fbpx

“ወጣቱ በልብ ወለድ ላይ የሚያውቃት አስመራ ታሪክ ሆናለች”

“ ወጣቱ በልብ ወለድ ላይ የሚያውቃት አስመራ ታሪክ ሆናለች”

                                   አቦይ ጣዕመ ለምለም (44 ዓመት በዛላንበሳ ከተማ የኖሩ ኢትዮጵያዊ)

 

በአንድ ወቅት ከሰው ምላስ እና ከመገናኛ ብዙሃን ስሟ የማይጠፋ የነበረ አሁን ግን በድብርት እና በጥልቅ እንቅልፍ  ላይ ያለች በምትመስለው እና በርካቶች ህይወታቸውን በገበሩባት የሰሜኗ ጭፍ ከኤርትራ ጥቂት ኪሎ ሜትር ርቀቶች… ዛላንበሳ ከተማ ላይ ተገኝቻለሁ፡፡

ዛላንበሳ  በሻዕቢያ ከተወረረች በኋላ ከመኖር ወደ አለመኖር  ተሸጋግራ የነበረች ከተማ ናት፡፡ ለዓመል እንኳን አንድም ቤት እንዳይታይ አድርጎ ከተማዋን ያፈራረሳት እና  የጣራ ቆርቆ

ሮ እንኳን ሳይቀር ጭኖ ወደ ሀገሩ ያጓጓዘው የሻዕቢያ ጦር  ለዚህ ማሳያ ይሆን ዘንድ ያወደመው የዱቄት ፋብሪካ ዛሬም ህያው ምስክር ሆኖ ተቀምጧል፡፡ ሻዕቢያ በዚህች ከተማ መቀመጫውን ሲያደርግ ለዘመናት እቆይበታለሁ በሚል ዙሪያ ገባዋን በምሽግ ያጠረ መሬቷን አንደፍልፈል ቦርቡሮ  ወና ያደረጋት አሳዛኝ ከተማ ናት ፡፡ ጦሩ እንደህልሙ ሳይሆን መሬቱን ለቆ ቢወጣም ጥሎ ያለፈው መጥፎ አሻራ ግን ዛሬም ዛላንበሳን ከድብርቷ እንዳትነቃ  ያደረጋት ይመስላል፡፡ መንገዶቿ ወና ናቸው… መንግስት ከሚከተለው ፖሊሲ አንጻር ሰላምም ጦርነትም በሌለበት ሁኔታ ለዓመታት የተቀመጠችው ዛላንበሳ ነገ ምን እንደሚፈጠር ማወቅ ባልቻሉ ጥቂት ሰዎቿ ኑሮን ተያይዛዋለች፡፡

ዛላንበሳ የኤርትራ ሬዲዮም ሆነ ቴሌቭዥን ለመከታተል አንቴና እንጂ ዲሽ የማያስፈልግባት የሀገራችን የተለየች ክፍል ናት ከኤርትራ በጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ የምትገኘው  የዚህች ከተማ ህዝቦች ካለ ዲሽ ከአስመራ ሬዲዮ በቀጥታ በሚተላለፉ የኤርትራ ሙዚቃዎች ሲወዛወዙ ማየት የሚቻልባት ውብ ግን አሳዛኝ ከተማ ናት፡፡

ለመጀመሪያ ግዜ  ዛላንበሳን ስረግጥ  በህይወት አሉ ወይ? ስል የጠየቅኩት ስም አቦይ ጣዕመ ለምለምን ነበር፡፡ ጋዜጠኛና ደራሲ መሀመድ ሰልማን  መሀሙድ ጋ ጠብቂኝ በተሰኘ ታዋቂ ስራው የሚያነሳቸው የኢትዮጵያ ሆቴል ባለቤቱ አቦይ ጣዕመ  ከወረራው ሶስት ቀን ቀደም ብለው ወደ ከተማ ቢሸሹም ከጦርነቱ በኋላ ግን ዛሬም እዛችው ከተማ ላይ ናቸው፡፡ ከአቦይ ጣእመ ጋር ዛላንበሳ በሚገኘው እና የሀገር መከላከያ ሰራዊት ዘላንበሳን አስለቅቆ ባንዲራውን ከሰቀለበት አደባበይ ፊት ለፊት በሚገኘው ኢትዮጵያ በተሰኘው ሆቴላቸው በረንዳ ላይ ቁጭ ብለን ስለ ሁለቱ ህዝቦች  እና ስላለፈው ዘመን እንዲህ አወጋን ፡፡

 

ሸገር ታይምስ፡- አቦይ ስላየሁዎት ደስ ብሎኛል

አቦይ ጣዕመ፡- እንኳን ደህና መጣህ ልጄ

ሸገር ታይምስ፡-  ጤናዎት እንዴት ነው? አሁንም ስራ ይሰራሉ ጠንካራ ነዎት

አቦይ ጣዕመ፡- አዎ በዚህ በዚህ እንኳን አልታማም እኔ የአንተ አባት ጠንካራ ነኝ ፡፡

ሸገር ታይምስ፡- ዛላንበሳ ምን ያህል ዓመት ኖሩ?

አቦይ ጣዕመ፡- እድሜዬን በሙሉ በለው 44 ዓመት ነው በዛላንበሳ ከተማ የኖርኩት፡፡ ኢትዮጵያ የሚባል ሆቴል አለኝ በንግድ ስራ ተሰማርቼ ነው የምኖረው፡፡

ሸገር ታይምስ፡-  አስኪ  ከጦርነቱ በፊት ስለነበረችው ዛላንበሳ እና የሁለቱ ሀገር ህዝቦች ይንገሩን?

አቦይ ጣዕመ፡- ምኑን እነግርሀለሁ ልጄ…. ከጦርነቱ በፊትማ የዚያ.. የዚህ የሚባል ነገር አልነበረም፡፡ ገበያቸው እኮ እዚህ ነበር፡፡ እኛ ወደ እነሱ የሚያስኬደን ብዙ ገበያ አልነበረም፡፡ እነሱ ግን የሚፈልጉትን ሁሉ የሚጠቀሙት እና የሚሸምቱት ከዚሁ ከእኛ ገበያ ነበር፡፡ እዚህ ተገበያይተው ውለው አድረው ነበር የሚሄዱት እኛም እንደዛው፡፡

ሸገር ታይምስ፡-  የጦርነቱን ወቅት እንዴት ያስታውሱታል?

አቦይ ጣዕመ፡- እኛ ጦርነቱ ሊጀመር  ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ነው ሸሽተን ወደ አዲግራት ከተማ የሄድነው የሻዕቢያ ሰራዊት ጥሶ ሲመጣ የኛ መከላከያ ሰራዊት ደንጎሎ ከሚባለው ቦታ ሊያሳልፋቸው አልቻለም፡፡ ግን ሻእቢያ በቆየበት ጥቂት ግዜያትም ቢሆን ቀላል የማይባል ጥፋትን ነው በከተማዋ ላያ ያደረሰው፡፡

 ሸገር ታይምስ፡- ቀድማችሁ ስላወቃችሁ ነው አከባቢውን የለቀቃችሁት ወይስ መንግስት ነው ያስለቀቃችሁ?

አቦይ ጣዕመ፡- የሻዕቢያ ሰራዊት ባልተለመደ ሁኔታ ጠጋ ብለው መሬት መቆፈር ሲጀምሩ እናያቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ሊወሩን ነው አልያም በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ሊከፍቱ ነው ብለን በጭራሽ አላሰብንም ነበር፡፡ ሁኔታው ግን ትንሽ ከፍ እያለ ሲመጣ እና ጥርጣሬ ሲያድርብን ለግዜው ዞር እንበል ያልን ለቀን ወጣን እኔ በነበረችኝ መኪና እቃዎቼን ይዤ በወጣሁ በሶስተኛው ቀን  የሻዕቢያ ሰራዊት ጦርነቱን ከፈተ አዲግራት ላይ ሆነን ሁሉንም እንሰማ ነበር፡፡

ሸገር ታይምስ፡- በወቅቱ ከተማዋን ለቀው ያልወጡ ሰዎች አልነበሩም?

አቦይ ጣዕመ፡- ያልወጡ ብዙ ሰዎች ነበሩ በርካታ ነጋዴዎችም ነበሩ ከእኛ በሁዋላ በነበሩት ቀናት ነው ሰው የወጣው እንጂ ብዙ ሰው ነበር እኮ

ሸገር ታይምስ፡-  ያልወጡ ሰዎች መጨረሻ ምን ሆነ ታዲያ?

አቦይ ጣዕመ፡- እኔ እንኳን የማውቃቸው አስር ነጋዴዎች ነበሩ እስካሁን ድረስ የት እንደደረሱ አይታወቅም

 ሸገር ታይምስ፡- ሰለሰዎቹ በህይወት መኖር አለመኖር የተሰማ ነገር የለም?

አቦይ ጣዕመ፡- አይ የኔ ልጅ…..በጭራሽ ይግደሏቸው ይሰሯቸው የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ድንገት ተሰወሩ ይሄው እስካሁን ድምጻቸው የለም፡፡ በህይወት ይኖራሉ ብሎ ማመን ግን ይከብዳል፡፡

ሸገር ታይምስ፡- ሻዕቢያ ዛላንበሳን ሲወር የመጀመሪያ ተግባሩ ምንድን ነበር?

አቦይ ጣዕመ፡- ማፍረስ ነበር፡፡ አንድም ለምልክት እንኳን የቀረ ቤት አልነበረም፡፡ የበር መዝጊያ ፣ ቆርቆሮ፣ ድንጋይ ሳይቀር ነው የወሰደው የቀረው ነገር አልነበረም፡፡ እንደመንግስት ይዞ እንኳን ቢቀመጥበት መልካም ነበር፡፡ የሱ ምርጫግን ማፍረስ እና ማውደም ነበር፡፡ እንዳለ ከተማዋን ወና ነው ያደረጋት በቃ ሜዳ! እንዴት አንድ መንግስት ነኝ የሚል አካል ማውደም እና ማፍረስን እንደመረጠ ሁሌም ይገርመኛል፡፡ እዚህ አጠገባችን የምታየውን የዱቄት ፋብሪካ ሳይቀር እንደምታየው አውድመውት ነው የሄዱት፡፡ ያው ከጦርነቱ በኋላ መንግስት ባደረግልን የገንዘብ ድጋፍ ነው እንደገና እንደ አዲስ ከተማዋን ገንብተን ነው ነቃ ያደረግናት፡፡

 ሸገር ታይምስ፡- አሁን ጦርነት ይነሳል የሚል ስጋት የለባችሁም?

አቦይ ጣዕመ፡- አሁንማ ምን ሊያመጣ? መከላከያው አለ እኮ፡፡ ያኔም በአሳቻ እና ባልታሰበ ሰዓት ሆኖ እኮ ነው፡፡ አሁን የሚሰጋና ጦርነት ይነሳል ብሎ የሚፈራ ማንም ሰው የለም፡፡

ሸገር ታይምስ፡-  ቀደም ሲል ከሌሎች ከተሞች ጋ የምትገናኙት ግማሽ በግማሽ በእነሱ ምድር ላይ አቋርጣችሁ ነበር አሁንስ?

አቦይ ጣዕመ፡- እንዳልከው ከጦርነቱ በፊት በኤርትራ ምድር ላይ አቋርጠን የምናልፍበት መንገድ ነበር አሁን ያ ቀርቷል በእግር የሚሄድ ሰው ካልሆነ በቀር ወደዛ የሚያገናኘው መንገድ ቀርቶ አዲስ መንገድ ተሰርቷል፡፡ በዛ ነው የምንሄደው እንዳልኩህ ያንን መንገድ ህዝብ ሊጠቀምበት እና ሊንቀሳቀስበት ይችላል ተሽከርካሪ ግን በዛ መንገድ አይሄድም፡፡

ሸገር ታይምስ፡- ህዝቡ ግን ይገናኛል?

አቦይ ጣዕመ፡- ያው እርሻ ምናምን አላቸው  መተያየቱ ሊኖር ይችላል ግንኙነቱ ግን ሙሉ ለሙሉ ተቋርጧል፡፡ ከእነሱ በኩል ብዙ ግዜ እየጠፉ ወደዚህ የሚመጡ አሉ መንግስት እነሱን እየተቀበለ ወደ ስደተኛ ጣቢያ ይልካቸዋል በየቀኑ ነው የሚመጡት፡፡

ሸገር ታይምስ፡- የሚመጡበት ምክንያት ምን እንደሆነ ትሰማላችሁ?

አቦይ ጣዕመ፡- የሚያስመጣቸው ጭንቀት እንጂ ምቾት  አይደለም፡፡ ይህንን ብዙ ግዜ እንሰማለን በኤርትራ ምድር ያለው ነገር ሲከብዳቸው በብዙ መከራ እና እንግልት ወደዚህ መጥፋታቸውን ነው የሚነግሩን፡፡

ሸገር ታይምስ፡- የኤርትራ ቴሌቭዥን ካለ ዲሽ ነው የሚታየው ይባላል እውነት ነው?

አቦይ ጣዕመ፡-  አዎ እውነት ነው፡፡ ቆይ ልክፈትልህ እና አንተ ራስህ አይተህ አረጋግጥ ( ቴሌቭዥኑን ከፍተውት ተመለሱ እንደተባለውም ያለ ሪሲቨር እና የዲሽ ሳሕን የኢሬ ቲቪ ሀገር ውስጥ ካሉ አንዳንድ ጣቢያዎች በተሻለ ጥራት ይታያል) ድሮ የተተከለ የኤርትራ አንድ ዲሽ ከዚህ አንድ አስራ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው ያለው፡፡ ዛላንበሳ ላይ ሆነህ የእነሱን ቴሌቭዥን በዲሽ ሳይሆን በአንቴና ነው የምታየው በጣም ቅርብ ነው፡፡

ሸገር ታይምስ፡- የሁለቱ ህዝቦች መጪ ግዜን እንዴት ያዩታል ተለያይቶ መቅረት ወይስ..?

አቦይ ጣዕመ፡- አንድ መልክ አንድ ቋንቋ ያለን ሰዎች ነን፡፡ ይሄ ነገር መጣ እንጂ ዝምድናም ጉርብትናም ነበረን እኮ፡፡ አብረን ክፉውንም ደጉንም አሳልፈናል ፣ አብረን ኖረናል ችግሮች መፍትሄ ቢያገኙና ሁኔታዎች በሰላም ቢፈቱ ህዝቡ ለመገናኘት አንድም ቀን አያድርም ይሄ ነው በዚህም በዚያም ያለው ስሜት ሰላሙ ለሁላችንም ነው ጦርነት ግን የሰው ሕይወት ይበላል ለማንኛውም ወገን ጥቅም የለውም ሰላም እንዲሆን ነው ፀሎታችን፡፡

ሸገር ታይምስ፡- ይሆናል ብለው ያስባሉ?

 አቦይ ጣዕመ፡- ሰላሙ በእርቅ ቢሆንልን የተሻለ ነበር ያለጦርነት ማለቴ ነው፡፡ ጦርነት ብዙ ነገር ያበላሻል የድሮዋ እና የአሁኗ ኢትዮጵያ አንድ አይደለችም፡፡ በልማቱ ትልቅ ነገር እየተሰራ ነው ይሄን ያመጣው ትግል ነው ትግሉ ወደ ሰላም ስለተቀየረ ነው በልማቱ እድገት እያሳየን ያለነው፡፡ ሀገራችን አድጋለች ስለ ሰላምም ብዙ ግዜ ነው የምትሰብከው ከእነሱ ጋርም በሰላም እና በእርቅ ቢፈታ የሁላችንም ምርጫ ነው፡፡

 ሸገር ታይምስ፡- እነሱስ ሰላሙና እርቁን ይፈልጉት ይሆን?

አቦይ ጣዕመ፡-  ሰላም ማግኘት ማን የሚጠላ አለ ብለህ ነው? የሻዕቢያ መንግስት ይጠላው ይሆናል እንጂ ህዝቡማ በየቀኑ እየመጣ አይደል እንዴ? በቀን ውስጥ በርካታ ሰው እኮ ነው እየጠፋ የሚመጣው ጠፍተው የሚመጡትን ኤርትራውያን ስንጠይቃቸው የሚነግሩን ነገር ይሄንኑ ነው ያቺ በልበወለድ ላይ ወጣቱ የሚያውቃት አስመራ ታሪክ ሆናለች ቢፈቀድለት ሲቪሉ ህዝብ ኤርትራን በአንድ ቀን ለቆ ከመውጣት አይመለስም ይሄንኑ ነው የሚነግሩን፡፡

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram