fbpx

HT

ሐበሻ ታይምስ ሚዲያ

AMHARIC

ዓለምን ያስደመሙት የቭላድሚር ፑቲን አዳዲሶቹ የኑክሌር መሣሪያዎች

የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እ.ኤ.አ. ማርች 1 ቀን 2018 በዓመታዊው የምክር ቤት (ዱማ) ስብሰባ ንግግር ሲያደርጉ፣ ቃላቶቻቸውን ለማፅናት የተለያዩ ተንቀሳቃሽ ምሥሎችን ለማሳየት ንግግራቸውን በተደጋጋሚ ሲያቋርጡ ነበር፡፡

‹‹እስከ ዛሬ ድረስ ማንም አልሰማንም ነበር፣ አሁን ግን ልትሰሙን ግድ ይላችኋል፤›› ያሉት ፑቲን፣ ‹‹እስካሁን ሩሲያን ለማፈንና ለመቆጣጠር የተደረጉ ጥረቶች በሙሉ ፍሬ አልባ ሆነዋል፡፡ እውነቱን ለመቀበል ጊዜው አሁን ነው፡፡ ይህ ባዶ ማስፈራሪያ አይደለም፤›› በማለት ለተቀናቃኝ ኃያላን አገሮች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ፑቲን ይኼንን ዓለም ሲከታተለው የነበረውን ንግግራቸውን በጠንካራ ቃላት እንዲሞሉ ያደረጉዋቸው ዋነኛ ምክንያቶችም በግድግዳው ላይ በንግግራቸው መካከል ሲያሳዩዋቸው የነበሩ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች ውስጥ ሲታዩ የነበሩት፣ ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት መጨረሻ ላይ ተሞክረው ውጤታማነታቸውን ያስመሰከሩት አኅጉር አቋራጭ ሚሳይሎችና የውኃ ውስጥ በራሪ ድሮኖች ነበሩ፡፡

ፕሬዚዳንቱ ንግግር እያደረጉ በመሀል ሲያሳዩዋቸው ከነበሩ በኮምዩውተር የተቀናበሩ ምሥሎች በአንዱ ከሩሲያ የተወነጨፈው ሚሳይል አትላንቲክ ውቅያኖስን አቋርጦ፣ የላቲን አሜሪካን ጥጋ ጥጎች ታክኮ ወደ ሰሜን አሜሪካ ክልል ሲገባ ያሳያል፡፡ የእርሳቸው ሚሳይል እጅግ ትኩረት ሊስብ የቻለው ግን ‹‹ሊገታ የማይችል›› ነው መባሉ ነው፡፡

ፑቲን እንደሚያሸንፉበት ግምት የተጣለበት ምርጫ የሁለት ሳምንታት ዕድሜ ሲቀረው፣ ባለፈው ሳምንት በዱማ ያደረጉት ንግግር ስድስት ዓይነት መሣሪያዎች ይፋ የሆኑበት ነበር፡፡

የመጀመርያው ርቀት የማይገድበው በኒክሌር የተደገፈ አኅጉር አቋራጭ ሚሳይል ነው፡፡ ይኼ መሣሪያ ይዞት የመጣው እምብዛም ለየት ያለ ነገር እንደሌለው ተነግሮለታል፡፡ በ1960ዎቹ የአሜሪካ አየር ኃይል ዝቅ ብሎ የሚምዘገዘግ ሚሳይል ላይ ምርምር ሲያደርግ እንደነበር ያስታወሱም ነበሩ፡፡

ይህ መሣሪያ በተለይ ከምድርም ሆነ ከህዋ የሚተላለፉ ቅድመ ማስጠንቀቂያዊችም ሆኑ የሚሳይል ማስተጓጎያና መከላከያ መሣሪያዎች፣ ሊለዩትና ሊያስቆሙት እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡

ነገር ግን ሩሲያ እንዴት ይኼንን ሚሳይል ወደ ተግባር ልታመጣው ትችላለች የሚለው ጥያቄ ግን ብዙዎችን እያወያየ ነው፡፡ ሆኖም ቭላድሚር ፑቲን፣ ‹‹ይህ መሣሪያ በዓለም ላይ የትኛውም አገር የለውም፣ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ያኔ ደግሞ እኛ የተሻለ መሣሪያ ይኖረናል፤›› ሲሉ ሚሳይሉን ቀድመው የሩሲያ ማድረግ መቻላቸውን አስረግጠዋል፡፡

ሙከራ ተደርጎ ውጤታማ መሆን እንደቻለም በሙከራ ጊዜ የተቀረፁ ምሥል ተጠቅመው ለማረጋገጥ ሞክረዋል፡፡

ሁለተኛው ፑቲን ይፋ ያደረጉት የመሣሪያ ዓይነት ‹አቫንጋርድ› የተሰኘ ነው፡፡ ከሰማይ የተወረወረ የኮከብ ስባሪ ይመስል ዒላማውን ድባቅ ሊመታ የሚችልና እንደ ቀደመው ሚሳይል ሁሉ ከህዋም ሆነ ከምድር የሚደረጉ ክትትሎችን በቀላሉ ሊያልፍ የሚችል እንደሆነ ገልጸው፣ አቅጣጫውን በፍጥነት በመቀየር ዒላማው ዘንድ ለመድረስ የሚያደርገው ጉዞ ከዕይታ የተሰወረ ነው ብለዋል፡፡

እንዲህ ያሉ መሣሪያዎች በአጭር ጊዜ ወይም ያለምንም ማስጠንቀቂያ በጠላት ንብረቶችና ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ አደጋ ለመጣል ተወዳዳሪ የሌለው ይሆናልም ተብሏል፡፡

ሳርማት የተባለው አርኤስ 28 ከባድ አኅጉር አቋራጭ ባሊስቲክ ሚሳይል ሌላኛው ፑቲን በምሥል ተደግፈው ይፋ ያደረጉት መሣሪያ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2014 ሥራው ተጀምሮ እ.ኤ.አ. በ2021 ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቅ የሚሳይል ዓይነት ነው፡፡ ካሁን በፊት ጥቅም ላይ ይውል የነበረው አገር 38 የተባሉትን ሚሳይል የሚተካ ሲሆን፣ የአሜሪካን የሚሳይል መለያ መሣሪያዎች ማለፍ የሚችል መሆኑ ተነግሮለታል፡፡

ይህ ሚሳይል የሚሸከማቸው የተለያዩ መሣሪያዎች ሲኖሩት፣ በተፈለገ ርቀት በዒላማውን ለመምታት የሚያስችለው ቴክኖሎጂ ገጥሞለታል፡፡ ፑቲን ይኼንን መሣሪያ በተመለከተ ሲያስረዱ የተጠቀሙበት በኮምፒዩተር የተቀነባበረ ቪዲዮ፣ ሚሳይሉ እነዚህን መሣሪያዎች የአሜሪካ ግዛት በሆነችው ፍሎሪዳ ላይ ሲጥል ያሳያል፡፡

ሌላው ግርምትን የፈጠረውና ፑቲን ይፋ ያደረጉት መሣሪያ የውኃ ‹‹ውስጥ ድሮን›› ሲሆን፣ ይህም ኑክሌር አቅም ያለው ነው፡፡ ይህ መሣሪያ ለረዥም ጊዜያት ሩሲያ እየሠራችው ነው እየተባለ ቢወራም፣ ከመንግሥት የተሰጠ ምንም ዓይነት ማረጋገጫ ግን አልነበረም፡፡ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት ይህ የባህር ሰርጓጅ መሣሪያ የሚሳይል መከላከያዎችን ለማምለጥ እስከ ዛሬ ድረስ ከነበሩ የተለያዩ ዕርምጃዎች ለየት የለ እንደሆነ ተነግሮለታል፡፡

ስድስተኛውና የመጨረሻው የሚሳይል ዓይነት 1250 ማይል ርቀት መሄድ የሚችልና ከድምፅ ፍጥነት በ10 እጥፍ ሊጓዝ የሚችል ዘመናዊ መሣሪያ ነው ተብሏል፡፡

ምንም እንኳን ፑቲን እነዚህም መሣሪያዎች ቢያስተዋውቁም፣ ሩሲያ ረዥም ርቀት ላይ ያለን ዒላማ የመምታት ውስንነት ለማስተባበል የተጠቀሙበት ስትራቴጂ ነው በማለት ያጣጣሉት አልጠፉም፡፡ ፑቲን ይኼንን ይፋ እንዲያደርጉ ያደረጋቸውም አሜሪካ በረዥም ርቀት ሚሳይል ያላት የመሪነት ሚና አሳስቧቸው እንደሆነም ያወሳሉ፡፡

ከፑቲን መሣሪያዎች ይፋ መሆን በኋላ የተለያዩ ሚዲያዎች የማይበገረው የሩሲያ ሚሳይል ይፋ ሆነ እያሉ ይፋ ሲያደርጉ፣ አሜሪካ ደግሞ ምንም ይሁን ምን ለሚመጣው ሁሉ ዝግጁ ነኝ ስትል በፔንታጎን ቃል አቀባዩዋ ዳና ዋይት አማካይነት አስታውቃለች፡፡ ‹‹ለሚመጣው ሁሉ ዝግጁ ነን፤›› ሲሉ ዋይት ተናግረዋል፡፡

ቃል አቀባዩዋ ይኼንን ይበሉ እንጂ አሜሪካ የሚሳይል መከላከል አቅሟ እጅግ ደካማ እንደሆነ፣ ይህም ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ አሜሪካ አብራው የኖረችው እውነታ እንደሆነ የሚናገሩ ተቺዎች አሉ፡፡ ስለዚህም እንኳን የተባሉት የሚሳይል አቅሞች ተጨምረው ይቅርና አሁን ባላት የሚሳይል አቅም ሩሲያ ከአሜሪካ በእጅጉ የላቀ የሚሳይል አቅም እንዳላት የሚናገሩ ብዙ ናቸው፡፡

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram