fbpx

የሀገሪቱ መሪ “ዶላር የታጨቀ ቦርሳ” ይዘዉ ቢሮ ዉስጥ የተነሱት ፎቶ እያነጋገረ ነዉ

ከሚኖሩበት ዙምባቤ ‹‹ትግላችን›› የተሰኘ መጽሐፍ አሳትመው በ39 የአሜሪካ ዶላር እየቸበቸቡ ነው፡፡ በእርግጥ ሀገር ከመሸጥ መጽሐፍ መሸጥ የተሻለ ነበር፡፡ ምን ዋ¬¬ጋ አለው እንጂ፤ ምክንያቱም ጓድ መንግስቱ መጽሐፋቸውን ቸብችበው ሳይጨርሱ ወይም ገበያው በደራበት ሰአት ‹‹የዚህን አምባገነን ሰው መጽሐፍ በነፃ ኮምኩሙ›› ያሉ የቀድሞ ተቀናቃኞቻቸው፣ ለእኛ ለ‹‹አቅመ መግዛት›› ላልደረስነው በድህረ ገፆች ለቀቁልን፡፡ (መጽሐፉን ያመጡልኝን ሰዎች ውለታ ማሳነስ ተደርጎ እንዳይወሰድብኝ) መቼም የመንጌን መጽሐፍ እንደ ጉልት ቲማቲም፤ ያውም በነፃ እንዲህ በየቦታው እንድናገኘው ያደረገው ኢህአፓ ከተሰኘው ፓርቲ ጥቂት የሙት ትራፊዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በመፃሀፉ ውስጥም ከግንባር ቀደም ተወጋዦች አንዱ ነው፡፡ ‹‹ኢህአፓ››፡፡ ለነገሩ ምን ያደርጉ ብለህ ነው ‹‹ከስልጣን ማውረድ›› ባይሳካለትም፣ እንዲህ ከገበያ ያውርዳቸው እንጂ፡፡

የሆነ ሆኖ የመንግስቱ ኃ/ማርያምን መጽሐፍ አንብቤ ጨረስኩት፡፡ በእርግጥ ይሄ ቅፅ አንድ ሲሆን፣ በቀጣይ ቅፅ ሁለት እና ሶስት ይታተማሉና ጠብቁኝ ስላሉን ጨረስኩ ማለት አይቻልም፡፡ ገና እናነባለን፡፡ እሳቸውም ገና ይፅፋሉ፡፡ እንደ መፀሀፈቸው ጭብጥ ደግሞ አብዮቱም ገና አልተቀለበሰም፡፡ የስልጣን ጥማቸውም ገና አልተቆረጠም፡፡ እናም ጥማቸው ይርካ ዘንድ እንዲህ አሉ፡-

‹‹ኢትዮጵያ ዛሬ ጀግና ብቻ ሳይሆን ሰው አልባ ምድረ በዳ እየሆነች ነው፡፡ ዛሬ ሰው የምንላቸው ኢትዮጵያዊያን አንድም ተገለዋል፣ አንድም ተሰደዋል፣ አብዛኛውም በወያኔ እስር ቤቶች ታጉረዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የሚዋጋና የሚታገል ቀርቶ የሚናገርም የለም፡፡ ከዚህ እጅግ ከከፋና ከከረፋ ጨቋኝና ጎታች ጉልታዊ ስርዓት የኢትዮጵያ ህዝብ ነፃ ያወጡት አብዮታዊያን መሪዎችና የአገሪቱ ወጣቶች በወያኔ እስር ቤቶች በረት የተዘጋባቸው መሆናቸውን እያስተዋለ ሁሉም ዝም ብሏል፡፡›› (73-74)

‹‹ትግላችን›› መጽሐፍ በአንድ በኩል የመንግስቱ ኃይለማርያምን ብዙ ማንበብ በመጠቆም ከስልጣን ከተባረሩ በኋላ ጊዜያቸውን በአግባቡ እንደተጠቀሙበት ያሳያል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እንደተለመደው ራሳቸውን የተከላከሉበት እና የሁልጊዜም ‹‹እኔ ንፁህ ነኝ›› መዝሙራቸውን የዘመሩበት ነው፡፡ ስለዚህም መጀመሪያ ከመጽሐፉ የማይዋጡልንን በወፍ በረር ቃኝተን፣ ለጥቀን ደግሞ የሚዋጡልንን ወይም ፍሬያላቸውን እናያለን፡፡

መንግስቱ ኃ/ማርያም በመጽሐፋቸው ካመሰገኗቸው ሰዎች መካከል ልክ እንደ አቶ በረከት ስምኦን ባለቤታቸውም ይገኛሉ፡፡ በእርግጥ መንጌ እንደ በረከት ‹‹የእኔ ውድ፣ አለኝታ፣ የአንች…›› ምናምን ሲሉ በፍቅር አንጀት አልበሉም የ‹‹አብዮቱ ቆራጥ›› መሪ ናቸውና፡፡ እናም በቀጥታ እንዲህ ነው ያሉት ‹‹…ለመጽሐፉ ዝግጅት የሚያስፈልጉኝን ቁሳቁሶች በማቅረብ ብቻ ሳይሆን የእኔንም ጤንነት በመንከባከብ፣ በመላላክ እንደነሱ ፍላጎት ቢሆን ኖሮ ከወሰደብኝ ጊዜ ባጠረ ጽፌ እንድጨርስ ከእኔ ባለመለየትና በመትጋት የረዱኝ ውድ ባለቤቴ ጓድ ውብአንቺ ቢሻው…››(ገፅ 5)፡፡ መንጌ ጋ አንጀቴ፣ ሆዴ፣ ጉበቴ… አይሰራም፡፡ ወላ ሚስት፣ ወላ ፍቅረኛ፣ ወላ… ‹‹ጓድ›› ነች፡፡ ጓድ መንግስቱ ኃ/ማርያም፤ ጓድ ውብአንቺ ቢሻው…

ይሄም ሆኖ መጽሐፉን ከማየታችን በፊት ጥያቄ ማንሳት ያለብን ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ዘመኑን ስንመረምርው የወጣው የሚወርድበት ሲሆን፤ ማን ያውቃል የወረደውም… መቼም ከመንጌ ጋር በአንድ ነገር እንስማማለን፡፡ የወጣው በሚወርድበት፡፡ ‹‹የወረደው…›› በሚለው ግን እዛው በፀበላቸው፡፡ እናም ጥያቄ እናንሳ፡፡ ለምሳሌ መንግስቱ መፅሐፋቸው በዚህ ወቅት ለምን እንዲታተም ፈለጉ? (እንዲያውም በመጽሐፉ የተነሳ ከእሳቸው ጋር ቅርበት ያለው ሰው እንደነገረኝ መጽሐፉ እንዲታተም የፈለጉት በዘንድሮ መስከረም ሁለት ቀን ነበር፡፡ በሳቸው ደግሞ ሰላሳ ምናምነኛው የአብዮት በአል፡፡ ይሄ ስላልተሳካላቸውም ከመጠን በላይ ተበሳጭተዋል አሉ) ይሄ እንግዲህ የመጽሐፉ አንዱ አለማ ‹‹ራስን ለመከላከል ነው›› ከሚለው ባሻገር መሆኑ ነው፡፡

በእርግጥ በመጽሐፉ ‹‹መቅድም›› ላይ እንደተገለፀው መጽሐፉ ሊፃፍ የነበረው የአስረኛው አብዮት በአል ዋዜማ አካባቢ ነበር፡፡ እንዲያውም ታሪኩ እንዲፃፍ ካሳሰቡት ምሁራን መካከል ፍቃደኛ የነበሩትን አሰባስቦ ‹‹የታሪክ አርቃቂ ምሁራን ኮሚቴ›› ሁሉ ተመርጠው ነበር፡፡ (የኮሚቴው አባላቶች ጓድ ሻለቃ ናደው ዘካሪያስ፣ ጓድ ፍሰሃ ዘውዴ፣ ዶ/ር መርዕድ ወ/አረጋይ፣ ዶ/ር ባህሩ ዘውዴ፣ ዶ/ር ብርሃኑ አበበ እና አቶ ሽፈራው በቀለ እንደነበሩ ጠቅሰዋል) የመጀመሪያው ረቂቅ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተዘጋጅቶ ሲቀርብላቸም መንጌ ‹‹የፖለቲካዊ ስርዓት አመራር አካላት በስልጣን ላይ እያለን የታሪኩ ፀሐፊዎች ያለአንዳች ስጋት ፍርጥርጥ አድርገው ለመፃፍ ድፍረቱ ይኖራቸዋል ወይ?›› ምናልባት ፀሐፊዎቹ ለዚህ ብቃት አላቸው ብለን ራሳችንን ብናሳምንም እንኳን አንባቢው ህዝብ ፀሐፊዎቹ በተሟላ ህሊና የፃፉት ታሪክ ነው ብሎ ይቀበለዋል ወይ? በሚሉ ጥያቄዎች ላይ እንደ ተወያዩበት ገልፀዋል፡፡ ከውይይቱ በኋላም ታሪክ መፃፉ እንዲቆም ተደረገ ይሉናል፡፡

በዚህም ምትክም ለአብዮቱ ሲታገሉ ለተሰዉ እና በህይወት ላሉ አብዮተኞች መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ ያለው ‹‹ትግላችን›› ሀውልት ቆመ ካሉን በኋላ ‹‹ታሪክ የመፃፉን ተግባር ለራሱ ለታሪክና ለህዝቡ እንተወው በሚለው አቋማችን ጸንተን ለአገራችን አንድነት፣ ለአብዮቱ ደህንነትና ለህዝቡ የተፋጠነ ማህበራዊ እድገት ስንታገል በሰሜን አሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም፣ በከሃዲዎቹና አብዮት ቀልባሾቹ ሩሲያዊያን በተጎነጎነ ታላቅ ሴራ የተገፉትና የተመሩት የውስጥ አድህሮት ኃይላት፣ በመምሰልና በማስመሰል አብረውን የተሰለፉ ከሀዲዎች ከያሉበት ተጠራርተውና ተረባርበው የኢትዮጵያ ህዝብ አምጦ የወለደውን አብዮት ቀለበሱት፡፡ የወጠነውንና የገነባውን ሁሉ አፈረሱት፡፡ ለአገሩ ታማኝና አለኝታ፣ ለህዝቡ መከታና የሰላሙ ዋስትና የሆነውን ህዝባዊና አብዮታዊ የመከላከያ ሰራዊት በመበተን ከአንድ አናሳ ብሄረሰብ መካከል በወጡ ጎጠኞችና የባዕድ ምንደኞች፣ ሀገርን በመገንጠል የእናት ጡት ነካሽና አባት አስለቃሽ በሆኑ ህዝብ አሸባሪ ቀማኛ ፋኖዎች ተኩት፡፡

ኤርትራን ገንጥለው በሕብረት አዲስ አበባ የገቡት ምንደኞች ኢትዮጵያ ቅኝ ሆና፣ በቋንቋና በጎጥ ተሸንሽና ዳግም የባሕር በር አልባ ሆነች፡፡ የአገራችን ታሪካዊ ጠላቶችን ወክለው አገራቸውን የወጉ ምንደኞች ራሳቸውን ታጋይና የነፃነት አርበኛ፣ የፍትህ ዳኛ፣ እነሱ ከሳሽም ፈራጅም ሲሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ዘር አጥፊና የጦር ወንጀለኛ ተብሎ መፈረጁን በመስማቴ ለታሪክና ለህዝቡ የተውነውን የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ የትግል ታሪክ እኔ እራሴ ለመፃፍ ተገደድኩ፡፡›› ሲሉ የፃፉበትን ምክንያት ዘርዝረዋል፡፡ በእርግጥ መንጌ ዛሬም ከስልጣን መውረዳቸው የተዋጠላቸው አይመስለኝም፡፡ በእርግጥ እሳቸውን የ‹‹ተንሳኤው ተስፋ›› አድርጎ የሚጠብቅ የለም፡፡ በእርግጥ መንጌን የተኳቸውን መለስንም ቢሆን የሚፈራ እንጂ ተስፋ ያደረጋቸው ያለ አይመስለኝም፡፡ በእርግጥ መንጌ ለጀግናው የኢህአዴግ አመራር አንድ ነገር አስተምረዋል፡፡ ‹‹የፖለቲካ ስልጣን የያዙ ታሪክ ታሪክ ይሰራሉ እንጂ ታሪክ አይፅፉም›› ሲሉ፡፡ እውነት ግን እንዲህ በሽሚያ ታሪካቸውን እየፃፉ እና እያፃፉ ያሉ መሪዎቻችን ይህንን ሲያነቡ ምን ይሉ ይሆን? …ልክ እንግሊዞች ሲገቡ ሀገራቸው፤ ምን አሉ? እንደተባለው… ሰው የለ በእጃቸን ብለው ይሆን? ይሄ ጥያቄ ነው፡፡

መልስ የሚሰጥ ካለ ደህና፤ ካሌለም ወደ መፀሀፉ እንመለስ፡፡ እኒህ ‹‹የግዴታ ታሪክ ፀሀፊ›› ለ17 ዓመት ሀገሪቱን የጦር አውድማ ከማድረጋቸው ባሻገር፣ ከአንድ ትውልድ ወጣት ለወሬ ነጋሪ ጥቂቱ ሲቀር ሙሉውን ለማለቁ ምክንያት ናቸው፡፡ እናም የእልቂቱ መሪ የነበሩት ጓድ መንግስቱ ስለዚህ እልቂት ትንሽ ሳይሉ ነው 505 ገፅ ያለው መጽሐፋቸው ያለቀው፡፡ ወይም እስከ 1970ዓ.ም ድረስ ይተርካል የተባለው መፀሀፍ ያለቀው፡፡ መቼም ‹‹ቀይ ሽብር›› እና ‹‹ነጭ ሽብር›› እየተባለ ዛሬም በፖለቲካ ፋይዳው ለጓድ መለስ ዜናዊ እያገለገለ ያለው ‹‹ሽብር›› በዋናነት የተካሄደው በ1969 እና በ1970 መጀመሪያ ላይ ነው፡፡

ከ1970ዓ.ም በኋላ ‹‹ነጭ ሽብር››፣ በ‹‹ቀይ ሽብር›› በመመታቱ የጎዳና ላይ ግድያውም ሆነ በጠፍ ጨረቃ ከእየእስር ቤቱ እየተጎተቱ አብዮታዊ እርምጃ መወሰዱ ቆሟል፡፡ እናም መንግስቱ በ‹‹ትግላችን›› ስለዚህ ሁኔታ በሚገባ አልገለፁም፡፡ ወይም አንዳች የጥፋተኝነት ፀፀት እንዳለባቸው አላሳዩም፡፡ በግልባጩ ‹‹የኢትዮጵያን ህዝብ ነፃ ያወጡት አብዮታዊያን መሪዎችና የአገሪቱ ወጣቶች በወያኔ እስር ቤቶች በረት የተዘጋባቸው መሆናቸውን እያስተዋለ ሁሉም ዝም ብሏል፡፡›› ሲሉ ከአብዮቱ የተረፈውን ህዝብ ወቅሰዋል፡፡ ወቀሳው ግን ፈር የሳተ ነው፡፡ ይሄ ትውልድ ለአብዮታዊያን መሪዎቹ ባለዕዳ አይደለም፡፡ የሞራልም፣ የውለታም፡፡ ለምን? ከተባለ ከእነሱ አብዮት ያተረፈው በጥይት ተደብድቦ መሞት እና ከሀገር መሰደድ ነው፡፡ በተቀረ አብዮታቸው ልክ እንደኢህአዴግ አብዮት ራሳቸውን ነው የጠቀመው፡፡ እናም ስለታሳሪዎች ከተነሳ ትውልዱ ባለእዳነቱ ለወጣት ታሳሪዎች ብቻ ነው የሚሆነው፡፡

ጓድ መንግስቱ ‹‹ጲላጦስ ነኝ›› ያሉት በቀይ ሽብር ከፈሰሰው ደም ብቻ አይደለም፡፡ ከራሳቸው ጓዶችም ደም እንጂ፡፡ እንደዋዛ ‹‹ለምሳ ሲያስቡን፣ ለቁርስ አደረግናቸው›› እያሉ በጥይት ያስደበደቧቸውን የ‹‹አብዮቱ›› መሪዎችንም ግድያ ምክንያት ፈልገው ለጥፈውበታል፡፡ ለምሳሌ ‹‹አብዮቱ››ን በመምራት ከራሳቸው ከመንግስቱ ሳይቀር ቀዳሚ የነበሩት እና ‹‹አብዮት ልጆቿን ትበላለች›› በሚል ቧልት ስለተበሉት አጥናፉ አባተ ሞት፤ አስፈላጊነት ብዙ ምክንያት ደርድረዋል፡፡

ጓድ መንግስቱ የምስራቁን ጦር ወክለው አጥናፉ በሚመሩት 4ኛ ክፍለ ጦር ጊቢ የተሰባሰቡትን አማፂ ወታደሮች በተቀላቀሉ የመጀመሪያዋ እለት በአዳራሹ በተናገሩት ንግግር አጥናፉ እንደተቀየሟቸው ጽፈዋል… ‹‹እኔ በሰጠሁት አስተያየትና ባቀረብኩት ሂስ ደስተኛ አልነበረም፡፡ ከዓላማ አኳያም ሆነ ከአሰራር ጉድለት የተናገርኩት ሁሉ የሱን (የአጥናፉን) አመራር በመንቀፍ ስልጣን ፍለጋ አድርጎ ነው የተመለከተው፡፡›› (ገጽ 151) ሲሉ ፡፡

በአጠቃላይ አጥናፉ አባተ የኮንጎ ዘመቻ በመሆናቸው የኮንጎ ዘማቾችን የአባል ይከፈለን ጥያቄ ከጀርባ ሆኖ የሚያቀሳስሩ ብቻ ሳይሆን እስከዛሬ ያልሰማነውን ‹‹የክርስቲያን ዴሞክራቲክ ፓርቲ›› የሚባል ፓርቲም በድብቅ መስርተው መንግስቱ ‹‹ለስራ ጉዳይ ወደ ውጭ ሀገር ሄድኩ›› ባለበት ሰዓት መፈንቅለ መንግስት እንደተሞከረባቸው ገልፀዋል፡፡ እንዲሁም የኢህአፓ አባል ነበሩ ሲሉ ከወነጀሏቸው በኋላ በአንድ ሰብሳባ ላይ አጥናፉ አባተ ‹‹በአገራችን ባህል፣ ሃይማትና ታሪክ ጋር ፈፅሞ የማይገጥምና የማይስማማ የሶሻሊስት ስርዓት እንከተላለን ብለን አገሪቱን የጦርነት አውድማ አደረግናት፡፡›› (254) ማለታቸውን ተከትሎ መላው የደርግ አባል አወገዛቸው፡፡ እንዲያውም አንድ አባል ተነስቶ ‹‹ይህ ደርግ እኝህን ሰው ምንድን ነው የሚያደርገው? የኢትዮጵያ ትቅደም ሰይፍ መመዘዝ ያለበት ዛሬ ነው፡፡ የኮሎኔል አጥናፉ ከእኛ ጋር ጉዞ እዚህ ላይ ያበቃል ብሎ መፈክር ሲያሰማ ሁሉም የደርግ አባላት ተነስተው መፈክሩን አስተጋቡ›› (255) ይሉንና ስለግድያው ደግሞ በገፅ 258 ላይ ሲነግሩን ‹‹በየዋህነቱና በክፉ መካሪዎቹ ወደ ኋላ ቃል ኪዳኑን ሳተ፡፡ አብዮት ልጆቿን ትበላለች እንደሚባለው ጓድ አጥናፉንም የፈጠረው ደርግ በላው›› በሚል ስላቅ ነው፡፡

መቼም ይሄ ቧልት ነው፡፡ እውነታው አጥናፉን ደርግ በላው ከሚሉን እኔው እራሴ በላሁት ቢሉ ትልቅ ንሳሐ በሆነላቸው ነበር፡፡ ነበር… ነው ያልኩት፤ በእርግጥ ‹‹ነበር›› በሚል ርዕስ ጓድ ገስጥ ተጫኔ (ዘነበ ፈለቀ) በተባሉና የጓድ ለገሰ አስፋው ልዩ ረዳት በነበሩ ሰው የተፃፈው መጽሐፍ በአጥናፉ ላይ የተወሰነው የሞት ቅጣት በደርግ አባላት እንዳልተወሰነ ያትታል፡፡ በወቅቱም የቋሚ ኮሚቴ አባላት ካልሆኑ በቀር ብዙሃኑ ደርግ በየክፍለ ሀገሩ መበተኑን ይገልፃል፡፡ በገፅ 208 ላይም እንዲህ ይላል ‹‹እነ ብርጋዴር ጄነራል ተፈሪ ባንቲ ሲገደሉ አንድም የደርግ አባል እጅ አውጥቶ አልወሰነም ነበር፡፡ ነገር ግን በተወሰደው እርምጃ አብዛኞቹ የደርግ አባላት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተስማሚነት አዝማሚያ አሳይተዋል፡፡ ‹ርምጃው ልክ ነው› በማለት ሲናገሩም ተደምጠዋል፡፡ የሌ/ኮሎኔል አጥናፉ ጉዳይ ሲነሳ ግን ለየራሳቸው በመፍራት በግልፅ አውጥተው አይናገሩት እንጂ ውስጥ ውስጡን ያጉረመርሙ ነበሩ፡፡ ሐዘናቸውም አመዝኖ ይታይ ነበር፡፡›› ጓድ መንግስቱ ደግሞ በጓድ አጥናፉ ላይ መላው ደርግ ሞት ፈረደባቸው፤ መፈክር ፈከረባቸው፤ ከዛም በቅፅል ስሙ ‹‹አብዮት›› የሚባል ሰይፍ መዘዘባቸው ይሉናል፡፡

ECADF

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram