fbpx

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ታጥቦ ያልጠራ የኦዲት ግኝት

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በ2008 ዓ.ም መቀሌ ዩኒቨርሲቲን ኦዲት በማድረግ የተለያዩ ጉድለቶችን አግኝቷል። ይህን ተከትሎም ጉድለቶቹ እንዲስተካከሉ ለተቆጣጣሪው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳውቋል። በምክር ቤቱ የመንግስት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዩኒቨርሲቲው ጉድለቱን ለማስተካከል መርሀ ግብር በመዘርጋት የማስተካካያ እርምጃ እንዲወስድ አሳስቧል፡፡ በመርሀ ግብሩ መሰረትም ለዋና ኦዲተር እና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ማስተካካያውን ቆጥሮ እንዲያስረክብ ጠይቋል። ዩኒቨርሲቲውም የኦዲት ህጸፆቹን አርሞ ለዋና አዲተር ለማሳወቅ ቃል ገብቶ ነበር። ከሁለት ዓመት በኋላ ባለፈው 15 ቀን የቃላቸውን ፍሬ ለመሰብሰብና የተደረሰበትን ለማወቅ ባለጉዳዮቹ በምክር ቤት ተገናኝተዋል።

 

የመጀመሪያው መጀመሪያ

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሪት ወይንሸት ገለሶ፤ ዩኒቨርሲቲው ከዋና ኦዲተር ጋር ያደረገውን የመውጫ ስብሰባ፣ በኦዲት ግኝቱ እንዲስተካከል ለተገለፁ ጉዳዮች መርሀ ግብር መላካቸውን እና በመርሀ ግብሩ መሰረት እርምት ስለማድረጉ እንዲያሳውቅ በመጠቆም መድረኩን ለዩኒቨርሲቲው ሃላፊዎች አስረከቡ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሪዚዳንት ዶክተር አብዱልቃደር ከድር፤ የመውጫ ስብሰባ ማድረጋቸውን፣ መርሀ ግብር መዘርጋታቸውን፣ እርምት ያደረጉባቸውና ያላረሟቸው የኦዲት ግኝቶች መኖራቸውን አሳወቁ። ሰብሳቢዋ የምክትል ፕሬዚዳንቱን ቃል እውነትነት ዋና ኦዲተሩ እንዲያረጋግጡ ዕድል ሰጡ። ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ዱቢሶ፤ የመውጫ ስብሰባ መደረጉን፣ መርሀ ግብር ዘግይቶ መላኩን አረጋገጡ። ተወሰዱ የተባሉ እርምቶች ግን እንዳልተላኩላቸው በመጠቆም እርምቱን ማረጋገጥ እንደማይችሉ አረጋገጡ።

ህገ ወጥ ክፍያ

ቋሚ ኮሚቴው ዋና ኦዲተር በ2008 ዓ.ም ያደረገውን ኦዲት ዋቢ በማድረግ ለዩኒቨርሲቲው ሃላፊዎች ጥያቄ አቅርቧል። በ2008 ዓ.ም በተደረገው ኦዲት የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 515/1999ን ዓ.ም በመተላለፍ በቦርድ በማስወሰን 343ሺ 356 የተለያዩ ክፍያዎችን አከናውኗል። የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ሚኒስቴርን ሳያስፈቅድ ሁለት ሚሊዮን 912ሺ 900 ብር የትርፍ ሰዓት ክፍያ ፈፅሟል፡፡ መደበኛ ባልሆነው መርሀ ግብር ላስተባበሩ የአስተዳደር ሰራተኞች ከውስጥ ገቢ ከቦርዱ እውቅና ውጪ 999ሺ 756 ብር ወጪ ተደርጓል። ዩኒቨርሲቲው በቀረጸው የውሎ አበል ማወራረጃና ከህግ ውጪ የዓመት ዕረፍት በድምሩ 74ሺ 460 ብር ወጪ መሆኑ በኦዲት ተረጋግጧል። ዩኒቨርሲተው እነዚህን ህገ ወጥ ተግባሮች በኦዲት የማስተካከያ ሀሳብ መሰረት የእርምት እርምጃ መውሰዱን እንዲያብራራ ከቋሚ ኮሚቴው ጥያቄ ቀርቦለታል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የፋይናንስ ዳይሬክተር ወይዘሮ በላይነሽ አብርሃም፤ “ቦርድ በማስወሰን” ለመምህራን የተደረገው ክፍያ የውስጥ ገቢ ስለሆነ ህጉ ቦርዱን በማስፈቀድ መጠቀም ስለሚፈቅድ አካሄዱ ትክክል መሆኑን ይናገራሉ። “መደበኛ ባልሆነው መርሀ ግብር ላስተባበሩ ሰራተኞች” የተከፈለው ከጤና ቢሮ ውል በተገባው መሰረት በመሆኑ ዋና ኦዲተር እንዲስተካከል ያቀረበው አስተያየት ተገቢነት እንደሌለው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አበበ እጅጉ፤ ‹‹ዩኒቨርሲቲው የውስጥ ገቢውን ቦርዱን በማጸደቅ መጠቀም እንደሚችል በህግ ተፈቅዶለታል›› በማለት የማስተካከያ ጥያቄው ተገቢ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ ዓመቱን ሙሉ በስራ ላይ ለነበሩ ሰራተኞች የዓመት እረፍታቸው ወደ ገንዘብ ሲቀየር ለፐብሊክ ሰርቪስና ለሰው ሀብት ሚኒስቴር አለማሳወቅ ስህተት መሆኑን አምነው አፈፃጸሙ ግን ህጉን የተከተለ ነው ብለዋል፡፡ ከቦርዱ እውቅና ውጪ የተከናወነው ክፍያ ስህተት መሆኑን ተናግረው ቀድሞ ከተፈፀመው ውጭ ግን ስህተት አለመደገሙን ገልጸዋል።

ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ዱቢሶ እንደሚሉት፤ የዩኒቨርሲቲው ቦርድ ገንዘብና ፋይናንስን በሚመለከት እንዳይወስን የሚኒስትሮች ምክር ቤት በህግ ደንግጓል። ቦርዱ የሰራተኞችን ክፍያ ተመን ሊያወጣ እና ክፍያ ሊወስን አይችልም። የውስጥ ገቢን በሚመለከት በመመሪያው መሰረት ብቻ ነው ሊወስን የሚገባው። የዩኒቨርሲቲው ሃላፊዎች ቦርዱ ባልተሰጠው ሃላፊነት እንዲወስን ያደርጋሉ። ይህም ህገ ወጥ ነው። በኦዲት አስተያየት የተሰጠባቸው ማስተካከያዎች መታረምና ዳግመኛም እንዳይፈጸሙ ማድረግ ይገባል። ሃላፊዎቹ ያንጸባረቋቸው ሃሳቦች ትክክል ያልሆኑና መታረም የሚገባቸው ናቸው።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በዋና ኦዲተር የተነሱ ሃሳቦች ትክክል መሆናቸውን በማንሳት ህጸጾችን ማረም እንደሚገባ አስገንዝበዋል። አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ የሚመለከታቸውን አካላት በማስፈቀድ ክፍያውን መፈጸም እንደሚቻልም ነው የጠቆሙት። ከዚህ ያለፈ ችግር ሲያጋጥምም ወደ ምክር ቤት ይዞ በመምጣት ህጎችን የማሻሻልና አዲስ እስከ ማውጣት የሚደርስ እርምጃ ማስወሰድ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ እነዚህ የመፍትሔ አማራጮች እያሉ ህግን መተላለፍ ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል አስጠንቅቀዋል።

ህገ ወጥ ግዥና ወጪ

ዩኒቨርሲቲው ለሃላፊዎች የመንግስት ግዥ አፈፃፀም መመሪያን በመተላለፍ ያለጨረታ ሁለት ሚሊዮን 701ሺ 807 ብር፣ በተቆራረጠ ፕሮፎርማ ግዥ 764ሺ 224 ብር ፣ እንዲሁም በጨረታ መፈጸም የሚገባው የ636ሺ ብር ግዥያለ ውድድር መፈፀሙን ቋሚ ኮሚቴው አንስቷል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለሚገዛው እቃ ወይም አገልግሎት ወዲያውኑ ህጋዊ ደረሰኝ መስጠት ቢገባውም ጊዜያዊ ደረሰኝ መስጠቱ ተረጋግጧል፡፡ ያለ ደረሰኝና በተራ ፋክቱር የተወራረዱ፤ በአታችመንት ብቻ የተያዙ የሶስት ሚሊዮን 792ሺ 176 ብር ሂሳቦችም ተገኝተዋል። ስድስት ሚሊዮን 582ሺ 659 ብር ያለሂሳብ መደብ ተመዝግቦ የተገኘ ሲሆን በጀት ዓመቱን ያልጠበቀ አምስት ሚሊዮን 449ሺ 667 ብር ወጪ መካሄዱን በማንሳት የዩኒቨርሲቲው ሃላፊዎች ምላሽ እንዲሰጡበት ተደርጓል።

የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አበበ እጅጉ፤ዩኒቨርሲቲው በኮሌጆቹ ያልተማከለ የአስተዳደር ሥርዓት መዘርጋቱን በመጠቆም ግዥውም በዚህ ሥርዓት እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡ በተበጣጠሰ መልኩ ግዥ መከናወኑ የጨረታ ሂደትን እንዳይከተል ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ ግዥን በማዕከል በማድረግ ችግሩን ለመፍታት እየጣሩ እንደሆነ ቢጠቁሙም ከስፋቱ አንፃር በተበጣጠሰ መልኩ የመግዛቱ ሂደት ሊቀጥል እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል።

እንደ ዶክተር አበበ ገለፃ፤ በተራ ፋክቱር የተወራረዱት ሂሳቦች እቃዎቹ በቴክኒክ ኮሚቴው ትክክለኛነት እስከሚረጋገጥ ነው። ትክክለኛነቱ እንደተረጋገጠ ህጋዊ ደረሰኝ ተሰጥቷል። ይህን የአሰራር ሥርዓት ለመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ ኤጀንሲ በማሳወቅ ህጋዊ አሰራር እንዲሆን ተደርጓል። በኦዲት ወቅት ደረሰኛቸው ያልተያያዘ ደረሰኝ ተፈልጎ የተያያዘ ሲሆን አንዳንድ ደረሰኝ የማይቀርብላቸው ግዥዎች እንዳሉ ግንዛቤ መያዝ ይገባል፡፡

ያለሂሳብ መደባቸው የተመዘገቡ ስተካከላቸ ውን፣ በተለያየ ምክንያት በጀት ዓመቱን ያልጠበቀ ወጪ መፈፀሙንና ይህንን ለማስተካከልም አስቸጋሪ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ኃላፊዎች ጠቁመዋል። የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አበዱልቃድር ከድር፤ ‹‹የዩኒቨርሲቲው ያልተማከለ የአስተዳደር ሥርዓት ዓላማውን ለማስፈጸም የሚያስችል ቢሆንም አሰራሩ የኦዲት ግኝት እየሆነ በመምጣቱ የዩኒቨርሲቲውን ዓላማ ለማሳካት እንቅፋት ሆኖብናል›› በማለት የአንድ ማዕከል ግዥ ሥርዓትን ተችተዋል። ወይዘሮ በላይነሽ፤ ‹‹ዩኒቨርሲቲው አስቸኳይ ሁኔታ ሲያጋጥመው ማኔጅመንቱን በማስፈቀድ ግዥ ፈፅሟል›› በማለት ‹‹የግዥ መመሪያ ተጥሶ ግዥ ተፈጽሟል›› ለተባለው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ለተፈጸመው ግዥ ተራ ደረሰኝ መስጠት ህጉ እንደማይፈቅድ ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ተናግረዋል፡፡ ይህም መስተካከል እንዳለበት ነው ያስገነዘቡት። ዩኒቨርሲቲው ለኤጀንሲው አሳውቆ ጊዜያዊ ደረሰኝ እንዲጠቀም ከተፈቀደለት ወደ አሰራር ማስገባት እንደሚቻልም አስረድተዋል፡፡ ይህም ለኪራይ ሰብሳቢነት በር እንዳይከፍት ጥንቃቄ በማድረግ የቴክኒክ ኮሚቴው ጥራቱን አረጋግጦ ቶሎ ህጋዊ ደረሰኝ መስጠት እንደሚገባው ገልጸዋል።

‹‹ግዥ በተበጣጠሰ መልኩ የሚከናወነው በእቅድ ስለማትመሩ ነው። ግዥዎች በተቀናጀ፣ በህጉና በአንድ ማዕከል መሆን አለባቸው። ደረሰኝ የሌላቸውን እቃዎች ወይም አገልግሎቶችን አስፈቅዶ መግዛት ይቻላል። በዚህ ዓይነት የተገዙትም ስለመፈቀዳቸው በኦዲት ወቅት ማስረጃ ማቅረብ ይገባል። ስለሆነም በህጉ መሰረት መስራት ተገቢ ነው። ከህግ ውጭ በመንቀሳቀስ ዋና ኦዲተር ለስራ እንቅፋት እንደሆነ መግለፅ ተቀባይነት የለውም። የዋና ኦዲተር ዓላማ ህግን መሰረት አድርጋችሁ እንድትስሩ መደገፍና ችግርም ሲፈጠር እንድታስተካክሉ ማድረግ ነው። በመሆኑም በኦዲት ግኝቶች እንዲታረሙ የተሰጡ አስተያየቶች መታረምና መስተካከል አለባቸው›› ሲሉ አቶ ገመቹ አስጠንቅቀዋል።

ገቢና ተሰብሳቢ

ቋሚ ኮሚቴው በዩኒቨርሲቲው የገቢ አሰባሰብ ላይ ያለውንም ችግር አቅርቧል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የመንግስት ገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286/1994 ዓ.ም በመተላለፍ የቅድመ ገቢ ግብርና እሴት ታክስ ሳይቀነስ 34ሺ807 ብር ተከፍሎ ተገኝቷል። አቅራቢዎች በውሉ መሰረት ባለመፈጸማቸው ለዩኒቨርሲቲው ገቢ መደረግ የነበረበት ሶስት ሚሊዮን 291ሺ 307 ብር የጉዳት ካሳ ገቢ አልተደረገም። ለዩኒቨርሲቲው የቀረበው አጀንዳ ጥራቱን ያልጠበቀ መሆኑ በግዥ ቴክኒክ ኮሚቴ ቢረጋገጥም ዩኒቨርሲቲው አንድ ሚሊዮን 71ሺ 984 ብር ክፍያ ፈጽሟል። በዩኒቨርሲቲው መሰብሰብ የሚገባው 13 ሚሊዮን 111ሺ 912 ብር ሳይሰብሰብ ወደ ቀጣዩ በጀት ዓመት ተዛውሯል። በ2007 ዓ.ም መከፈል የነበረበት 88ሺ 59 ብር ወደ 2008 ዓ.ም መዛወሩ በኦዲቱ ግኝቱ ተመልክቷል፡፡ ለእነዚህ ችግሮች በተወሰዱ ማረሚያዎች እና ተጠያቂ በተደረጉ አካላት ዙሪያ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ማብራሪያ እንዲሰጡ ተጠይቋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አበበ፤ የጉዳት ካሳን በተመለከተ የቀረበው ችግር ዩኒቨርሲቲው ባለመረከቡ የተፈጠረ ክፍተት በመሆኑ የጉዳት ካሳ እንደማያስከፍል ገልጸዋል፡፡ አጀንዳውም ዩኒቨርሲቲው ይገዛልኝ ብሎ ባስቀመጠው ደረጃ መሰረት የቀረበ በመሆኑ ክፍያው መፈፀሙን አስረድተዋል፡፡ በኦዲት ግኝቱ የተገለፁት አብዛኛዎቹ ንብረቶችና ገንዘብ ተሰብስበው ገቢ መደረጋቸውን ምክትል ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል፡፡ ገቢ ያላደረጉ ሁለት ተቋማት ጉዳይም በህግ መያዙን፤ የዩኒቨርሲቲውን ንብረትና ገንዘብ ወስደው ገቢ ሳያደርጉ ህይወታቸው ያለፈና ከአገር በወጡ ግለሰቦች ላይ መወሰድ ስለሚገባው እርምጃ ምክረ ሃሳብ መጠየቃቸውን፤ ገቢ ያልተደረጉ ንብረቶችና ገንዘብን ለማስመለስ እየጣሩ መሆኑን አብራርተዋል።

የፋይናንስ ዳይሬከተሯ ወይዘሮ በላይነሽ፤ በበኩላቸው የቅድመ ገቢ ግብርና እሴት ታክስ ሳይቀነስ መከፈሉ ትክክል አለመሆኑን በማመን ችግሩን መውሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በ2007 ዓ.ም መክፈል እየተገባው ወደ 2008 በጀት ዓመት ያሸጋገራቸውን ክፍያዎች አብዛኞቹን መክፈሉንና የቀሩትንም ወደ መንግስት ገቢ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ‹‹በዩኒቨርሲቲው የቀረበው የተሰብሳቢ ሂሳብ መቀነስ አስተያየት ውሸት ነው፡፡ በ2009 ዓ.ም በተደረገው ኦዲት ዩኒቨርሲቲው መሰብሰብ የሚገባው ገንዘብና ንብረት መጨመሩ ታይቷል፡፡ በውሉ መሰረት ዩኒቨርሲቲው መረከብ ካልቻለ ሃላፊዎቹ መጠየቅ አለባችሁ። ንብረትና ገንዘብ ሳይመልሱ ከአገር የወጡና ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች እንዴት መመለስ እንዳለበት የተዘረጋ የአሰራር ሥርዓት ስላለ ምክረ ሃሳብ ሳያስፈልግ ማስመለስ ይገባል›› ብለዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው “የቅድመ ገቢ ግብርና እሴት ታክስ ሳይቀነስ መከፈሉን በስህተትነት መውሰድ ሳይሆን የተደረገውን ማስተካካያ ነው ማቅረብ የሚገባው። እርምጃ መውሰድ የሚገባ ከሆነ እርምጃ ወስዶ ማስተካከል ይገባል›› የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል፡፡

ንብረትና ተሻጋሪው ኦዲት

በመጨረሻም ቋሚ ኮሚቴው የዩኒቨርሲቲው መኖሪያ ቤቶችና፣ ህንፃዎች ተመዝግበው አለመያዛቸው፤ ቋሚና አላቂ እቃዎች በአንድ መጋዝን መቀመጣቸው፤ የአንዳንድ እቃዎች የቢን ካርድ የመጠቀሚያ ጊዜ ማብቂያ አለመገለጹ፣ በአጠቃላይ በዩኒቨርሲቲው የንብረት አያያዝ፣ ክምችትና ስርጭት በህጉ መሰረት እየተሰራ አለመሆኑ በኦዲት ግኝቱ ተረጋግጧል።

ከዚህም በተጨማሪ በ2007 ዓ.ም ኦዲት ለአንድ የውጭ አገር መምህር ለትርፍ ስዓት ክፍያ 396ሺ 662 ብር ፣ ለቤትና ለውሎ አበል 695ሺ 995 ብር በብልጫ መከፈሉ በኦዲት ተረጋግጧል። የዩኒቨርሲቲው ግንባታ በወቅቱ ተግባራዊ ባለመሆኑ ለደረሰበት የጉዳት ካሳ 20 ሚሊዮን 997ሺ439 ብር መከፈል እንዳለበት በኦዲት ግኝቱ እንዲያርም አስተያየት ቢሰጥም እስከ 2008 በጀት ዓመት ማብቂያ ድረስ እርምጃ አለመወሰዱን በመጠቆም ማብራሪያ ጠይቋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አበበ፤ የንብረት አያያዙ መሻሻሉን በግርድፉ ገልጸዋል። በብልጫ የተከፈለውን የውሎ አበል ማስመለሳቸውንና ቀሪውን ለማስመለስ ጥረት እያደረጉ መሆን አብራርተዋል። ለውጭ አገር መምህር በብልጫ የተከፈለው ብቸኛ የፎረንሲክ መምህር በመሆናቸውና አቋርጠው ቢሄዱ ትምህርት ክፍሉ እንደሚዘጋ በማውሳት የሚመለከተውን አካል አለማስፈቀዳቸው ስህተት መሆኑን ተናግረዋል። የጉዳት ካሰው ክፍያውን ካልተከፈለው ገንዘብ ላይ ለመቀነስ ከሥራ ተቋራጮቹ ጋር መግባባታቸውን አብራርተዋል።

ማጠቃለያ

ዋና ኦዲተር የንብረት አያያዝን በሚመለከት በቀጣይ በሚያደርገው ኦዲት እንደሚያረጋግጥ አቶ ገመቹ ተናግረዋል፡፡ በኦዲት አስተያየት የተሰጠባቸውን ጉዳዮች ማስተካከል እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ የማያሰሩና እንቅፋት የሆኑ ነገሮች ካሉ ከሚመለከተው ጋር በመነጋገር መፍታት እንደሚያስፈልግ በመጠቆም። ህግን መሰረት አድርጎ መስራት እንደሚገባ ዋና ኦዲተሩ ጠቁመው ከዚህ ውጭ ከሆነ የኦዲት ግኝት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በዚህ ላይም ማስተካከያ የማድረግና ተጠያቂነት ሊከተል እንደሚችል ገልጸዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሪት ወይንሸት ገለሶ፤ በኦዲት አስተያየት መነሻነት ዩኒቨርሲቲው እንዳስተካከላቸው የተገለፁት ጉዳዮች መልካም መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ምክር ቤቱ ለተስተካከሉት ጉዳዮች ዕውቅና የሚሰጠው ማስተካከያውን ዋና ኦዲተር ሲያረጋግጥለት እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡

በኦዲት አስተያየቱ እንዲታረሙ የቀረቡት ሁሉም ጉዳዮች መታረም እንዳለባቸው ተጠቁሟል፡፡ በተለይም ከግዥ፣ ከክፍያ፣ ከገቢና ከንብረት ጋር ተያይዞ በተነሱ ችግሮች በትኩረት መስራት ይገባል፡፡ የዩኒቨርሲቲውን የውስጥ ኦዲት በማጠናከር በየጊዜው እያረሙ መሄድ ተገቢ ነው። ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ችግሩን በጋራ ለመስራት መንቀሳቀስ ቀጣይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ አካሄድ ነው፡፡ ህግን መሰረት አድርጎ መስራት ተገቢ ሲሆን፤ ህግን መተላለፍ ተጠያቂነትን ያስከትላል፡፡

 

አጎናፍር ገዛኽኝ – አዲስ ዘመን

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram