fbpx

ዓባይ የግብጽ ፖለቲካ መጫወቻ ካርታ!

ዓባይ የግብጽ ፖለቲካ መጫወቻ ካርታ! | ሬሞንድ ሃይሉ በድሬቲዩብ

የግብጹ ፕሬዘዳንት አብዱል ፈታህ ኤልሲሲ ትናንት የመጀመሪያ ስራቸው በሀገራችው ቴሌቪዥን ቀርበው አጭር መወድስ ማቅረብ ነበር፡፡ ፕሬዘዳንቱ ሁሌም ያስጨንቀናል የሚሉትን የዓባይ ጉዳይ አንስተው ሌሊቱን በዘለቀው የአዲስ አበባው ውይይት መንግስታቸው አጥጋቢ ውጤት ማግኘቱን ይፋ አድርገዋል፡፡

የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚንሰትር ቃለ አቀባይ አቡ ዛይድም በማለዳ ቲውት ሲያደርጉ የማለዳው ብስራታችን የአባይ ውሃ ላይ የምናደርገውን ውይይት በድል መጠናቀቁ ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ግብጻውያን ዛሬም እራሳቸውን በዓባይ ውሃ ላይ ብቸኛ አሸናፊ አልያም ተበዳይ ከማድረግ አሰተሳሰብ አልተላቀቁም፡፡በዚህ የተነሳም ድርድሩ ሰላመዊ ከሆነ አሸንፈናል እያሉ ዳንኪራ ይመታሉ፡፡ ጥቂት ዕክል ካለበትም እራሳቸውን ብቸኛ ተበዳይ አድረገው ይጮኻሉ፡፡

ለአብነት ያህል ከሳምንት በፊት ካይሮ ላይ ውይይቱ አለመሳካቱ ያበሳጨቸው የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ሳሚ ሸኩሪ ኢትዮጵያ በማናለብኝነት ውይይት እየረበሸች ነው ሲሉ ለህዝባቸው ተናግረዋል ነበር፡፡ ሱዳንንም በማይጠቅም ነገር ጊዜ እያጠፋች ነው ሲሉ ወርፈዋል፡፡

በነገራችን ላይ ይህ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ንግግር ህዝብን ከጎን በማሰለፍ የፕሬዳንት ኤልሲሲን አዲስ የካቢኔ ሹም ሽር ለማለፍ የተደረገ ሴራ አድርገው የሚቆጥሩት ብዙዎች ናቸው። በርግጥም ከሀላፊነታቸው ይነሳሉ የተባሉት ሰው ስለ ኢትዮጵያ ማውራታቸው ከመውረድ እንደታደጋቸው እርግጥ ነው የሚሉ ተንታኞችም ቁጥር ቀላል አይደለም።

ሽኩሪ የዚህ ሴራ አሸናፊ በመሆናቸው ጭምር ይመስላል ትናንት በቃል አቀባያቸው በኩል ድርድሩ ተሳካ ዕልልታ ያስፈልጋል ሱሉ የተደመጡት። ለመሆኑ ማክሰኞ ንጋት ድረስ የዘለቀው የሦስቱ ሀገራት ምክክር ምን ውጤት አሰገኘ?

የግብፁ ኢንዲፐንደንት ጋዜጣ ሀገራቱ ገለልተኛ የሆነ የከፍተኛ ተመራማሪዎች ቡድን ሊመሰርቱ መሰማማታቸው የአሁኑን ብቻ ሳይሆን የነገውንም ውዝግብ ያለዝበዋል፤ የተሸለ መተማመንንም ይፈጥራል ይላል፡፡ በዚህ ሳያበቃም ከፈተኛ ባለስልጣናቱ በዓመት ሁለት ጊዜ እንዲገናኙ የጋራ ፈንድም እንዲመሰረት ከስምምነት መደረሱን አብራርቷል፡፡

በርግጥ እነዚህ የትብብር ማዕቀፉን የሚያሰፉ ስምምነቶች ተቀናጅቶ ለመስራት ጥሩ መደላድል እንደሚሆኑ እሙን ነው፡፡ ይሁን እንጅ የግብጽ የፖለቲካ ኃይሎች ከመርህ ይልቅ ተራ ንትርክ የሚቀናቸው መሆኑ ስምመነቱን አድሮ ቃሪያ እንዳያደርገው ያሰጋል ፡፡የፈርዖን ሀገር ሰዎች ሁሌም የዓባይ ውኃን ትልቅ የፖለቲካ አጀንዳቸው እንዲሆን ይፈልጋሉ፡፡ ለህዝቡ ያላቸውንም ታማኝነት የሚገልጹት ስለህዳሴ ግድቡ ብቸኛ ጠባቃ ነኝ በማለት ጭምር ነው፡፡

በዚህ የተነሳ ዛሬ ቤት ዘግተው ጮቤ የረገጡበትን ስምምነት ነገ እራሳቸው ስጋት አድርገውት ከፊት ይሰለፋሉ፡፡ ያ ባይሆን ከማክሰኞ ሌሊቱ የአዲስ አበባ ዜና ይልቅ ካይሮ ላይ እየቀረበ የነበረው ጥናት ቀልባቸውን ይስበው ነበር፡፡ ይህን ጥናት የካበተ ልምድ አላቸው የሚባሉት የኦክሰፎርድ ዩኒቨርስቲው ተመራማሪ ኬቨን ዊል (ዶ/ር) ያቀረቡት ሲሆን ህዳሴ ግድቡ ለግብጽ ስጋት አለመሆኑንም በውሉ አብራርቷል፡፡ ይሁን እንጅ የፈርዖን ቤተ-መንግስት ሰዎች እንዲህ ያለ ወሬ አይጥማቸውም ። ምክንያቱም ግድቡ ስጋት አይደለም ካሉ ነገ ምን አጅንዳ ያነሳሉ፡፡ DireTube

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram