fbpx

የመቐለ ዩኒቨርስቲ የህክምና ዶክተሮችን ጨምሮ 362 የጤና ባለሙያዎችን አስመረቀ

የመቐለ ዩኒቨርስቲ የአይደር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በቅድመና ድህረ ምረቃ መርሀ ግብር በተለያዩ የህክምና ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 362 ባለሙያዎች አስመረቀ።

ኮሌጁ ካስመረቃቸው መካከል 157ቱ በመጀመሪያ ዲግሪ በህክምና ዶክተርነት የሰለጠኑ ሲሆኑ፥ ከነዚሁ ውስጥ 50ዎቹ ሴቶች ናቸው።

የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ክንደያ ገብረህይወት በምረቃው ላይ እንደተናገሩት፥ ኮሌጁ በመጀመሪያ ዲግሪ ካስመረቃቸው የህክምና ዶክተሮች በተጨማሪ በተለያዩ የህክምና አይነቶች 38 ስፔሻሊስት ሀኪሞችም ይገኙበታል።

ከነዚሁ ውስጥም ሁለቱ በሽንት ቱቦ፣ ፍኛና ኩላሊት ህክምና በሳብ ስፔሻሊቲ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመረቁ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ የጤና ዘርፎች 167 ባለሙያዎች በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሀኑ፥ ምሩቃን የሙያውን ስነ ምግባር በማክበር ሀገሪቱ በጤና ዘርፍ ላስቀመጠችው ዘላቂ ግብ ሰኬታማነት ጠንክረው እንዲሰሩ አሳስበዋል።

ሚኒስትሩ አያይዘው እንዳሉት የአገሪቱን የጤና አገልግሎት ለማሻሻል ከተያዙ የትራንስፎርሜሽን አጀንዳዎች አንዱ የመረጃ አብዮት ነው።

ይህንን በስራ ለመተርጎም በአገር አቀፍ ደረጃ በ240 ወረዳዎች፣ በ1 ሺህ 875 ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች ለኤሌክትሮኒክስ የህክምና መረጃ ምዝገባና ክትትል በሚያመች መንገድ የመረጃ መርብ እየተዘረገላቸው መሆኑንም አስረድተዋል።

በዘርፉ ተጨማሪ ስራዎችን ለማከናወንና የመረጃ ቋቶችን የማደራጀት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው የመረጃ አብዮት ዋነኛ አላማ የጤና ስርዓቱን ከማዘመን ባለፈ መረጃን መሰረት ያደረጉ የጤና መርሀ-ግብሮችን መንደፍ እንደሆነ ተናግረዋል።

ከተመራቂ ሀኪሞች መካከል ዶክተር ጎይተኦም ካህሳይ እንደገለጸው በሙያው ስነምግባር እና በገባው ቃል ኪዳን መሰረት ሁሉንም ወገኑን በእኩልነት ለማገልገል ተዘጋጅቷል።

ሌላዋ ወጣት ተመራቂ ዶክተር ሚሻ አባይነህ በበኩሏ “የህክምና ሙያ ዘር ሃይማኖት ቋንቋ እና ሌሎችም ነገሮች ሳይገድቡት ለሁሉም እኩል አገልግሎት መስጠትን የግድ የሚል ነው” ብላለች።

ለሙያዋ እና ለህብረተሰቡ ታማኝ በመሆንም በስራ ዘመኗ የሚጠበቅባትን አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ማድረጓንም ተናግራለች።

ምንጭ፦ ኢዜአ

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram