fbpx

የህወሓት ውሳኔ የት ያደርሳል?

የህወሓት ውሳኔ የት ያደርሳል? 

ከሩሲያው የዓለም ዋንጫ በላይ በሀገር ውስጥ ተመለካቹ የሚጠበቀውን ጨዋታ መቐሌ በነሀሴ ወር ታስተናግዳለች፡፡ 27 ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰማይ ስር የደመቁት ህወሓቶች በፍፃሜው ጨዋታ በመሪነቱ አናት ላይ ከሚገኘው ኦህአዴድ ጋር የሚደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡ ከብአዴንና ደኢህዴን በፉክክሩ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ የሚያጠናቅቀውስ ማን ነው የሚለውም ጥያቄ ገና መልስ አላገኘም፡፡

የኢህአዴግ የነሃሴ ጉባዔ በጉጉት የሚጠበቀው ከላይ ያነሳሁትን የብሄር ድርጅቶችን ስለሚያፋልም ብቻ አይደለም፡፡ ይለቁኑም የተፎካካሪዎቸቹ የርዕዮተ አለም ልዩነት ከመቼውም ጊዜ በላይ በሰፋበት ወቅት በመካሄዱም ነው፡፡ ህወሓት በትናንቱ መግለጫ በውሉ እንዳስቀመጠው አብዮታዊ ዲሞክራሲዊ መስመሩን በዚህ ወቅት መታደግ የሀገሪቱን ህልውና ከመታደግ አይተናነስም፡፡
ኦህዴድ መራሹ ኢህአዴግ ግን ለአብዮታዊው ልማታዊው መስመሩ ግድ የሚሰጥ አይመስልም፡፡ በዚህ የተነሳም ከህወሓት ጋር ወደ ለየለት የርዕዮተ ዓለም ቁርሾ እየተንደረደረ ነው፡፡

በገዥው ፓርቲ ቤት ከፍተኛው የስልጣን ባለቤት የኢህአዴግ ጉባዔ ነው፡፡ በተዋረድ ከተመለከትነው ስራ አስፈፃሚው ከኢህአዴግ ምክር ቤት በመቀጠል ሦስተኛው የስልጣን አካል ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ የድርጅቱ ሊቀመንበርነትም ከዚህ በመቀጠል የሚሰጥ ስልጣን መሆኑን ኢህአዴግ በመተዳደሪ ድንቡ ላይ በግልፅ አስፍሯል፡፡

እንዲህ ከሆነ የህወሓት የትናንት ስሞታ ለየበላይ አካል የቀረበ መሆኑን እንረዳለን፡፡ መሰረታዊው ሀሳብ ግን ህውሓት ለምን ስሞታ አቀረበ የሚለው አይደለም ፡፡ዋናው ጉዳይ የህወሓት አቤቱታ ምን ያህል ተገቢ ነው የሚለው ይመስላል፡፡ የህወሓት ሰዎች ኢህአዴግን የገነቡ ማህንዲሶች በመሆናቸው የፓርቲውን የአደጋ ጊዜ መውጫ በር በድንብ አድረገው ያውቁታል፡፡

በዚህ የተነሳም ትናንት ያቀረቡት ስሞታ ተራ መነታረኪያ ሳይሆን በኢህአዴግ መተዳደሪያ ደንብ ላይ የሰፈሩ ህጎች ለምን ተሻሩ በሚል የተቃኘ ነው፡፡ 43 ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰማይ ስር የበረሩት አዛውንቶቹ የህወሓት አማራሮች የትኛው የድርጅቱ ህጎችን አሁን ያለው አመራራ እየጣሰ እንደሆነ ባይነግሩንም ለመገመት ግን አስቸጋሪ አይደለም፡፡

የመጀመሪያው የኢህአዴግ አዲሱ አመራር ከሰሞኑን ውሳኔዎቹ ጋር በተያያዘ ጥሶታል ተብሎ የሚገመተው ህግ አንቀፅ 19 ይመስላል፡፡ ኢህአዴግ በመተዳደሪ ደንቡ አንቀፅ 19 ቁጥር 2 ላይ እንዳሰፈረው ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ትላልቅ ውሳኔዎችን ጉባዔው እስኪደርስ ድረስ የመወሰን ሀላፊነት ያለው የኢህአዴግ ምክር ቤት ብቻ ነው፡፡ ከዚህ አንቀፅ አንፃር የሰሞኑን የከፊል ፕርይቬታይዜሽንና የአልጀርስ ስምምነት ውሳኔዎችን የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ብቻውን ማስተላለፉ ተገቢ አለመሆኑን አንረዳለን፡፡

በርግጥ እኔ ባለኝ መረጃ የኢህአዴግ ምክር ቤት ሁለቱን ጉዳዮች በተመለከተ ጥናቶች ተካሂደው የመጨረሻ ውሳኔ እንዲተላለፍ ውሳኔ አስተላፎ ነበር፡፡ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚም የሰሞኑን ውሳኔ ያስታለፈው ብዙዎች እንደሚሉት የግማሽ ቀን ስብሰባ በማድረግ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁኑ ምክር ቤቱ የሰጠውን አቅጣጫ መሰረት በማድረግ ጥናት አስጠንቶ ነው፡፡

በእኔ ግምት የኢህአዴግ ስራ አሰፈፃሚ ምክር ቤቱን ሳይጠብቅ ታሪካዊ የሚባለውን ሀገራዊ ውሳኔ ያስተላለፈው ጥናት ይደረግና ይወሰን የሚለውን መረጃ ብቻ በመያዙ ይመስላል፡፡ ይህ ውሳኔ በቁሙ ሲታይ ትክክል የሚሆነውም ለዚህ ነው፡፡ ነገር ግን ከመተዳሪያ ደንቡ አንጻር ያለ ምክር ቤቱ ስብሰባ ውሳኔው መተላለፍ አልነበረበትም፡፡

ህወሓቶች ስራ አስፈጻሚዎቻቸው ሳይቀር የተሳተፉበትን ውሳኔ መልሰው እንደ ዕቃቃ ጨዋታ የሚያፈርሱበትን ወኔ የታጠቁትም ከዚህ በመነሳት ነው ፡፡ አሁን የጠቅላይ ሚንሰትር አብይ አህመድ አመራር ከገባበት የኢኮኖሚ ቀውስ ሊያመልጥበት አስቦት የነበረው የአዳጋ ጊዜ መስኮት ተዘግቶባል ፡፡የጠቅላይ ሚንሰትሩ አመራር ወደ ለየለት የኢኮኖሚ ቀወስ እየተንደረደ ባለበት በዚህ ስዓትም ከራሱ ፓርቲ የተነሳው የተቃውሞ ማዕበል ወደሱ እየተጠጋ ነው፡፡

አሶሼትድ ፕረስ ትናንት ያወጣው ዘገባም በፓርቲ ውስጥ የለየለት ፉክክር መኖሩን ጠቁሟል፡፡ ህወሓቶች የኢህአዴግ ምክር ቤት ስበሰባ ተጠርቶ እየሄድንበት ያለው መንገድ ይገምገም የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ይህ ጥያቄያቸው ዕውን የሚሆነው ግን ስራ አስፈፃሚው ሲያምንበት ብቻ ነው፡፡

በድርጅቱ መተዳደሪያ ድንብ መሰረት ምክር ቤቱን አስቸኳይ ስበስባ መጠራት የሚችለው ስራ አስፈጻሚው መሆኑ በግልጽ ስፍሯል፡፡ ሁለቱን ሀገራዊ ውሳኔዎች ያስተላለፈው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የኼድኩበት መንገድ ትክክል ነበር ብሎ ምክር ቤቱን ለመጥራት ቢያመነታስ?

ህሀሓቶች ሁለተኛውን አማራጭ የመጠቀም ዕድል አላቸው ፡፡ ይህ ዕድል የምክር ቤቱን አንድ ሶስተኛ ፊርማ ማሰባሰብ ነው፡፡ በዚህ አካሄድ እነሱ የተጓደሉትን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ቢያሟሉ እንኳን የ15 ተጫማሪ የኢህአዴግ ምክር ቤት አባላትን ፊርማ ማሰባሰብ አለባቸው፡፡ ይህ ለህወሓት ከባድ የሚባል አይደለም፡፡ ምክንያቱም በአራቱም ድርጅቶች ቁጥራቸው ይለያይ እንጅ በአዲሱ የኢህአዴግ አመራር ደስተኛ አለመሆንና እየሄደበት ያለው መንገድ በአግባቡ እንዲገመገም የመፈለግ አዝማሚያዎች በመስተዋላቸው ነው፡፡

ይህ ደግሞ የኢህአዴግ ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ እንዲቀመጥ ያስገድደዋል ፡፡ እንዲህ ያለው ያልታሰበ የምክር ቤቱ ስብሰባ ለጠቅላይ ሚንስትሩ የሚዋጥ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ዶ/ር አብይ በፓርቲያቸው ውስጥ ያለን የመረረ ግምገማ በዚህ ጊዜ መጋፈጥ አይፈልጉም፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋናው መንስዔ ከዚህ በፊትም ለመግለፅ እንደሞከርኩት የጠቅላይ ሚንስትሩ አካሄድ ህዝብን በሚጨበጥም በማይጨበጥም ተስፋ ከጎኔ ካደረኩ ኢህአዴግ እኔ ላይ የመወስን አቅሙ ይዳክማል ብለው ከማሰባቸው ይመነጫል፡፡

ይህ አካሄዳቸው ትክክል መሆን አለመሆኑን ለማየት ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ በህወሓት በኩል ግን አሁንም በፉክክሩ ቢሸነፍ እንኳ አንድ የመጨረሻ ጥይት መተኮስ ይችላል፡፡ ይህ ጥይት ከኢህአዴግ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 13 ቁጥር ሁለት የሚነሳ ነው፡፡ ይህ አንቀፅ ማንኛውም ዕህት ድርጅት የግንባሩን ምክር ቤት አሳውቆ በፈለገው ጊዜ ከኢህአዴግ ቤት መውጣት ይችላል ይላል፡፡

ህወሓቶች እዚህ ደረጃ ላይ ሊደርሱ ይችላሉ ወይ? የሚለው ጥያቄ አወዛጋቢ ቢሆንም ከደረሱ ግን በኢህአዴግ ቤት አጥፍቶ መጥፋት መካሄዱ የሚቀር አይመስልም፡፡ በርካታ የጠቅላይ ሚንሰትር አብይ ወዳጆች ገና ከአሁኑ ህወሓት ከኢህአዴግ ቤት ቢሰናበትስ ምን እንዳይመጣ ነው እያሉ መዛት አብዝተዋል፡፡

በእኔ ግምት ሁለቱ ወገኖች ልዩነቶቻቸውን በፍጥነት ካልፈቱ ሀገሪቱ ወደለየለት ቀውስ መግባቷ አይቀርም፡፡ ከሦስት አመታት በፊት ታገኝ ከነበረው የውጭ ብድር በስድስት ዕጥፍ ያነሰ ገንዘብ ማገኘቷ ቀውሷን ያባባሰባት ኢትዮጵያ የፖለቲካ መረጋጋትን ካልፈጠረች ነገዋ አሳሳቢ ይመስላል፡፡ DireTube

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram