው ስብሰባ በኢህአዴግ ቤት ያለን የአቋም ልዩነት እንዴት ይታረቃል? እንዲህ ሁነንስ እሰከመቼ እንዘልቃለን የሚሉ ሀሳቦች ሊነሱበት እንደሚችሉ እሙን ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ዘላቂ መፍትሄን መስጠት ባይቻል እንኳ የነሀሴውን የኢህአዴግ ጉባዔ መጠበቅ የውዴታ ግዴታ ነው፡፡

ለእኔ የነሀሴውን የኢህአዴግ ጉባኤ ከአለም ዋናጫም በላይ እንድጠብቀው የሚያሰገድደኝ እውነትም ይኼው ነው፡፡ ህዝብን በባሌም በቦሌም ብሎ ከጎኑ እያሰለፈ ያለው ኃይልና ርዕዮተ ዐለም የሚሉትን ጉዳይ ምርኩዙ ያደረገ እንጃ የፍፃሜ ጨዋታ ሰለሚያደርጉበት፡፡

ድሬቲዩብ

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram