የመከላከያ ሰራዊቱን ከፍተኛ አዛዦች ያካተተ አጣሪ ቡድን ወደ ሞያሌ ማቅናቱ ተገለፀ
የመከላከያ ሰራዊቱ ከፍተኛ አዛዦች የሚገኙበት አንድ አጣሪ ቡድን ሞያሌ ላይ በንጹሃን ዜጎች ላይ የደረሰውን ጉዳት ለማጣራት ወደ ስፈራው ማቅናቱ ተገለጸ።
ቡድኑ የተጎጂ ቤተሰቦችንና ህብረተሰቡን በማነጋገር እንደሚያጽና እና የማረጋጋት ስራውንም እንደሚሰራ የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬቴሪያት ተወካይ ሌተናል ጄኔራል ሃሰን ኢብራሒም ተናግረዋል።
በደረሰው ጉዳትም ኮማንድ ፖስቱ የተሰማውን ሀዘን እንደሚገልጽ ነው ሌተናል ጄኔራሉ የተናገሩት።
በአገሪቷ የተፈጠረውን ሁኔታ ለማባባስ ያለመ የኦነግ ኃይል በሶስት አቅጣጫ ወደ አገሪቷ ሰርጎ ለመግባት ያደረገውን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ወደ ሞያሌ የተጓዘው አንድ የሻለቃ ጦር የተሳሳተ መረጃ በመያዝ በተፈጠረ ግጭት የግዳጅ አፈጻጸም ደንቡን ባልተከተለ አኳኋን እርምጃ በመውሰዱ የሰው ህይወት ላይ ጉዳት መድረሱ ነው የተገለጸው።
በዚህ ተግባር ላይ በተሳተፉ የመከላከያ ሰራዊቱ አባላት ላይ ትጥቅ የማስፈታትና በቁጥጥር ስር የማዋል የመጀመሪያ እርምጃ መወሰዱን የተናገሩት ሌተናል ጀነራሉ፤ የማጣራቱና የምርመራ ስራ እንደተጠናቀቀም ወደ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ተወስደው እንደሚዳኙ ገልጸዋል።
ለወደፊቱም በየቦታው ያሉ አዛዦች የግዳጅ አፈጻጸም ደንቡን በአግባቡ እንዲያስፈጽሙ አሳስበዋል።
ህብረተሰቡም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ኮማንድ ፖስት መመሪያ ለማስፈጸም በሚንቀሳቀሱ የጸጥታ አካላት ጋር ሰላሙን ለማስጠበቅ መስራት እንዳለበት ጥሪ ማስተላለፋቸዋን ኢዜአ ኢቢሲን ጠቅሶ ዘግቧል።
ኮማንድ ፖስቱ እንዳስታወቀው በኦሮሚያ ክልል ሞያሌ አካባቢ አምስት የመከላከያ ሰራዊት አባላት የተሳሳተ መረጃ ይዘው ባደረጉት እንቅስቃሴ የዘጠኝ ሰዎች ህይወት ሲያልፍ፤ በ12 ሰዎች ላይ ደግሞ የመቁሰል አደጋ መድረሱ ይታወሳል።
ኤፍ.ቢ.ሲ