ዙከርበርግ እና የአውሮፓ ፓርላማ አባላት በዝግ ስብሰባ ሊወያዩ ነው

ብሩሴልስ ላይ ማርክ ዙከርበርግን የአውሮፓ ፓርላማ አባላት በግላዊ መረጃ ጉዳይ ላይ ሊያናግሩት እንደሆነ ገለጹ፡፡

የሚገናኙበት ቀን በይፋ ባይገለጽም የፓርላማ አባላቱ በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚገናኙ ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡

ውይይቱ በዝግ ስብሰባ የሚካሄድ ሲሆን፥ የህብረቱ ፕሬዚዳንትና የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች ይገኙበታል ተብሏል፡፡

አስተያየት ሰጪዎች የዝግ ስብሰባ መሆኑን የተቃወሙ ሲሆን፥ አንዳንዶችም እንደማይገኙ በትዊተር መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ሌሎች ደግሞ ሁለት ቢሊየን የፌስቡክ ተጠቃሚ በቀጥታ ያለውን ነገር ሁሉ ሲያጋራ ስራ አስፈጻሚ በአንጻሩ ተመሳሳይ ምላሽን አልሰጠም በማለት ትችታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

የዝግ ስብሰባውን ተከትሎ ደግሞ ለህዝብ ይፋ በሆነ መልኩ የጥያቄና መልስ ፕሮግራም እንደሚኖረውም ተገልጿል፡፡

የጥያቄና መልሱ ፕሮግራም የተለያዩ የፌስቡክ ስራ አስፈጻሚዎች በተገኙበት በሰኔ ወር ሊካሄድ እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

በፓሪሱ ኢሊዜ ቤተመንግስት ደግሞ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በግንቦት 15 ከዙከበርግ ጋር ለመወያየት እንዳቀዱ ተነግሯል፡፡

ተቀማጭነቱ በለንደን የነበረው ካምብሪጅ አናሊቲካ ከግላዊ መረጃ ጋር በተገናኘ ድርጅቱ በቅርቡ መዘጋቱ ይታወሳል፡፡

ፌስቡክ ባለፉት ጊዜያት ከግላዊ መረጃ አያያዝ ጋር በተገናኘ በርካታ ወቀሳዎችም እየቀረቡበት ቢሆንም በአንጻሩ ይህንን ተቋቁሞ ትርፋማ መሆኑን ቀጥሎበታል፡፡

 

ምንጭ፦ቢቢሲ

Share your thoughts on this post