fbpx

የሆድ ድርቀትን በቀላሉ ለማከም

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የሆድ ህምም በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል። የሆድ ህመም ሁሉም ሰው በህይወቱ ከአንድ ጊዜ በላይ ሊያጋጥመው እንደሚችልም ይጠበቃል። ችግሩ በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰት ቢሆንም ዋናው ነገር ከጀርባው ያለውን ምክንያት አውቆ እራስን መጠበቁ ላይ ነው። ከዛም ባለፈ ህመሙ ሌላ የተደበቀ በሽታን እንደሚያመ ላክትም አውቆ በፍጥነት ወደ ሆስፒታል መሄድ ተገቢ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ለምሳሌ የምግብ አለመፈጨት፣ የሆድ ድርቀት፣ የምግብ ብክለት፣ የጨጓራ ቁስለት፣ የሃሞትና የኩላሊት ጠጠር፣ የትርፍ አንጀት በሽታ፣ የተለያዩ ሆድ ውስጥ በሚኖሩ ረቂቅ ተህዋሲያንና አማካኝነት ህመሙ ሊከሰት ይችላል።

የሆድ ህመም አንድ ቦታን ለይቶ አሊያም እንዳለ ሆድን አጠቃሎ ሊያም ይችላል። ከግማሽ በላይ የሆነውን ክፍል የሚያመው አይነት የሆድ ህመም በቀላል የህክምና ክትትል ሊድን የሚችል ሲሆን አንድ ቦታን ብቻ ለይቶ የሚያም ከሆነ ደግሞ ከበድ ያለ ችግር እንዳለ የሚያመላክት ነው። ይህ ምልክትም ለምሳሌ እንደትርፍ አንጀትና የጨጓራ ቁስለት የመሳሰሉ በሽታዎች መኖራቸውን ጠቋሚ ተደርጎም ይወሰዳል። ስለዚህም ከላይ ከተጠቀሱት የሆድ ህመሞች መካከል ለዛሬ ትኩረት በማድረግ የምናየው የሆድ ድርቀትን ይሆናል። የሆድ ድርቀት ህመም መንስኤውና ህክምናውን አስመልክቶ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ይሰጡን ዘንድ በየካቲት 12 ሆስፒታል ሕክምና ኮሌጅ የውስጥ ደዌ እስፔሻሊስት ዶክተር ይታገሱ ጌታቸውን አነጋግረናል።

አዲስ ዘመን፡- ስለ ሆድ ድርቀት አጠቃላይ ምንነት ቢገልፁልን?

ዶክተር ይታገሱ ፡- የሆድ ድርቀት የሰውን ልጅ ምቾት የሚነጥቅ ችግር ሲሆን፤ በእራሱ ግን ህመም አይደለም። የበሽታዎች ስሜት መገለጫ እንጂ። ለምሳሌ ሌሎች በሽታዎች በሆድ ውስጥ የተከሰቱ ከሆነ ሆድ ድርቀት ይኖራል። በሌላ መልኩ ሆድ ድርቀት በእራሱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሰ በሽታዎች የሚፈጠሩበትን እድል ያመቻቻል። ከስሜቱ በመነሳት ግን ሌሎች በሽታዎች መኖራቸውን ማወቅ ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡- ለሆድ ድርቀት ህመም መንስኤዎቹ ምን ምን ሊሆኑ ይችላሉ?

ዶክተር ይታገሱ፡- የሆድ ድርቀት በአንጀት እንቅስቃሴ የሚመጣ ችግር ሲሆን የአንጀት እንቅስቃሴ ከሰው ሰው ይለያያል። ለምሳሌም አንዳንዶች በቀን እስከ ሶስት ጊዜ የአንጀት እንቅስቃሴ ሲኖራቸው ሌሎች ደግሞ በሳምንት ሁለት ወይም አንድ ጊዜ ብቻ ይኖራቸዋል። በዚህም ሳቢያ ሰውየው በህመሙ ተጠቂ ሊሆን ይችላል። ሌላው አንድ ሰው ቢያንስ ለሶስት ወር እጅግ የደረቀ ሰገራ፣ የሰገራ አለመጨረስና ማቋረጥ፣ የፊንጢጣ መሰንጠቅና መሰል ክስተቶች የሚታይበት ከሆነና በተከታታይ የአልኮል፣ የሻይ፣ የወተት ተዋጾዎችን የሚወስድ ከሆነ ሰውዬው በህመሙ የመያዝ እድሉ የሰፋ ነው። በተጨማሪም በእድሜ መግፋት፣ በቂ ፈሳሽ ያለመውሰድ፣ በፋይበር የበለፀጉ ምግቦችን ያለመጠቀም፣ ምንም አይነት የአካል እንቅስቃሴ ያለማድረግ ለድርቀት ሊያጋልጡ የሚችሉ መድሃኒቶችን መጠቀምና የመሳሰሉትም እንዲሁ የሆድ ድርቀትን ያመጣሉ።

ሌላው ደግሞ በትልቁ አንጀት ወይም በደንዳኔ ውስጥ መዘጋት በሚፈጠርበት ጊዜ የአንጀት መታጠፍ፣ የትልቁ አንጀት ካንሰር፣ የትልቁ አንጀት ጥበት፣ አንጀት ላይ ጭነት ሊፈጥሩ የሚችሉ ሌሎች የሆድ ውስጥ ካንሰሮች፣ በደንዳኔ ግድግዳ ላይ አድገው የሰገራን መተላለፊያ ሊዘጉ የሚችሉ ነገሮች (ሬክቶ ሲል)፣ በትልቁ አንጀትና በደንዳኔ አካባቢ ባሉ ነርቮች ላይ ችግር በሚከሰትበት ወቅት፣ በሰውነት ውስጥ ባሉ ሆርሞኖች ላይ ችግር መከሰትና መሰል ተግባሮች በሚታዩበት ጊዜ ለሆድ ድርቀት ሊያጋልጡ ይችላሉ።

አዲስ ዘመን፡- ህመሙ ሲከሰት ምን ዓይነት ምልክቶችን ያሳያል?

ዶክተር ይታገሱ፡- ጥያቄውን በሁለት መልኩ መመልከት ይቻላል። ለረጅም ጊዜ የሚታይና ጊዜያዊ የሆነ የሆድ ድርቀት በማለት። አንድ ሰው ለተከታታይ ሳምንታትና ከዚያ በላይ በቂ ጊዜ ሰገራ መውጣት የሚያስቸግረው ከሆነ ወይም በሳምንት ከሶስት ጊዜ በታች ሰገራ የሚወጣ ከሆነ ለረጅም ጊዜ የቆየ የሆድ ድርቀት አለው ተብሎ ይገለፃል። ጊዜያዊ የሆነው ደግሞ ብዙ ጊዜ በሰዎች ላይ የሚከሰትና ህመሙም ብዙ ሳይቆይ የሚድን ነው። ለረጅም ጊዜ የሚቆየው የሆድ ድርቀት ግን የታማሚውን የዕለት ተዕለት ሥራ ከማወኩም በላይ በህመሙ እንዲሰቃይ ያደርገዋል።

አዲስ ዘመን፡- የሆድ ድርቀት ሕመም ደረጃ ይኖረው ይሆን?

ዶክተር ይታገሱ፡- አለው ይኸውም ህመሙ ለአጭርና ለረጅም ጊዜ የሚቆይ በማለት ሊታይ ይችላል። አንድ ሰው ለተከታታይ ሳምንታትና ከዚያ በላይ በቂ ጊዜ ሰገራ መውጣት የሚያስቸግረው ከሆነ ወይም በሳምንት ከሶስት ጊዜ በታች ሰገራ የሚወጣ ከሆነ ለረጅም ጊዜ የቆየ የሆድ ድርቀት እንዳለበት በህክምናው ይገለፃል። ጊዜያዊ ወይም ለአጭር ጊዜ የሚከሰተው ህመም ደግሞ ብዙ ጊዜ በበርካቶች ላይ የሚከሰት ሲሆን ህመሙም ብዙ አይደለም።

አዲስ ዘመን፡- ህመሙን ቀድሞ መከላከል ይቻላል?

ዶክተር ይታገሱ፡- አዎ። በፋይበር የበለፀጉ ምግቦችን የመመገብ ሁኔታን በመጨመርና በቂ ፈሳሽ በመውሰድ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የጥራጥሬ ዘሮች በብዛት በመመገብ፣ የአካል እንቅስቃሴ በማዘውተር፣ የሰገራ ሰዓትን ሳያሳልፉ በአግባቡ በመጸዳዳት፣ የሰገራ ማለስለሻ ፋይበሮችንና መድሃኒቶችን በመጠቀም፣ የዳሌና ጡንቻዎች ስልጠና በመውሰድና ከአንድ ሊትር ተኩል እስከ ሁለት ሊትር ተኩል ውሃ እና ሌሎች ፈሳሾችን በቀን በመጠጣት ህመሙን መከላከል ይቻላል። (ካፌን) የያዙ ፈሳሾችን ለምሳሌ፦ ቡና፣ ሻይና አልኮል ነክ መጠጦች እንዲሁም የወተት ተዋዕጾዎችን ባለመጠቀምም እንዲሁ። ምክንያቱም እነዚህ መጠጦች የሰውነት ፈሳሽን የማድረቅ ባህሪ ስላላቸው አጠቃቀማቸውን መቀነስ አስፈላጊ ነው።

አዲስ ዘመን፡- የሆድ ድርቀት ህመሙ ከተከሰተስ በኋላ ምን ዓይነት ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል?

ዶክተር ይታገሱ፡- ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራት መተግበር በቂ ነው። ምክንያቱም ህመሙ የሚከሰተው ከአንጀት ችግር የተነሳ፣ ከአመጋገብ ልምድና የመድሃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳቶች በሚገባ ያለመረዳት በመሆኑ መከላከያዎቹን ማወቅ ከህመሙ ለመዳንም እገዛ ያደርጋል።

አዲስ ዘመን፡- ለሆድ ድርቀት ጊዜያዊ ማስታገሻ አለው? በተከታታይስ በሚጠቀሙበት ጊዜ ጉዳት ይኖረው ይሆን?

ዶክተር ይታገሱ፡- አለው። ለአብነትም የሰገራ ማለስለሻ (እስቱል ሶፍትነር)፣ ላክሳቲቭና ሌሎች በቤት ውስጥ በቀላሉ የሚገኙ ነገሮች ለምሳሌ፡-ጥራጥሬንና በቂ ፈሳሽ በመውሰድ ህመሙን ማስታገስ ይቻላል። ተግባሩን በሚያከናውኑበት ጊዜ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። ምክንያቱም ለምሳሌ ላክሳቲቭ የሚባለውን መድሐኒት ያለ ሐኪም ትዕዛዝ ከሁለት ሳምንት በላይ ቢጠቀሙ ህመሙን እንዲባባስ ያደርገዋል። በመሆኑም አጠቃቀሙን በሚገባ ተረድቶ መተግበር ተገቢ ነው። ይህ ካልሆነ ግን ከህመሙ አልፎ ሌሎች በሽታዎችን ሊያስከትል ይችላል።

አዲስ ዘመን፡- ሕመሙን በቋሚነት ማዳን ይቻላል?

ዶክተር ይታገሱ፡- ሕመሙ ስሜት እንጂ በሽታ ስላልሆነ መዳን ይችላል። ሆኖም ግን ለህመሙ አፋጣኝ ምላሽ ሳይወሰድ የቆየ የሆድ ድርቀትና ሌሎች በሽታዎች የተከሰቱ ከሆነ ለማዳን አስቸጋሪ የሚሆንበት አጋጣሚ ይፈጠራል። ስለዚህ ከሐኪም ጋር በመመካከር ህመሙ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሳይደርስ በአጭር ጊዜ መፍትሄ መሻት ያስፈልጋል።

አዲስ ዘመን፡- የሆድ ድርቀት አጠቃላይ ህክምናው ምን ይመስላል?

ዶክተር ይታገሱ፡- የደም ምርመራን በማድረግ፣ የሆርሞኖች አለመመጣጠን ለማወቅ የ«ባርየም»፣ የአንጀት መዘጋት የሚገጥም ከሆነ ደግሞ የ«ኮሎ ኖስኮፒ» ጥናት በማድረግ ህመሙን ማወቅ ይቻላል። በሌላ መልኩ ደግሞ በቀዶ ጥገና ህክምና ሊስተካከሉ የሚችሉ የጤና ችግሮችን ለምሳሌ፡- የፊንጢጣ መቀደድ፣ ሬክቶሴሌና የአንጀት ጥበት የመሳሰሉትን ሁኔታዎች የቀዶ ጥገና ባለሙያን በማማከር ህክምናው ሊሰጥ ይቻላል። በተጨማሪ ከሁለት እስከ አራት ብርጭቆ ውሃ በመጠጣት፣ ቁርስ ላይ ፍራፍሬና አትክልቶችን በመጠቀም፣ ሐኪሙ ባዘዘው ልክ የዓይነ ምድር ማለስለሻዎች መጠቀምና መሰል ተግባራትን በመጠቀም ሕክምናው ይከናወናል።

አዲስ ዘመን፡- ከሆድ ድርቀት ጋር ተያይዘው የሚመጡ በሽታዎች ይኖሩ ይሆን? ካሉስ ምን ምን ናቸው?

ዶክተር ይታገሱ፡- አሉ። ከብዙዎቹ ጥቂቶቹን ለማንሳት ሆርሞኖች በሰውነት ውስጥ ያለውን ፈሳሽ ተመጣጥኖ እንዲገኝ የማያደርጉ ሲሆን የስኳር ህመም፣ የፓራታይሮይድ ዕጢ ችግር፣ እርግዝና፣ የታይሮይድ ዕጢ ሆርሞኖች ማነስንና መሰል በሽታዎችን ሊያመጣ ይችላል። በድንገት የሚነሳ ሃይለኛ ህመም ደግሞ አንጀት መቀደድን፣ ኩላሊት ጠጠርን፣ የሃሞት ከረጢት በሽታዎችን፣ የሴት እንቁላል ማምረቻ ወይም የወንድ የዘር ፍሬ ማማረቻ መቋጠርን አሊያም የትልልቅ የደም ቧንቧ ችግርን ይፈጥራል። ሌላው አንዳንዴም ከከፍተኛ እንቅስቃሴ በኋላ የሚኖር የጡንቻዎች መኮማተር (ስትራፖ) ህመሙ እንዲከሰት ያደርጋል። እንደነዚህ ዓይነቱ ህመሞች አስቸኳይ ህክምና ስለሚያስፈልጋቸው በፍጥነት ወደ ሆስፒታል መሄድ ያስፈልጋ።

አዲስ ዘመን፡- ህመሙ የእድሜ እርከንን ይለይ ይሆን? ከለየስ በብዛት የትኛውን የእድሜ ክልል ያጠቃል?

ዶክተር ይታገሱ፡- ማንኛውም ሰው በሆድ ድርቀት በህይወቱ ቢያንስ አንዴና ከዚያ በላይ ተጠቂ ሊሆን ይችላል። በተለይም ሕፃናትና ከስልሳ አምስት ዓመት በላይ ያሉ አዛውንቶች። ምክንያቱ ደግሞ ሕጻናት የተለያዩ ደረጃዎችን ያልፋሉ በዚህ ምክንያት ህመሙ ሊከሰት ይችላል። ከእነዚህ መካከልም ህፃኑ ከእናት ጡት ወደ ደረቅ ምግብ በሚሸጋገርበት ጊዜ፣ ህፃኑ ሽንት ቤት መጠቀም በሚማርበት ጊዜና ህፃኑ ትምህርት ሊጀምር ሲቃረብ ያሉት ጊዜያት አካባቢ ነው። አዛውንቶች ደግሞ ህመሙ የሚከሰትባቸው እንቅስቃሴ ባለማድረጋቸው የተነሳ ነው።

አዲስ ዘመን፡- የሆድ ድርቀት ህመም ዓለም አቀፋዊና አገራዊ ገፅታው እንዴት ይገለፃል?

ዶክተር ይታገሱ፡- አገር አቀፍ ይዘቱን በተመለከተ ብዙም መረጃዎች የሉም። ነገር ግን ዓለም አቀፍ ይዘቱ ሲታይ ከ12 እስከ 15 በመቶ በህመሙ የመጠቃት ሁኔታ ያጋጥመዋል።

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram