fbpx

ዕውነትን ለማብቀል በቆፈርነው ምድር

ዕውነትን ለማብቀል በቆፈርነው ምድር
ውሽት ዘራንበት በልተን እንድናድር
ሬሞንድ ሃይሉ በድሬቲዩብ

ጠቅላይ ሚንሰትር አብይ አህመድ ወታደራዊ ሹማምንቱ ጋር በነበራቸው ውይይት ከደካማ ሀገር ጄነራል ይልቅ የጠንካራ ሀገር አስር አለቃ ይከበራል የሚል ሀሳብ ሰንዝረው ነበር፡፡ እውነት ነው ሀገሩ የፈረሰችበት ወታደር ወታደር አይደለም፡፡ ግን የእኛ ሀገርን ወታደር ይህ አገላለጽ ይመጥነዋል?

የኢትዮጵያ መከላክያ ሃይል በሌላ ፅሁፌ ላይ በስፋት እንደጠቀስኩት ሀገር ቀውስ ውስጥ ሲገባ ጎዳና ወጥቶ ህዘብ አልዘረፈም፡፡ ስልጣን ስጡን ብሎ ወደ ቤተ-መንግስት ለመገስገስ አልተቻኮለም፡፡ በዘር ተከፋፍሎ ዕርስ በዕርሱ አለተጫረሰም፡፡

ሌላው ቢቀር ግማሽ ዕድሜውን ሀብት ትዳር ሣይል የተጋደለለት የሀገሩ ድንበር ለጠላቶችህ ይስጣል ሲባል ተቆጥቶ መንግስት ላይ አልዛተም፡፡ አዕላፍ ወንድሞቹን የቀበረበት መሬት በ36 ሰዎች ውሳኔ ለሌላ ሀገር ሲተላለፍ ጨዋታው ፈረሰ አባይ ደፈረሰ ሊለን አልወደድም፡፡

በዚህ የተነሳም ባለፉት ጥቂት አመታት ያልጠፋነው በገዥው ፓርቲ ጥንካሬ ሳይሆን በወታደሩ ምህረት ነው ብሎ መግለፅ ይቻላል፡፡ እንዲህ ከሆነ የጠቅላይ ሚንሰትሩን አገላለፅ በቦታው ለመጠቀም እንሞክር፡፡ በእኔ ግምት የእሳቸው ንግግር ትክክለኛ ቦታው የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ናቸው፡፡ (አንዳንዱ መናኛ ብዙሃን ይላቸዋል፡፡)

ይህ ሲባል በደካማ ሀገር ላይ ካለ ጋዜጠኛ ይልቅ ጠንካራ ሀገር ላይ ያለ መንገድኛ የተሻለ ነገር ስለሀገሩ ማውራት ይችላል እንደማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ከሞላ ጎደል የራሳቸው ኤድቶሪያል ፖሊሲ(ህገ-መንግሰት) አላቸው፡፡ በዚህ ፖሊሲያቸው ላይም ውግንናቸው ለህዝብ መሆኑን በግልፅ አስፍረወል ፡፡ከነፈሰው ጋር ላይነፍሱ የሙያውን መርሆች ሊያከብሩም ቃል ገብተዋል፡፡

ይሁን እንጅ ጉዟቸው እንደ ግመል ሽንት ወደ ኋላ ነው፡፡ ነገአቸው የተሻለ ይሆናል ብሎ ተስፋ ለሚያደርግ ሰውም ቀቢፀ ተስፋን ይመግባሉ፡፡ እዚህ ሀገር ላይ ለፖለቲካ ትርፍም ተብሎ ቢሆን በዕስር ላይ ያሉ ጋዜጠኞች ተፈተዋል፡፡ ፆሙን እራሱ እንዳይፈቱብን እየተባለ የሚቀለድባቸው ጠቅላይ ሚንሰትር አብይ፤ መገናኛ ብዙሃኑን ግን እስካሁን አልፈቷቸውም፡፡

በዚህ የተነሳም የመንግስት መገናኛ ብዙሃን የጠቅላይ ሚንሰትሩ የፕሮፖጋንዳ ማሽን ከመሆን አልዳኑም፡፡ ኢቢሲም ሆነ ፋና፤ የአማራ ቴልቪዥንም ሆነ ኦ ቢ ኤን አሁንም እንደ ገደል ማሚቴ የአለቃቸውን ጮኸት ከማስተጋባት ወጥተው መጠየቅ አልጀመሩም፡፡ ለአመታት ያወገዙትን ነገር ጠቅላይ ሚንሰትሩ ጥሩ ነው ሲሉ ካደመጡ ካለምንም ሀፍረት ያንኑ ያስተጋባሉ፡፡

ሌበራሊዝምን ጭራቅ ነው እያሉ ቴሌቪዥን ላይ ለመተንተን ሲዳክሩ ግማሽ ዘመናቸው ያሳለፉ ጋዜጠኖች ከኢህአዴግ ውሳኔ በኋላ ልብሳቸውን እንኳን ሳይቀይሩ ሌበራሊዝምን የተከተለ ይድናል የሚል ስብከት ጀምረዋል፡፡ ዓለም ባንክ ከሪፖርቱ ጋር በሚያወጣው ምክረ ሃሳብ የኢትዮጵያ መንግስት ትላልቅ ድርጅቶችን ለግል ባልሃብት ያስተላልፍ የሚል አስተየያት ሲሰጥ፤ የኒዎሌበራል ኃይሎች ተላላኪ ስልሆነ ነው ሲሉን ከርመው ትናንት በአንፃሩ አርቆ አሳቢው መንግስታችን ሌበራላይዜሽን ላይ ቀድሞ ለመግባት መወሰኑ ያስመሰግነዋል ሲሉን ተደመጡ፡፡

የኤርትራን መንግስት የሰላም ጥረቱን አፍራሽና የመንደር ጎረምሳ መሆኑን ሲለፉ ከርመው ዛሬ በዛው ምላሳቸው አንድ አምባገነንን መለማመጥ እንደ ትልቅ ነገር ቆርጠው የኤርትራ መንግሰትን ማባበል ላይ ተጠመዱ፡፡ ሻዕቢያ ድንበራችን ወሯልና ኑ ውጡ ብለው አዕላፍ የሀገሬን ልጆች ካስጨረሱ በኋላ እኛን ወራሪ የሚያደርግን ስምምነት ተቀብለው ስለባድመ መሄድ ጠቀሜታ ሊመክሩን ይሞክራሉ፡፡

እሱን ዕንደምን ስትሻገር ደግሞ በሌላ ወሬ ያጃጅሉሃል፡፡ የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ላይ እንኳን ተገኝተው የማያውቁትን ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ለአህጉሩ እያበረከቱ ባሉት አስተዋፆ ከዩጋዳ መንግስት ሽልማት አበረከተላቸው ይባልለሃል፡፡ (እስኪ ይኼ ዜና የገባው ካለ ያብራራልኝ) ከዚህ ሁሉ ነገር ብለህ ሌላ ጣቢያ ላይ ዜና ለማየት ስትቀይር ደግሞ የጣቢያው ክብር ስፖንሰር ይመስል ኢህአዴግ ሆደ ሰፊ ዕርምጃ መውሰዱን አንዳንድ የመዲናዋ ነዋሪዎች ገለፁ፤ የገዥው ፓርቲ ውሳኔዎች አየር መንገዱን ተጠቃሚ ያደርጋሉ …….ወዘተ ሲባል ታደምጣለህ፡፡

ጋዜጠኛው ከሚይዘው ካሜራ የተለየ መሆን አለበት፡፡ ካሜራው ሬክ ብለህ ከተውከው የሚያየውንና የሚሰማውን ሁሉ ይቀዳል፡፡ከዛ ፕሌይ ስትለው የቀደውን ሁሉ ያሰማሃል፡፡ እኛ ሀገር በጋዘኛውና በሚይዘው ዕቃ መካካል ልዩነት ዕየጠፋ ነው፡፡ ያ ባይሆን በካሜራው ያስቀሩትን መረጃ ለምንና እንዴት ብለው በመጠየቅ ለዕውነቱ የሚጠጋ መረጃ ለማድረስ ይባትሉ ነበር፡፡

DireTube

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram