fbpx

ኮለኔል አብዲሳ አጋ ሲታወሱ| Fana Television

በኦሮሚያ ወለጋ የተወለደው አብዲሳ የኢትዮጲያን ጦር የተቀላቀለው በ14 አመቱ ሲሆን ጣልያን ኢትዮጲያን ስትወር አገሩን ለመከላከል በሚደረግ ውጊያ ላይ መሳተፍ ጀመረ። እጅግ ዘመናዊ መሳሪያዎች ከታጠቀው የጣልያን ጦር ጋር በሚደረገው ውጊያ ላይ ባጋጠመው የመቁሰል አደጋ ህክምና ላይ ከቆየ በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ ፒያሳ አካባቢ በሚገኝ ቤት በቁም እስር ላይ ነበር። በኋላ ጣልያን ኢትዮጲያን እንዲያስተዳድር በሾመችው ግራዚያኒ ላይ የመግደል ሙከራ ከተደረገ በኋላ አብዲሳ አጋ እና ሌሎች 37 የሚሆኑ የቁም እስረኞች ተጠርጣሪ ተብለው በከባድ ስቃይ እስር ቤት ከቆዩ በኋላ በወቅቱ የጣልያን ግዛት በነበረችው በሱማሊያ በኩል ወደ ሲሲሊ ተወስዶ በጣልያን አገር የጦር እስረኛ ተደረገ።

በእስር ቤት ጠባዎች ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበት አብዲሳ እዛው ታስሮ የሚገኝ ሁሊዮ የተባለ የዩጎዝላቪያ ምርኮኛ በጋራ እቅድ በማውጣት ከእስር ቤት ማምለጥ ቻለ። ከእስር ካመለጡ በኋላ ከፋሺስት ጣልያን ወታደሮች በመደበቅ እና በመሸሽ ፋንታ በአብዲሳ መሪነት እና እቅድ አውጪነት በሌሊት ታስረው ወደነበረበት እስር ቤት ተመልሰው ጠባቂዎቹ ላይ ጥቃት በመፈጸም የታሰሩትን እስረኞች በሙሉ ነጻ በማውጣት የኢትዮጲያውያንን ጀግንነት በአድዋ ብቻ ሳይሆን በጣልያን ምድርም ያስመሰከረ ድንቅ ተዋጊ ነበር። የአብዲሳ ጀግንነት በዚህ አላበቃም ከእስር ቤት ያስመለጧቸውን ሰዎች በማሰባሰብ የራሱን ጦር ካደራጀ በኋላ ጣልያኖችን በገዛ አገራቸው ያንቆራጥጣቸው ገባ። ከአድዋ ጀምሮ የኢትዮጲያውያንን ወኔ የተረዱት ጣልያኖች የአብዲሳን ጦር በፍርሃት ያዩ የነበረ ሲሆን በተለያዩ ቦታዎች ከጣልያን ጦር ጋር በመዋጋት ብዙ ድሎችን እያስመዘገበ ነበር። ቆራጥነቱን የተረዱት ጣልያኖች የሚያረጉት ግራ ቢገባቸው ከበርካታ ስጦታዎች ጋር ጦሩን ይዞ የጣልያንን ሰራዊት እንዲቀላቀል መማጸን ጀምረው ነበር። ለፋሺስት ጦር መዋጋት አገር መክዳት እንደሆነ አስረግጦ የተናገረው አብዲሳ ትግሉን አፋፍሞ በቀጠለበት ወቅት የሁለተኛው የአለም ጦርነት ተቀሰቀሰ።

የተባበሩት የአሜሪካ እና እንግሊዝ መንግስታት ከጀርመን ጋር ያበረችውን ጣልያንን እየተዋጉ በነበረ ሰዓት ስለ አብዲሳ ዝና ከሰሙ በኋላ ለጦሩ የሚገባውን ድጋፍ በማድረግ የፋሺስት ስርዓቱን ለማዳከም ከሚያግዙ መንገዶች አንዱ ሆኗቸው ነበር። በድጋፉ በመጠናከር ፋሺስቱን ሰራዊት ማርበድበድ የቀጠለው አብዲሳ የጣልያን ጦር ተሸንፎ ዋና ከተማዋ ሮም በአሜሪካን እና እንግሊዝ የሚመራ ጦር እጅ ስር ከወደቀች በኋላ የሚመራቸውን ከተለያዩ አገር የወጡ ወታደሮች በሙሉ ክንዳቸው ላይ የኢትዮጲያን ባንዲራ እንዲያስሩ በማድረግ የሃገሩን ባንዲራ እያውለበለበ ሮም ከተማ ሲገባ በአለም አቀፉ ህብረት ጦር ትልቅ አቀባበል ተደርጎለት ነበር። ከዛም በኋላ ከተጨማሪ ወታደሮች ጋር በአለም አቀፉ ህብረት ስር የሚመራ ጦር መሪ በመሆን ጀርመንን ለማሸነፍ በሚደረገው የመጨረሻ ውጊያ ላይ ተሳትፎ ግዳጁን በሚገባ በመወጣት የኢትዮጲያን ባንዲራ ከእጁ ሳይለይ በርካታ የጀርመን ከተሞችን ነጻ ማውጣት ችሎ ነበር።

ከጦርነቱ መገባደድ በኋላም የእንግሊዝ፣ የካናዳ እና የአሜሪካ መንግስታት ጦራቸውን ተቀላቅሎ እንዲቀጥል በርካታ ጥቅማ ጥቅሞችን አቅርበውለት ነበር። እብዲሳ ግን ኢትዮጲያ ምንም ያህል ድሃ ብትሆንም ህዝቡን እና መንግስቱን ጥሎ እንደማይሄድ አስረግጦ በመናገር ጥያቄውን ውድቅ አደረገ። በዚህ የተናደዱ ምዕራብውያንም በፈጠራ ወንጀል ከሰው ወደ እስር ቤት አስገብተውት ነበር። በኋላም እስሩ ወደ ገንዘብ ቅጣት ተቀይሮ ከተከፈለ በኋላ በክብር ወደ ሃገሩ ሊመለስ ችሏል። ወደ ኢትዮጲያ ከተመለሰ በኋላ ሰራዊቱን በቅንነት ያገለገለው አብዲሳ በኮረኔልነት ማዕረግ የአጼ ሃይለስላሴ ልዩ ጠባቂ ጦር እየመራ ቆይቶ ንጉሱ ከስልጣን ከወረዱ ከጥቂት አመታት በኋላ ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል።

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram